ለኢትዮጵያውያን ዕስራ ዓመት (ሚሌኒየም) በአል አልአሙዲ ቦሌ ባስገነባው ማስጨፈሪያ ላይ መጥታ ትዘፍናለች ተብሎ ሲነገርላት የነበረችው ቢዮንሴ እንደማትገኝ ታወቀ፡፡ በምትኩ “ብላክ አይድፒስ” የተባሉ አቀንቃኞች እንደሚመጡም ተነግሯል፡፡
ከቦሌ መንገድ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ሲገባ በስተ ግራ በኩል ባለው የተንጣለለ መሬት ላይ ከስድስት ወራት በፊት ኤም ኤ የተባለ የማስታወቂያ ድርጅት ለሚሌኒየሙ የስደስት ወር ፌስቲቫል ለማዘጋጀት አካባቢውን የማስተካከል ስራ ጀመረ፡፡ “እኔ እያለሁ” ያሉት አቶ አብነት ገ/መስቀልና ሼክ መሐመድ አልአሙዲን እሱን አስነስተው ብዙ ብር ሊያመጣ የሚችል አዳራሽና መድረክ ማሰራት ጀመሩ በዋዜማውም ታዋቂ የውጭ አቀንቃኞች ይመጣሉ ተብሎ መወራት ጀመረ አንዷም ቢዮንሴ ነበረች፡፡
ሰሞኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እንደገለጹትም በዋዜማው ለሚደረገው ለዚህ ዝግጀትም ቢዮንሴ እንደማትገኝና በምትኩ “ብላክ አይድ ፒስ” የተባሉ አቀንቃኞች እንደሚገኙና ኢትዮጵያውያን ዘፋኞች እንደሚጋበዙ ተገልጿል፡፡
ለዚህ ዝግጅት መግቢያ የተመደበውም ለአንድ ሰው 1600,00 የኢትዮጵያ ብር ነው፡፡ በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ስታዲየም ዝግጅት ለማዘጋጀት ገንዘብ ከፍሎ የነበረ አንድ ድርጅት ስታዲየሙ “ሕብር” የተባለ ዝግጅት ይዘጋጅበታል ተብሎ እንደተከለከለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ መስቀል አደባባይ ላይ “ቴስት ኦፍ አዲስ” በግለሰቦች ሊዘጋጅ የነበረው ዝግጅትም መሰረዙ የሚታወስ ነው፡፡