The following is a testimonial letter from Amare Mammo — a former cadre of the ruling TPLF/EPRDF regime — who used to work for the Ethiopian Agricultural and Food Organization.
Letter addressed to: Dr. Seid Hassan – Murray State University
Received: November 23, 2009.
ከውጭ በርዳታ የሚገኘው በሙስና የተዘፈቀው ድጎማ (Safety Net) በኢትዮጵያ ምን ይምስላል?
ጤና ይስጥልኝ ዶ/ር ስይድ።
ኢትዮጵያን እያሽመደመደ የሚገኘውን ሙስና በሚመለከት ትኩረት ሰጥተው በመያዘዎ አመሰግናለሁ። በድጎማ መልክ ለገበሬው የሚሰጠውን ገንዘብ በሚመለከት ግንዛቤ እንዲኖረዎትና፤ መረጃ እንዲሆንዎት የግሌን ለማበርከት/ለመወጣት ይህችን ደብድዳቤ ጽፌአለሁ። ስለ እኔ ትንሽ ለማለት ያህል፤ ወደ አሜርካ ከመጣሁ ይኸውና ሁለተኛ አመቴ ነው። በግብርና እና የምግብ ድርጅት የገበሬዎች የእርሻ አማከሪ ሆኘ በተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ ወረዳዎች ሠርቻለሁ።
ከላይ በተገለፀው አርዕስት ያለውን ሁኔታ ከመግለፄ በፊት፤ ከ1997 ዓ/ም ምርጫ በኋል፤ የገጠሩ ሕዝብ ኢሕአደግን የመረጠው ለማስመስልና ከተሜውን ለማሸበር ይነገሩ በነበሩት ግጥሞች መካክል ልጀምር፤
መራቡን ይራበው – የከተማ ሕዝብ፤
የዋህ ገጠሬ ሕዝብ – ይብላ ይደልብ።
ንብ ትነድፋለች አለ – የከተማ ሰው?
በልቶ ይመርቃል – ድሀ ገበሬው።
እንደሚታወቀው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ገበሬ በርሀብ ተጠቅቶ እንዳይሞት ከውጭ አገር በሚደርግ ድጎማ ሳያሰልስ “እየተረዳ” ነው። ይህ ድጎማ በእንግሊዝኛው ሴፍቲ ኔት (Safety Net) የሚባለው ተቋም ነው። ፕሮጀክቱ በአብዛኛው የሚመራውም በመንግሥት ካድሬዎች ሲሆን የድርጅታዊ አወቃቀሩና አከፋፈሉም እንደዚህ ነው።
ሀ) ሴፍቲ ኔት (Safety Net) ከ7 ተኩል እስከ 14 ሚሊዮን የሚሆነውን የገጠር ሕዝብን ያቀፈ ፕሮግራም (ተቋም) ነው። ፕሮግራሙ ከ1997 እስከ 2002 ዓ/ም ለአምስት ዓመት የሚቆይ ነው። [ለአንባቢያን ማሳወቂያ፡ – የዚህ ድጎማ ለጋሾች በአብዛኛው የዓለም ባንክና የአሜሪካ መንግሥት ሲሆኑ፤ በቅርቡ የዓለም ባንክ ያደርግ የነበረውን ድጎማ አሁን እንደገና አዲሷል። በድጎማው 292 ወረዳዎች እነደሚረዱም ገልጿል።] ድጎማው የሚያተኩርባቸው አካባቢዎች ድርቅ ያጠቃቸው ቢሆኑም በየክፍለ ግዛቱ ለሚጋኙት ሁሉ ነው። ለዚህ ድጎማ ተጠቃሚ የሚሆነውን አርሶ አደር የመመልመያ መለኪያዎች እነዚህ ናቸው፤
