ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከውስጥም ከውጭም ከፍተኛ ችግሮች አጋጥመውታል፡፡ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተቋቁሞ በግንቦት 97 ዓ.ም. ምርጫ አመርቂ ውጤት ያስመዘገበው፣ ከጥምረት ወደ ውህደት ለመሸጋገር የበቃውና ዛሬም ድረስ በሀገሪቱ ፖለቲካ መድረክ ላይ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ እንደሆነ የዘለቀበት አብይ ምክንያት በፕሮግራሙ የገለፀውና በተፈፃሚነቱም አመራሩ ቃል የገባለት ዓላማው የሕዝብን ተቀባይነትና ድጋፍ በመግኘቱ ነው፡፡
ቅንጅት ዓላማውን ተፈፃሚ ለማድረግ በሚያከናውነው ትግል ከሚመራባቸው መርሆች መካከል ሕጋዊነት፣ ዴሞክራሲያዊ የጋራ አመራር፣ የአሰራር ግልጽነትና መልካም ሥነ-ምግባር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ መርሆች በአገር ደረጃም ሆነ በፓርቲው ውስጥም ተግባራዊ እንዲሆኑ ቅንጅት በጽኑ ይታገላል፡፡
ፓርቲው የተነሳለትንና ሕዝብ መስዋዕትነት የከፈለለትን ቅዱስ ዓላማ ከግብ ለማድረስ፣ ለሕዝብ የገባውንም ቃል ተግባራዊ ለማድረግ በቅድሚያ የፓርቲው ሕልውና መረጋገጥ በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የላዕላይ ም/ቤቱ ተሟልቶና ተጠናክሮ መጀመርና በፓርቲው ውስጥ ለሚታዩ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እልባት መስጠት አቢይ ተግባር ይሆናል፡፡
ስለሆነም ነው የቅንጅት ሥራ አሰፈፃሚ ኮሚቴ ለሦስት ጊዜ የላዕላይ ም/ቤት ስብሰባ ጠርቶ በሦስተኛው በተገኙ አባላት አሳሪ ውሣኔ እንደሚተላለፍ ያስታወቀው፡፡፡ በዚህም መሠረት ታህሣሥ 20 ቀን 2000 ዓ.ም. በተካሄደው የላዕላይ ም/ቤት ስብሰባ፡-
1. የተጓደሉ የላዕላይ ም/ቤት አባላትን ስለሟሟላቱ፣
2. የፓርቲውን ሕጋዊነት ስለማረጋገጥና
3. ሊቀ መንበሩ ስለወሰዷቸው ሕገ-ወጥ እርምጃዎች
በሚሉ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ምክር ቤቱ በስፋት መክሮ የጋራ ግንዛቤ ይዟል፣ ውሣኔዎችንም አስተላልፏል፡፡
ም/ቤቱ የተገነዘባቸው ጭብጦች
1. ፓርቲው ሥራውን በአግባቡ መቀጠል እንዲችል የላዕላይ ም/ቤቱ ቁጥር ማሟላት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን፣
2. በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 9.2.3 መሠት የተጓደሉ የላዕላይ ም/ቤት አባላት የማሟላት ኃላፊነት ሥራ አስፈፃሚው በውክልና የተሰጠው መሆኑን፣
3. ከቅንጅት ለቀው የሌላ ፓርቲ አባላት በሆኑ፣ ከፓርቲው ጋር ላለመቀጠል መወሰናቸውን በተለያየ መንገድ በገለጹና በጤና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ከሀገር ከወጡ ቢያንስ ስድስት ወራት በሆናቸውና መኖሪያቸውን በዚያው ባደረጉት የላዕላይ ም/ቤት አባላት ምትክ ማሟላት አስፈላጊ መሆኑን፣
4. የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን፣
5. ሊቀ መንበሩ አምስት የላዕላይ ም/ቤት አባላትን ማገዳቸውና እንዲሁም ተተኪዬ ሆኖ እንዲሠራ በሚል ሰው የመደቡ መሆናቸውን መግለፃቸው የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ የጣሰና መሠረታዊ የሆኑትን የዴሞክራሲያዊ አሰራር መርሆችን ያላገናዘበ መሆኑን፣
6. የሊቀ መንበሩን አካሄድ እየተከተሉ በሀገር ውስጥ በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ቅንጅትን ለማዳን በሚል ሽፋን የሚያከናውኑት ተግባር የግል ፍላጎትን ለማሳካት የሚከናወን ከቅንጅቱ መሠረታዊ ዓላማ ጭራሹኑ ባፈነገጠ መሆኑን ተገንዝቧል፡፡
የተላለፉ ውሣኔዎች
1.1 በተጓደሉ የላዕላይ ም/ቤት አባላት ምትክ ስለማሟላት፡-
ፓርቲው የገጠመውን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ተቋቁሞና አስተማማኝ መፍትሔ ሰጥቶ የተነሳለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚያስችለውን ተግባር ለማከናወን ላዕላይ ም/ቤቱ በአጭር ጊዜ ቁጥሩ ተሟልቶና ተጠናክሮ ሥራ መጀመር ስላለበት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 9.2.3 በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የማሟላቱን ሥራ አከናውኖ በአስቸኳይ ለላዕላይ ም/ቤቱ እንዲያሳውቅ፣
