በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ለሚሰሩ ሰራተኞች ከ37-38 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ይደረጋል ሲል የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ በታየው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ከተወሰኑት በስተቀር ሁሉንም ሕዝብ የጎዳ ነበር፡፡ በተለይ አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል፡፡ በተለያየ መንገድ የኑሮ ውድነቱ የሚቀንስበትን መንገድ መንግሥት እንዲያስተካክል ጥረት ቢደረግም “ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ምክንያት እድገት ነው” እየተባለ ያለምንም መፍትሄ ሕዝቡ አሁንም በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ይገኛል፡፡
በዛሬው ዕለት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ ለጋዜጠኞች እንደገለፁት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ለመንግሥት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ለሚደረገው የደሞዝ ጭማሪም ለ2000 ዓ.ም 1.8 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፣ ከዚህ ውስጥ 1.3 ቢሊዮን ብር ለክልሎች የተመደበ ሲሆን 500 ሚሊዮን ብር ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የመንግሥት ሰራተኞች መመደቡን ነው፡፡
እንደሚኒስትሩ ገለፃም ለአንድ የመንግሥት ሰራተኛ ደሞዝ ተከፋይ ከ37-38 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ይደረጋል፡፡ ይህም ከመስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው፡፡
የኑሮ ውድነቱ ሳይባባስ በፊት የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግ ግፊት ሲደረግ የነበረ ቢሆንም መለስ ዜናዊ “የደሞዝ ጭማሪ መፍትሄ አይሆንም” ሲሉ ጠንካራ አቋሟቸውን ሲገልፁ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለኑሮ ውድነቱም አሳማኝ ያልሆኑ ምክንያቶችን ሲደረድሩ ቆይተዋል፡፡
አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት አሁንም ቢሆን በተደረገው የደሞዝ ጭማሪ የኑሮ ውድነቱ ሊረጋጋ እንደማይችል ነው፡፡ የዋጋ ንረቱና የተጨመረው ደሞዝ በፍፁም አይመጣጠንም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከመንግሥት ሰራተኛው ውጭ ኑሮውን ለመደጎም ሌላ አማራጮችን እየተጠቀመ ደፋ ቀና የሚል በርካታ ህዝብ በመኖሩ ነው ይላሉ፡፡
መንግሥት ከምርጫው ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባን ሕዝብ ለመበቀል በመፈለጉ ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ዘዴ ዋጋ እንዲንር ተደርጓል፡፡ ከዛም ለሕዝቡ የተጨነቀ በሚመስል ስሜት መፍትሄ ያልሆነ ግን መፍትሄ የሚመስል ነገር ይዞ እዛም እዛም ይላል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ፡፡ ወደዚህም ተባለ ወደዚያ ዋናውና ትልቁ ነገር መካከለኛና አነስተኛ ገቢ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮው ከብዶታል እጅግም ተወዶበታል፡፡ በዚህ አቅጣጫ ከቀጠለም ደሐ፣ መካከለኛና ሐብታም ተብሎ በሶስት የተከፈለውን አኗኗር የኑሮ ውድነቱ በሁለት እንደሚከፍለው ነው፡፡ ሐብታምና ደሐ በሚል፣ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው ይጠፋል ይላሉ ኢኮኖሚስቶቹ፡፡ የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ ለህዝቡ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚችልና እንደማይችል የመመልከቻው ግዜ ሩቅ እንደማይሆንም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል፡፡