ከቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር እውቅና ውጪ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የፓርላማ ተመራጮችን በመላክ “ልዩ ዘመቻ” የጀመሩት የቀድሞው የመኢአድ አባላት በደረሱባቸው ክልሎች ሁሉ ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠማቸው መሆኑን የዜና አገልግሎቱ ምንጮች ገለፁ፡፡
በአቶ አባይነህ ብርሃኑ አመራር ስር የሚገኙት እነዚህ ቡድኖች እስካሁን ካደረጓቸው ጉዞዎች የቅንጅቱ ከፍተኛ ድጋፍ ባለበት ደሴና ጎንደር ላይ “አካሄዳችሁ የፓርቲውን ሕልውና አደጋ ላይ ጥሎታል” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ወደ ደሴ ተጉዘው የነበሩት የላዕላይ ም/ቤት አባል አቶ ወንዶሰን ተሾመ “የተከፈለው መስዋእትነት ለቅንጅት እንጂ ለመኢአድ አልነበረም” በማለት አባላትን በማደራጀትና በመንቀሳቀስ አጀንዳ የሄዱትን አባል ሕዝቡ ዳግም እንዳይመለሱ አስጠንቅቆ አባሯቸዋል፡፡
ለተመሳሳይ ተልእኮ ወደጎንደር የሄድት አቶ ግርማም እንዲሁ በፓርቲው ስም ከመነገድ እንዲቆጠቡ በሙሉ ድምፅ አሳስቧቸዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም ሀገረ ማርያም የደረሰው ቡድን ተመሣሣይ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