1.2 የፓርቲውን ሕጋዊነት ስለማረጋገጥ፡-
ቀደም ሲል ይህንን ተግባር እንዲያከናውን የተቋቋመው ኮሚቴ ያከናወናቸውን ተግባራት በመገምገምና እንደ ግብአት በመጠቀም የፓርቲውን ሕጋዊነት በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን በማጥናት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለላዕላይ ም/ቤቱ እንዲያቀርብ፣
1.3 አቶ ኃይሉ ሻውል የወሰዷቸውን እርምጃዎች በተመለከተ፡-
ሀ/ የፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ በክፍል ሦስት አንቀጽ 24 በስምንት ንዑሳን አንቀፆች ውስጥ እንኳንስ የሥራ አስፈፃሚንና የላዕላይ ም/ቤት አባለትን ቀርቶ ማንኛውንም አባል የማገድ ሥልጣን የሚሰጥ ቦታ የለም፡፡
ለ/ እንዲሁም የግል ተወካይ የመሾምም ሆነ የመመደብ ሥልጣን ለሊቀ መንበሩ የሚሰጥ አንቀጽ የለም፡፡ ዴሞክራሲያዊ አሰራርን በሚከተል ፓርቲ ውስጥ እንዲህ ዓይነት አሰራር ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፡፡
ሐ/ የፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 1 ሊቀ መንበሩን ተክቶ የመሥራት ኃላፊነት የተ/ም/ሊቀ መንበር መሆን በግልጽ ይደነግጋል፡፡
መ/ በፓርቱው ሊቀ መንበር፣ ተ/ም/ሊቀ መንበር፣ ም/ሊቀ መንበር፣ ዋና ፀሐፊና ሌሎች የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ላይ እርምጃ መውሰድ የሚችለው ላዕላይ ም/ቤት መሆኑን የሚደነግገው የመተዳደሪያ ደንባችን አንቀጽ 9.3.18 ይህ ሊሆን የሚችለው በ2/ኛ ድምጽ መሆኑን አስፍሯል፡፡
ስለሆነም ሊቀ መንበሩ የወሰዱት እርምጃ ፍጹም ሕገ-ወጥ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መርህ በቅንጅት ፖለቲካ ከሚሰጠው ሥፍራ አንፃር ደግሞ እንዲህ ዓይነት የሕግ ጥሰት ሲፈፀም በቸልታ ማለፍ በፍፁም የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ በመሆኑም ደን በሚፈቅደው መሠት ጉዳዩ በዝርዝር ታይቶ ውሣኔ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ ሊቀመንበሩ ሕገ ደንቡ ከሚፈቅድላቸው ውጭ በመንቀሳቀስ ቅንጅቱንና አጠቃላይ የፖለቲካ ትግሉን የሚጎዳና የድርጅቱን አባላትና ደጋፊዎች የሚያሳዝን ተግባር ከመፈፀም እንዲታቀቡ ም/ቤቱ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
2.4 በሊቀ መንበሩ ሕገ-ወጥ ድርጊት ላይ ተመርተው በሀገር ውስጥ በተመሣሣይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ጥቂት የላዕላይ ም/ቤት አባላትም በፓርቲው ሕጋዊ አሰራር ላይ እንቅፋት ከመሆን እንዲቆጠቡ ም/ቤቱ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
በመጨረሻም ቅንጅት በሕጋዊነት፣ በጋራ አመራር፣ በአሰራር ግልጽነትና በመልካም ሥነ-ምግባር መርሆች ላይ ተመስርቶ አሁን የገጠሙትን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች አልፎ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጣለበትን አደራ ለመወጣትና የገባውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ትግሉን በጽናት ይቀጥላል፡፡ ለዚህም ተግባሩ እውን መሆን ሕልናውናውን ማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ሁሉ ተግቶ ይሰራል፣ በሂደት የሚያጋጥሙትንም ችግሮች ለሕዝብ እያሳወቀ ጥረቱን የሚቀጥል መሆኑን እየገለፀ ሕዝቡ የተለመደ ድጋፉን እንዲሰጥ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የቅንጅት ለአንደነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ
የላዕላይ ም/ቤት
ታህሣሥ 23/2000 ዓ.ም.
አዲስ አበባ