1. ብዙ ልጅች ያለው ቤተሰብ፤
2. ኑሮው ዝቅተኛ የሆነ -ድህነት ያጠቃው – ለምሳሌ ክብቶችና የቤት እንስሳት የሌለው፤
3. ቤቱ የተቃጠለበት፤
4. አባት ወይም እናት የሌላቸው ልጆች፤
5. በእድሜ የገፉ አዣውንቶች፤
6. አካለ-ስንኩላን የሆኑና መሥራት የማይችሉ።
ለ) በድጎማው ተጠቃሚ ከሚሆነው አርሶ አደር የሚጠበቅበት ሥራ፤ አንድ የድጎማ (ሴፍቲ ኔት) ተጠቃሚ አርሶ አደር በወር ስድስት (6) ቀን ፤ በቀን 8 ሰዓት በራሱ ስም መሥራት አለበት። ባለቤቱም እንደዚሁ 6 ቀናት በቀን 8 ሰዓት መሥራት አለባት። እሷ መሥራት ካልቻለች፤ ባሏ በወር 12 ቀናት መሥራት አለበት።
ሐ) የሥራው ዓይነት፤ አብዛኛው ሰው የሚሠራው ለመኪና መሄጃ የሚሆን የመንገድ ሥራ ነው። የሚሠራ መንገድ ከሌለ የድርጅት ጽሕፈት ቤትን መሥራት፤ ይህ ካልሆነ ለአርሶ አደሩ መሰብሰቢያ የሚሆን የፖለቲካ ድርጅት ጽ/ቤትን በመሥራት በተለይም የዉሃ ማቆር ጉድጓድን በመቆፈር ይከናወናል።
መ) የአከፋፈል ዘዴ- ፓኬጅ ይባላል። በሰው (ነፍስወከፍ) 30 ብር፤ ለምሳሌ አንድ አባዎራ 5 ቤተሰብ ካለው 150 ብር በወር ይከፈለዋል። ክፍያው ለአንድ ዙር ለ6 ወራት ይቆያል።
ሌላው ደግሞ፤ የመጀመሪያው ፓኬጅ ተብሎ የሚጠራው 1,600 ብር ለአንድ አርሶ አደር በሁልት ዓመት የሚመለስ ተብሎ በብድር የሚሰጠው ነው። ነገር ግን ይህንን ብድር የሚያገኙት ገበሬዎች ሁሉም ሳይሆኑ ለሌላው አርዓያ ይሆናሉ ተብለው የተመረጡት ናቸው። የዚህ ብድር ተጠቃሚዎች አብዛኞቹ እርዳታው የማያስፈልጋቸው ከሌላው ገበሬ ጋር ሲወዳደሩ “ሀብታም” ናቸው ሊባሉ የሚበቁ ናቸው። በሁለተኛው ፓኬጅ 4,000 (አራት ሽህ) ብር ይሰጣል — ከላይ እንደተጠቀሰው በብድር ነክ ሆኖ አርዓያ ይሆናሉ ተብለው ለተመረጡት ነው የሚሰጠው።
ለዚህ ገንዝብ አከፋፈል እንደ መመሪያ ሆኖ የሚያገለግል ተጠርዞ የሚታደል “መጽሀፍም” አለ። እንግዲህ ከላይ እንደተገለጸው፤ ለአንድ ሰው የሚሰጠው ክፍያ በቤተሰብ ልክ ስለሆነ፤ አንድ አባወራ በፕሮጀክቱ የሚሰጠውን ብር ለማበርከት በርከት ያሉ ልጆችን እንዲያፈራ ይጋብዘዋል ማለት ነው። ልጅ የሌለውም አንዳንድ ጊዜ ብሩን ለማግኘት ሲል ከጎርቤት ልጅ ይዋሳል/ያሳድጋል። እርዳታው የሚሰጠው “ከብት ለሌለው” ነው ስለሚልም፤ አንዳንድ ገበሬዎች እርዳታውን ለማግኘት ከብቶቻቸውን ይሸጣሉ። ቤቶቻቸውን አቃጥለውም ተጠቃሚ የሆኑም አልጠፉ።
ለሚሠራው የመንገድ፤ የዉሀ ማቆር፤ የፓርቲና የገበሬ ጽ/ቤት ሥራ አስተባባሪዎቹና አዛዦቹ ካድሬዎች ናቸው። እነዚህም ካድሬዎች በተለይ የግብርናን ሥራ አስመልክቶ ችሎታ የሌላቸው ስለሆኑ፤ ይጥቀምም ይጉዳ እነሱ ከመሰላቸው ገበሬውን በማዘዝ ማስቆፈር ነው። ገንዘቡ የግድ ለገበሬው እየተሰጠ ነው መባል ስላለበትም ገበሬዎች መቆፈር አለባቸው። በሀላፊነት የተሾሙት ከሚያስቆፍሩትም አንዱ የውሀ ማቆር (ጉድጓድ) ስለሆነ የሚቆፈሩት ጉድጓዶች እንዳው ይብዙ እንጂ ዉሀ የማይቆጥሩ ናቸው። እንዳውም “መሠራት አለበት” ተብሎ የሚቆፈሩት የውሃ ማቆሪያዎች ከመብዛታቸውም በላይ ስለማይታጠሩ ባልታጠሩት ጉድጓዶች ውስጥ ከብቶች እየገቡ በመሠበራቸውና በመሞታቸው የተነሳ ገብሬዎቹ በጣም ይማረራሉ። ገበሬውችም “ጉዷዶቹ ይደፈኑልን” ብለው ለካድሬዎቹ ጥያቄዎች ሲያቀርቡ በአብነት እኔ እመሰክራለሁ።
ለውሀ ማቆር መገንቢያ ተብሎ አንድ ጊዜ እኔ በነበርኩበት ቦታ በ8 የአይሱዙ (Isuzu) መኪናዎች 250 ኩንታል ሲሚንቶ ተልኮ ነበር። ሲሚንቶውን ፈርሞ የተረከበውም እንደኔ የግብርና ባለሙያ የተባለው እኔ የማውቀው ግለሰብ ነበር። ነገር ግን ተከምሮ የነበረው አብዛኛው ሲሚንቶ የካብኔ አባላት ቤቶችን ማደሻና ማስጨረሻ ነው የሆነው። [ካብኔ ማለት በኢሕአደግ (በየወረዳው) የሚሾም ሥራ አስፈጻሚ ሰው ነው።] አብዛኛውን ሲሚንቶ የግብርና ባለሙያው ለካድሬዎቹ (ለካብኔ አባላቱ) በርካሽ ሸጠላቸው። የቀረው ለሙከራ ተብሎ ወደ የውሀ ማቆር ቦታ ተወስዶ ተከምሮ ለብዙ ጊዜ ስለቆየ ደርቆ ተበላሸ። በአጠቃላይ ሲታይ፤ በሀላፊነት ሲሚንቶውን የተረከበውም ሆነ የካብኔ አባላት ተጠቃሚ ስልሆኑ “ለጥፋቱ ተጠያቂ ማነው?” ብሎ የሚጠይቅ ማንም የለም ማለት ነው።
ከላይ እንደገለጽኩት አንዱና ዋናው ሥራ በየቀበሌው የሚገነባው የፖለቲካ ጽሕፈት ቤት ነው። ገበሬውን በነዚህ መሰብሰቢያ ቤቶች እያጎርን እንጨቀጭቀዋለን። እኛ ወደ ገጠር የተላክነው ዋናው ሥራችን ይህ ነው። እንዳውም አንድ ጊዜ አንዱ ፀሀፊያችን ይህንን አስመለክቶ በቀልድ አስመስሎ እውነቱን ለመናገር ሲነግረን “ኢትዮጵያ ሥብሰባ ማድረግን ስለምትችልበት ይህን ችሎታችንን አሽገን (“ስብሰባን ፓክ” አድርገን) ለውጭ ገበያ ብናቀርብ ብዙ ትርፋማ እንሆናለን እና ይታሰብበት” ብሎ ተናገረና በጣም አሳቀን።
በሴፍቲ ኔት ተጠቃሚ የሆኑትም የኢሕአደግ አባላት እንዲሆኑ በምርጫም ጊዜ ለዚሁ ፓርቲ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ (እንዲመርጡ) ይጠየቃሉ፤ ይነገራቸዋል፤ ማስጠንቀቂያም ይሰጣቸዋል። ባይጠየቁም እራሱ ጥቅሙ ይገዛቸዋል ብየ አስባለሁ። ይህንንም በከፊል ተገንዝቤአለሁ። ድጎማውን አስመልክቶ ዋና ተጠቃሚና የከበሩ የካብኔ አባላት ለገበሬው ድጎማውን ሰጥተው እያባበሉም ገና የምርጫ ጊዜው ሳይደርስ እነሱንና የእነሱን ፓርቲ ተዎካዮች እንዲመርጥም ያዋክቡታል። እነሱን ከመምረጥ ሌላ ምርጫ የለውም፤ በቃ!
