ሥልጣነ-ክህነት የቂም መወጫ በትር አይደለም!
[click here for pdf]
ከምትኩ ይመር፣ ዋሽንግተን ዲሲ
ዘበነ (መምህር) መንገድህን ፈትን ራስህንም ጠይቅ፤ ሥጋ ከባድ ነው፣ ትእቢትም ያሳፍናል። በእምነትና በሥራ እንጅ በቲፎዞ ገነት አትወረስም፣ መጽሃፉም አላለም። በአንጋፋው የሜሪላንድ ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ በቅርቡ በተካሄደ የምእመናን አባላት ስብሰባ ላይ በማይመለከትህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባትና አባላት በግል ሃሳባቸውን እንዳይለዋወጡ እንቅፋት ለመፍጠር ያደረከውን ሙከራ በመቃወም የተከበሩ አዛውንት እማማ ውድነሽ “ይህ የምእመናን ጉባኤና ውይይት እንጅ የካህናት አይደለምና ጣልቃ ገብነትህን አቁም። አንተን አይመለከትህም፣ ዝም ልትል ይገባሃል። በስብሰባው ላይ ልትገኝም አይገባህም፣ በነፃነት እንወያይበት” ብለው ሃሳባቸውን ስላቀረቡ ብቻ “ሀጢአትና ሸክላ የሚገስጸውን ይጠላል” የሚባለው ደርሶብህ እኝህ እናት የጌታችንና የመድኃኒታችንን እየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ወደሙ ለመቀበል በቀረቡ ጊዜ በሆድህ ቂም ቋጥረህ አሸምቀህ ስትጠብቅ ቆይተህ በወፈግዝት እንዳይቀበሉ ለማድረግ ያደረከው ከንቱ መከራ በመክሸፉ ልኡል እግዚያብሔር ይመስገን እንላለን። ለመሆኑ ባለቤቱ እንኳን “ሀጢአት ያላደረገ ድንጋዩን ይወርውር ነበር ያለው። አንተ በዛ ዘመን ብትኖር ኖሮ ደፋር ነህና ካድራጎትህ ትወረውር ነበር ማለት ይቻላል።
ጌታችንን መድኃኒታችንን እየሱስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ሥጋዬን ካልበላችሁ ደሜንም ካልጠጣችሁ ህይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው። እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል፣ ደሜም መጠጥ ነውና ስጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ህያው አብ እንደላከኝ እኔም በእርሱ እኖራለሁ” (ዮሐንስ ም.6 ቁ. 53-57):: በዚህ ቃል እውነትነት ያመኑት ትምህርቱን ወስደው፣ ከራሳቸው ጋር ተነጋግረው በነጻነት ወስነው፣ ጾመው፣ ጸልየው፣ መጽውተው፣ ንስሐ ገብተው፣ ሕጉንና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንና አዋጁን ጠብቀው በምሳሌነት ከቆሙትና ከምናከብራቸው አባቶቻችንና እናቶቻችን መካከል አንዷ የሆኑትና እንደ መንፈሳዊ እናትነታቸው በሁሉም የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. የማይታጡት የተከበሩ እናታችን ላይ ውርደት ለማድርስ ሞክርህ የነበረው በልኡል እግዚያብሔር ከሽፎብሃል። እኝህ አዛውንት እናታችን በጸሎት የተጠመዱ፣ መፅሀፍትን የሚያውቁ፣ በዘመኑ ትምህርትም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ፣ ሁል ጊዜ የሚያነቡ፣ የሚጠይቁ፣ ለቤተክርስቲያናችን ቀናኢነትና ተቆርቋሪነት ያላቸው፣ እውነትን ያለፍራቻ የሚመሰክሩና በፈጣሪያቸው የሚመኩ ቅን እናት ላይ ከዓለም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናት ደንብና ሥርዓት ውጭ እንደውም ከዓለም የቤተክርስቲያን ታሪክና አስተምሮት ያልታየና ያልተደረገ የእግዚያብሔር ሚስጢርን በማቃለል በግል ጥላቻና ቂም በመነሳት በወፈግዝት የተከበረውን የጌታችንን የመድኃኒታችንን እየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ለመቀበል እየተራመዱ እያሉ በአደባባይ አውግዧለሁ አይቀበሏትም ብለህ መደንፋትህ በርካታ የቤተርሲቲያኒቷ ምእመናን ላይ “ነግ በኔ” የሚል ከፍተኛ ጭንቀትና ሥጋት አሳድሯል። በእጅጉ Aሳዝኗል፣ አንገብግቧልም።
በመሠረቱ አዛውንቷ የአንተ ጥርስ ውስጥ የገቡት “ክህነት ማን ሰጠህ? መቼና የት? ብለው በመጠየቃቸውና መስቀልም ከአንተና ከመሰልህ ባለመሳለማቸውና ስላላመኑባችሁ በዲያቢሎሳዊ ስሜት ተነስተህ የግል ቂም በቀል መውጫ ለማድረግ እንዳይቀበሉ ለማድረግ ወፈግዝትህን በጭካኔ አወረድክባቸው። እንደተገነዘብነው ዘዴህ እኝህ ለሰማይ ለምድር የከበዱ አዛውንትን በማዋረድና በማዋከብ በአንተ ላይ ወቀሳና ተቃወሞ የሚያነሱብህን ሌሎች ምእመናን ላይ ጉልበትህን ለማሳየትና ለወደፊትም እንዳይነሱብህ ለመቀጣጫነትም እንደሆነ አይጠረጠርም። አንድ ነባር ምእመን እንዳሉት “ይህ ሰው የመለስ ዜናዊን ሥልጣን ቢያገኝ፣ ከእሱ በከፋ ሁኔታ የሰው ዘር አይተርፈውም ነበር ፣ ቂመኛና ጨካኝ ነው” ነበር ያሉት። ሁልጊዜ ይደልዎን፣ አድናቆትንና ምስጋናንና ብቻ አትጠብቅ። ስታጠፋ ለመገሰጽ፣ ስትሳሳት ለመታረም ዝግጁ መሆን አለብህ። “የሹም ዶሮ እሽ አትበሉኝ አለች” እንደሚባለው መሆን ተከባሎ አዘቅት ውስጥ መግባትን ያስከትላል።
ዘበነ ፣ልብ በል ሰባኪ ወይም መምህር ወደ ሰገነት የሚወጣው የእግዚያብሔርን ቃል ለመስበክ እንጅ ከግል ሁኔት በመነሳት ለውዳሴ ከንቱ ወይም ለእርግማንና ለወፈግዝት መሆን አይኖርበትም። በቀሪው ዘመናቸው እግዚያብሔርን እንዲያማርሩ አዛውንት ምእመናን ላይ ወጥመድ መሸመቅና ለማሸማቀቅ “ገዝቻለሁ” እያሉ በአውደ ምሕረቱ ማጓራት በጣም አስነዋሪ ድርጊት ነው። የንሥሐ አባታቸው አይደለህ፣ ብትሆንም እንኳዋ ለመቁረብ በገዛ ፈቃዳቸው የቀረቡትን ሰው “አይገባዎትም ተመለሱ” የማለት ሥልጣን ከየት አመጣህ? በተለይ በዚህ በምንኖርበት የሰው መብት በሚከበርበት Aገር ላይ ማን በማን ላይ ይጮሃል? በደንብ የሚያስቀጣ ሕግ አለው እኮ! ነገር ግን እርሳቸው በልጠውሃል በአካልና በመንፈስ ከመንገዳቸው ሳይለቁ “ይቅር ይበልህ” እያሉ የነፍስ መዳኛ ብቸኛው መድሃኒት የሆነውን የእየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደመ ተቀብለዋል። በእለቱ አገልግሎት ላይ የነበሩት ተረኛው ቀዳሽ ካህን ያንተን ተጽእኖ በመቋቋም ሳይታወኩ በማቀበልዎና ለእግዚያብሔር ህግ በመቆምዎ ኮራንብዎ! ለካስ ቤተክርስቲያናችን አሁንም ሰው አላት አልን። እውነተኛ አባት ህጉንና ሥርዓቱን ደንቡን ያውቃልና “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ“ እያሉ እየገሰጹ በተፈጠረው ሁኔታ ምእመናኑ እንዳይታወክ እየጸለዩ የቅዳሴ አገልግሎትዎን አጠናቀዋልና ምስጋና ከልብ ይድረስዎ። ትክክለኛ ካህንነትዎን በፈታኝ ጊዜ አስመስክረዋልና ኮራንብዎት! እግዚያብሔርም የቀደሙ አባቶቻችንን ፀጋና በርከት እንዲሁም እድሜና ጤና ሰጥቶ አገልግሎትዎን ይባርክ።
