በምርጫ 97 ቢሮው የቅንጅት ሆኖ ነበር፡፡ በምርጫ 97 ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ለመጨረሻ ጊዜ ፓርላማ እንግባ/ አንግባ የሚለውን ውይይት ያደረገበትና መግለጫ የሰጠበት ቢሮ በዛሬው እለት ከኢዴአፓ – መድኅን ቀምቶ ለኪራይ ቤቶች ተሰጠ፡፡
በምርጫ 97 ቅንጅቱ በተለምዶ ቴሌ መድኃኒያለም እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ቢሮ ይኑረው እንጂ ላንቻ ይገኝ በነበረው የኢዴአፓ – መድኅን ቢሮ ስብሰባዎችን ያካሄድበትና አንዳንድ የቢሮ ስራዎችን ይጠቀምበት ነበር፡፡ በቢሮው አጥር ላይም በትልቁ “ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ በሚል” በሰማያዊ ጨርቅ ላይ ተፅፎ ተለጥፎበትም ነበር፡፡ ከ20 ወራት ቆይታ በኋላ ከእስር የተፈቱት ዶ/ር ኃይሉ አርአያም ጥቅምት 22 እጃቸው ሲያዝ በዚህ ቢሮ ውስጥ በስራ ላይ እያሉ ነበር፡፡ በመጨረሻ እነ ልደቱ ቢሮውን የራሳቸው አድርገው ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን ኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት “ኪራይ ክፈሉኝ” በሚል ክስ መስርቶ የነበረ በመሆኑ በዛሬው እለት ፍርድ ቤቱ ባዘዘው መሰረት የቢሮው በር ተሰብሮ እቃው ከተቆጠረ በኋላ ውስጥ ያሉ ሰራተኞች እንዲወጡ ተደርጎና ቢሮው ታሽጎ ኪራይ ቤቶች ቤቱን ተረከበ፡፡
ቢሮው በ1984 ዓ.ም በእነ ክፍሌ ጥግነህ ይመራ ለነበረው ኢዲአቅ ለተባለው ፓርቲ ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን ፓርቲው ከኢዴአፓ – መድኅን ጋር ሲዋሃድ በጋራ መጠቀም ጀመሩ፡፡ በኋላም በዶ/ር በየነ የሚመራው አማራጭ ሃይሎ እዛ ገብቶ በጋራ ሲጠቀሙበት የነበረ ሲሆን የኢዴአፓ- መድኀን አመራር የነበሩት እነ ዶ/ር አድማሱ፣ ዶ/ር ኃይሉ አርአያና እነ ልደቱን ጨምሮ በንብረትነት ሲገለገሉበት ቆይተው በመጨረሻ ቅንጅቱ ሲጠቀምበት ቆየ፡፡
ሁሉንም እያባረሩ የራሳቸው ማድረግ የጀመሩት ልደቱና ጓደኞቹ ከጥቅምት ወር 1998 ዓ.ም በኋላ የራሳቸው አድርገው ሲጠቀሙበት ቢቆዩም ኪራይ ቤቶች ድርጅት “ቤቱ የኔ በመሆኑ ማንም ኪራይ ሳይከፍል ሊጠቀምበት አይገባም” በሚል በፍርድ ቤት በጀመረው ክስ ይረታል፡፡ ኪራይ ይከፈለኝ አሊያም ቤቴ ይለቀቅልኝ ሲል ይከራከራል፡፡ እነ ልደቱ ጠበቃ ቀጥረው እንደ ፓርቲ ድርጅትነታችን ቢሮ ሊኖረን እንደሚገባ እየታወቀ ኪራይ ክፈሉም ልቀቁም ልንባል አይገባም ብለው ይግባኝ ይጠይቃሉ፡፡ በይግባኙም ይረቱና ሰበር ይሄዳሉ፡፡ ሰበር ፍርድ ቤት በነሱ ላይ ወስኖ ቤቱን እንዲለቁ ያዛል፡፡ ከ20 ቀናት በፊት እቃቸውን አውጥተው ቤቱን ለኪራይ ቤቶች እንዲያስረክቡ ቢታዘዙም አቶ ልደቱ በየመንግሥት መ/ቤቶች ቢሮ በመራሯጥ ቤቱን ስለማስረከብ ጥረት ሲያደርግ እንደነበርና ማንም መቶ ሊቀማን አይችልም በሚል ልበ ሙሉነት አንዱን ክፍል ቢሮ ከፍተው ሲሰሩ እንደነበር ምንጮቻችን ጠቁመውናል፡፡
ከፍርድ ቤት፣ ከፖሊስ እና ከኪራይ ቤቶች ቤቱን ሊረከቡ ሰራተኞች ሲሄዱ ከአንድ ቢሮ በስተቀር ሁሉም ቁልፍ ሲሆንባቸው በቢሮው የነበሩትን የኢዴአፓ ሰራተኞች እንዲያስረክቧቸው ይጠይቃሉ፣ ፍቃደኛ የሚሆን ባለማግኘታቸው በሩን እየሰበሩ እቃውን ቆጥረው ኪራይ ቤቶች እንዲረከብ ከተደረገ በኋላ “ታሽጓል” የሚል ተለጥፎበት ኢዴአፓ ቢሮውን ለቆ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