ሌላው መረሳት የሌለበት ደግም እንደኔ ላሉት ወደ ገጠር ለሚላኩት “ሙያተኞች” የሚሰጠው የቀን አበል (per dime) ነው። የዚህ አበል እኔም ተጠቃሚ ነበርኩ። ይህንን በሚመለከት እስቲ አንድ ጊዜ የሆነውን ላጫውተዎ። አንድ ጊዜ ለሥራ ወደ ገጠር ተላክን። የተላክነው ለሁለት ቀናት ብቻ ነበር። ነገር ግን ተጽፎ የወሰድነው አበል ለ10 ቀናት ሆኖ አገኘነው። ከ5 ቀናት በኋላም (የመጀመሪያውን ሳንጨርስ) ወደ ሌላ ቀበሌ ለተመሳሳይ ሥራ የ12 ቀናት አበል ተፃፈልን። እንደገናም ወደ ሌላ ቀበሌ ተልከን የ8 ቀን አበል ወሰድን። በአጠቃላይ ሣንሠራ ሠርታችኋል፤ ባልሄድንበት ቦታ ሄዳችኋል ተብለን የ30 ቀናት አበለ ወሰድን ማለት ነው። በጋምቤላ አካባቢ አንድ የካብኔ አባል በአንድ ዓመት ውስጥ የ458 የቀን አበል፤ ሁለተኛው ደግሞ የ378 የቀን አበል በመውሰዳቸው ሁለቱም ከሥራ እንደተባረሩ አውቃለሁ። እንደዚህ አይኑን ያፈጠጠ የሙስና ተግባር ላይ በግልጽ የተሠማሩትና የታወቀባቸው “ሙያተኞች” “ከሥራቸው ተባረዋል” ቢባልም ነገር ግን አብዛኞቹ ቅጣት ሳይሆን ወደ ሌላ ወረዳ እንዲዛወሩ ነው የሚደረገው።
ረ) ሌሎችንም ልጨምርልዎ፤
1. አንዳንድ ገበሬዎች ምርጥ የዘር በጎች፤ የወተት ላሞች፤ የመሳሰሉትን ተገዝተው ይሰጣቸዋል። እነዚህን የቤት እንሥሳዎች ገበሬው ፈርሞ ሲወስድ ከተገዙበት በላይ ተጨምሮበት ነው። አንዳንድ ጊዜ ገበሬው የተገዙበትን ዋጋ ቢያውቅም አፉን ሸብቦ ከመቀበል ሌላ አማራጭ የለውም። ካጉረመረመ ሊያገኛቸው የሚችላቸውን እንሰሳዎች ከናካቴው ማጣት ስለሚሆንበት።
2. ሌላው ደግሞ ለድጎማው (ሴፍቲ ኔት) ተብሎ የተመደበውንና የሚላከውን ገንዘብ አስከትሎ ለፕሮጀክቶች (የፕሮግራሞች መጠቀሚያ) ተብሎ የሚከፍለው/የሚፈሰው የገንዝብ መባከን ነው። ይህን ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ልጠቀማም፤ አንድ ጊዜ በርከት ያሉ ለገበሬዎች የሚሰጡ ምርጥ የዘር በጎች ተገዝተው ወደተፈለገበት ቦታ ጭኖ ለመውሰድ አንድ የግል የጭነት መኪና (Isuzu) ተከራየን። መክፈል የሚገባን የገበያ ዋጋ 1,800 (አንድ ሺህ ስምንት መቶ) ብር መሆን ሲገባው፤ ለነጋዴው 6,000 (ስድስት ሺህ) ብር ተሰጠው። ታዲያ ይህን ያህል ገንዘብ የተከፈለው የመኪና ነጋዴ በተዘዋዋሪ ለአለቆቻችን ያካፍል ይሆን፤ ወይስ ገንዘቡ የግል ስላልሆነ ነው እንደዚያ የሚረጨው? ድርጊቱ ሁለቱም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሁለቱም ጥፋት ነው። የመጀመሪያው ሙስናውና ከሱም ጋር ተያይዘው የሚመጡት የፖለቲካ፤ የኤኮኖሚና የባሕል የተወሳሰቡ አባዜዎች ሲሆኑ፤ ሁለተኛው ድርጊት በተናጠል ሲታይ ደግሞ ሀገሪቱን ወጥሮ ለያዛት ግሽበት ችግር አባባሽ ነው። ይህንን ጉድ በአርባ ምንጭ ዞን በኮምባ ወረዳ ከታዘብኩ በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ለተመሳሳይ ሥራ ተዘዋወርኩ። ቦታው ወደ አዋሳ ቀረብ ያለ፤ በሲዳማ ዞን ቦርቻ ወረዳ ይባላል። እዚህም ሆኘ እያየሁት ያለው ተመሳሳይ ጉድ ነው። በተጨማሪም፤ በዚህ አካባቢ አንድ ጊዜ የአህያና የፈረስ ጋሪዎች ከአዋሳ ከተማ ተሠርተውና ተገዝተው ለገበሬዎች እንዲሰጡ የሚያደርግና በተግባር ላይ የዋለ ፕሮጀክት ነበር። ነገር ግን ገበሬው እነዚህን ጋሪዎች ሲረከብ፤ ከተገዙበት ዋጋ ከ400 እስከ 500 ብር ድረስ ተጨምሮበት ነው። 500 ጋሪዎች ተገዝተው ሲታደሉ በዓይኔ አይቻለሁ። ይህንን ፕሮጀክት የቀረፀውም፤ በሥራ ላይ ያዋለውም ገንዘብ ያዡ ነው። ገበሬው ጋሪ ባያስፈልገውም፤ ወይም የጋሪው ብዛት ጥቅሙን ዋጋ-ቢስ ቢያደርገውም፤ የከብኔ አባላት ችግራቸው አይደለም። ለገበሬው ችግር አዋቂውች እነሱ ብቻ ስለሆኑ የገብሬው ሃሳብ ወይም ፍላጎት ከቁጥር አይገቡም። ቁም ነገሩ ግን በዚህ የጋሪ ማደል ፕሮጀክት ቢያንስ ወደ 200,000 (ሁለት መቶ ሽህ) ብር ለግል ጥቅም ስለሚሰበሰብ፤ በዚህ አንድ ፕሮጀክት ብቻ 16 የሚሆኑት ተባባሪ የካብኔ አባላት መካፈላቸው ነው። ከሥር ያሉት ደግሞ የሚካሄድውን ሙስና እንዳያጋልጡ ከ20 እስክ 30 የሚሆን የቀን አበል ይጻፍላቸውና አፋቸው ይሸበባል። በነገራችን ላይ እኔ የአንድ አምስት የካብኔ አባላት መኖሪያ ቤቶችን ጎብኝቸ ነበር። የቤቶቻቸው ውበት ምን ልበለዎ! አንዳንዶቹም እስከ አምስት ቤት ድረስ እንዳላቸውም ተገንዝቤአለሁ። ብዙና ትርፍ ቤቶች አላችሁ እንዳይባሉም ትርፍ ቤቶቻቸውን በልጆቻቸው ስም እንዲመዘገቡ ያደርጋሉ።
3. በሄድኩበት ወረዳ ሁሉ በግብርናው ጽ/ቤት ሆነው የሚሠሩት አብዛኞቹ (ሁሉም ማለት ይቻላል) የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት አስተማሪዎች ከሌሎቹ የሥራ ባለድረቦቻቸው ጋር ሲመጣጠኑም ብቃት ያነሳቸው፤ ይህንኑም ችሎታ/ብቃት ማነስ የተገነዘቡ፤ ነገር ግን በጋለ ምጣድ ላይ ሆኖ እንደሚቆላ ነገር ምላሳቸው የሚንጣጣ አፈኞች ናቸው። አንዳቸውም የግብርና ሙያ የላቸውም። እኔ እንደሚመስለኝ፤ አሁን ለተፈጠረው የእህል ዋጋ መናር እንደነዚህ ያሉት በደሎች ሁሉ ተጨማምረው ነው። ፖለቲካውም እንደዚህ አላግባብ በሆነ መልክ በከበሩ ጥቂት ነቀርሳዎች ተወጥሮ ነው የተያዘው።
4. የገጠሩን ጉዳይ በዚህ ላይ ላቁምና በከተማው፤ በተለይ በአዲስ አበባ እያጋጠመን ያለውን ችግር በጥቂቱ ላካፍለዎ። እኔ እኖርበት በነበረው አካባቢ በሳምንት እስከ 5 ቀናት ድረስ መብራት ይቋረጣል። እንዳው ችግሩን ዘርዝሮ መግለጽ ስለማይቻል፤ እስቲ አንዳንዱን ልበል። በርካታ የቤተሰብ አባላት ያሏቸው ሰዎች ሥጋ ገዝተው ቤተሰቦቻቸውን በአንድ ሙሉ ኪሎ ሥጋ መመገብ ስለማይችሉ አንዱን ኪሎ ሥጋ ለ3 ሲቃረጡ ይታያል። ሁለት ጊዜ በልቶ ማደር ብርቅ እየሆነብን ነው ብለው የነገሩኝ ብዙ ናቸው። አንድ ጊዜ ብቻ በልቶ የሚያድረውን የሕብረተሰብ ክፍል ፈጣሪ ይወቀው። የጤፍ እንጀራን በዓመት አንድ ጊዜ እንኳ ያልቀመሰ ሰው እየበረከተ መምጣቱንም ተግንዝቤአለሁ። ከጥቂት አመታት በፊት አንድ “ደረቅ እንጀራ ይሸጣል?” ተብሎ ይጠየቅ የነበረው አሁን ያ ቋንቋ ተለውጦ “ደረቅ ምሳ ይሸጣል?” በሚል ተቀይሯል። ወጥ ከተጨመረበት ከአቅም በላይ ሰለሚሆን! በአንፃሩ ግን፤ ቡና ቤት ገብተው ውስኪያቸውን የሚያንቆረቁሩ፤ ምግብ ቤት ገብተው ጮማቸውን የሚቆርጡም አሉ። እንደነዚህ ያሉትን ጥጋበኞች የትካሻ/ጫንቃ ማበጥ የተመለከተ ሰው፤ የተራቡትን 5 ሰዎች ሊሸከም ይችላል ብሎ ማሰብ ይችላል።
እንግዲህ ሕዝባችን እንደዚህ ባለ የርሀብ ቸነፈር እየተቆላ ነው “ጀግናው መሪያችን” ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ አይናቸውን ፍጥጥ እያደረጉ “ኢኮኖሚአችን በ 11.8% አድጓል” ብለው ሲናገሩ በሰሙትም ሆነ ባልሰሙት ጉዳይ ላይ ሁለት እጃቸውን በጣም ከፍ አድርገው አውጥተው (ማጨብጨባቸው እንዲታወቅላቸም ይሆናል) የፓርላማ አባላት ሲያጨበጭቡላቸው፤ አቶ መለስ መነጽራቸውን ከፊታቸው ወረድ-ቀና፤ በእጃቸው ከፍ-ዝቅ እያደረጉ በጋለ መልክ ሲናገሩ ይታያሉ። ይህ እየሆነ እያለ፤ በአንፃሩ ደግሞ በርሀብ የተቆላው ሕዝብ አንጀቱ እርር ይላል! በነገራችን ላይ የ97ቱን ምርጫ አስገድፎ የተመረጡት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም የጭብጨባው ውድድር ተካፋይ ስለሆኑ በጭብጨባው ያላቸው ፉክክርና ትብብር አሳፋሪ እንዳይሆን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ተብሎ በሰፊው ይነገራል። ማስጠንቀቂያውም፤ “ማጨብጨባችሁን ቀጥሉበት ነገር ግን እንደበፊቱ ሳይሆን ትንሽ የሚባለውንም እያዳመጣችሁ አድርጉት” ተብለዋል ነው የሚባለው።
እንግዲህ በአዲስ አበባ (እኔ እዚያ እንደነበርኩም ሆነ አሁን) በከተማው ሕዝብ የሚባለውን፤ ከእርሰዎ ሙያ ጋር የሚስማማውን ትንሽ ብየ ልጨረስ። ኢኮኖሚያቸውን በ11.8% ያሳደጉት የ”ጀግናው መሪያችን” መለስ ዘናዊ እውቅና በጣም እየናረና እየገነነ መጥቷል። በዚህም የተነሳ ተፈላጊነታቸው በዝቶ “ጀግናው መሪያችን” ግን የሚያናግሯቸውን ሰዎች ለመምረጥ ተገደዋል። የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ 11.8% ያሳደጉት፤ ይህንንም በድፍረትና በመደጋገም የተናገሩትን “ጀግና” ለማናገር ተሠልፈው ከየሚገኙት መካከልም፤ የሀገራቸው ኤኮኖሚ ያሽቆለቆለው፤ የምዕራብ አገሮች ታላላቅ መሪዎች — አቶ ኦባንም ጨምሮ እንዲሚገኝ እየተነገረ ነው ያለው። እነዚህም የታላላቅ አገሮች መሪዎች እንደዚህ የደቀቀውን ኤኮኖሚያቸውን ለማቅናት ደፋ-ቀና እያሉ ከሚኳትኑ፤ እልቁንስ በ12% የሀገሩን ኢኮኖሚ እያሳደገ ያለውን “ጀግናውን የኢትዮጵያ” መሪ ጥቂት ደቂቃዎች ባልሞላ ጊዜ አማከረው መፍትሄ ቢያገኙ አይሻላቸውም? ይባልና፤ እንዳውም አንዳንዶቹ፤ ታወቅን የሚሉ የኤኮኖሚ ጠበብቶችም፤ የኤኮኖሚ እድገት ትምህርታቸውን ከልሰው እውቀታቸውን ለማዳበር “ከጀግናውና ከታላቁ የኢኮኖሚ ምሁር” ከአቶ መለስ ለመውሰድ ቦታው ሳይሞላ ተራቸውን ቢይዙ/ቢመዘገቡ ይሻላቸዋል! ብለው በድፍረት የሚናገሩም አልጠፉ።
አዎ፤ ይገባኛል! “የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ቀመሩ ተዥሞልሙሎ የተሠራው በነ አቶ መለስ መኝታ ቤት ስለሆነ የእነዚህ የታላላቅ አገሮች መሪዎች ሕዝብ ይህንን ሲያውቅ እንደሚቆጣባቸው፤ ከሥልጣን አሽቀንጥሮም እንደሚጥላቸው የአዲስ አበባ ሕዝብ እንዴት ይህንን ማሰታዎስ አቃተው?” ብለው ይጠይቁኝ ይሆናል። ቁጣን ካነሱማ፤ ከኛስ ሕዝብ ምን ቀርቶ። በወያኔ ካድሬ እየተገረፈ፤ እየተቃጠለ ያለ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ አንድ ቀን መገንፈሉ ይቀራል ብለው አያስቡም? በአገራችን አነጋገር፤ “ቡና እንኳ እሳት ላይ ብዙ ከቆየ መገንፈሉ አይቀርም” ይባል የለ?! ፈጣሪ ይርዳን።
በሌላ ርዕስ በሌላ ጊዜ እስከምንገናኝ እስከዚያው ቸር ይገጠመን።
አማረ ማሞ።
* * * * * * * * *
አንባቢ ሆይ፤
ከሚደርሱኝ ደብዳቤዎች መካከል ይቺ የአቶ አማረ ማሞ ደብዳቤ በገጠሩ አንሠራፍቶ ያለውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ እውነታ ያንፀባረቀች ስለሆነች አቶ አማረ በፋክስ የላከልኝን በእጅ የተጻፈ የስምንት ገጽ ደብደቤ እንደገና በኮምፑተር ጽፌ (ታይፕ አድርጌ) ለማካፈል ወስንኩ። የዚህ ፀሀፊ ደብዳቤ ወደ ገጠሩ ወሰድ አድርጎን፤ እየሆነ ያለውን ለሌሎቻችን ከማቅረቡም በላይ ለምሳሌ “ድጎማ” ተብሎ የሚሠጠው “እርዳታ” ምን እንደሚመስልና የሚያደርሰውን የለማኝነትና የጥገኝነት ስሜት አባዜ፤ አሁን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እንደሚነግሩንም፤ “ድጎማው” የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑን፤ በገለማው ሙስና የከበሩና እየከበሩ ያሉ ግለስቦች እንዳሉ፤ በሕዝብ ሕይዎት የሚጫወት የአውሬነት/አረመኔነት ጠባይ ያለው የሕበረተሰብ ክፍል (ክላስ) እንደተፈጠረ፤ ለ”ድጎማ” ተብሎ የሚሰጠው ገንዘብ ለግሽበቱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ፤ ወ.ዘ.ተ. ያሳያል።
ምስጋና ለአቶ አማረ ማሞና ኢትዮጵያን ወጥሮ እያብጠለጠላት ስላለው ሙስና መረጃን ለምትልኩልኝ ሁሉ!
(I can be reached at [email protected] or [email protected])