ዘበነ እኝህ በሃሰት የውግዘት አኮርባጅ የገረፋቸው አዛውንት እውነተኛ የክርስቲያን ተምሳሌት፣ አንጡራ የኦርቶዶክስ ሐብት ሲሆኑ አቧራ ጠርገው ላይ ታች ብለው ደክመው ዛሬ እግዚያብሔርን በቦታው እንድናመልክበት ቤተክርስቲያን ከሌሎች አባቶችና እናቶች ጋር ሰርተው ለአንተ (ለዘበነ) ኮሮጆ እንድትሞላበት ስላደረጉ፣ የሥራና የመተዳደሪያ መስክ ስለከፈቱልህ ውለታቸውን በማዋረድ ከፈልካቸው። “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” ማላት ይህ ነው። እኝህ እናት ቢሳሳቱ እንኳ ወደ ስጋ ወደሙ መቅረብ የህይወት መድሃኒት ነውና፣ ይፈውሳቸው ብለህ ልትጸልይላቸውና ልትመክራቸው በተገባህ ነበር። ለነገሩ አንተ ምን ታደርግ “ግርግር ለምን ያመቻል” እንዲሉ የቤተክርስቲያናችን በጠላቶችዋ እንድትከፋፈል መደረግ ለአንተና ለመሰሎችህ አመችቷልና። ግን እስከ መቼ? እራስህን መርምር። በኛ በምእመናን በራሳችን ገንዘብና ማእድ አትስደበን። ሸቀጥ ለተጠቃሚዎች ለመሸጥ እንደሚንገበገብ ማስታወቂያ ተናጋሪ የቃላት ወንጭፍ በጆሮአችን አትወርውር። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በትህትንና በአክብሮት ነው መልአኩን ገብርኤል “እንደ ቃልህ ይደረግልኝ” ያለቸው።በትህትና ነው ለተራበ ውሻ ጫማውን አውልቃ ውሃ ያጠጣችው። ሰባኪ እኮ ራሱ የእውነት መጀመሪያ መሆን ይገባዋል። የእምነትን ስብከት ከፕሮፓጋንዳ ለይ። አንተ የወንጌል ሰባኪ መምህር ነህ እንጅ ለስጋ ለገበያ የሚለፈልፍና የሚቀባጥር ካድሬ አይደለህም። ጌታችንን መድሃኒታችንን እየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን እውነቱንና ወንጌሉን ብቻ መስክር። “ሰው ሊያደርግባችሁ የማትወዱትን እናንተም በሰው ላይ አታድርጉ” የሚለውን የእግዚያብሔር ቃል ከማነብነብ ባሻገር አንተም በሥራ ላይ አውለው። ቃሉን ብቻ ስበክ። የምትሰብከውንም በስራ ላይ ማዋልህን አረጋግጥ። በአዛውንቷ ላይ የወረወርከው የወፈግዝት ፍላፃ አልፏል። ወዮ ለአንተ ግን በንስሐና በይቅርታ እስካልተመለስክ ድረስ በእድሜህ የፈተና ፍላጻ ይሆናል!
ስለምንተ ማርያም፣ ስለቸሩ እግዚያብሔር ብለው በመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት ችግሩን፣ ረሃቡንና ጥሙን ተቋቁመው በዓለም ወደር ካልተገኘለት የመንፈስ ቅዱስ የእውቀት ውቅያኖስ በሁሉም የእውቀት ዘርፎች እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱትን በተለይም ዘመናት ባስቆጠሩት በጎጃም፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በሸዋና በትግራይ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያናት ዋና ዋና የቅኔ፣ የትርጓሜ፣ የድጓና የዜማ ትምህርታቸውን አጠናቀው መንፈሳዊ ፒ.ኤች.ዲያቸውን ኩራት በሆነችው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያገኙትን እውነተኛ ካህናት አባቶቻችንን መሳድብ፣ ማቃለል፣ ማብጠልጠል፣ ማንጓጠጥና መዘርጠጥ የቤተክርስቲያን ጠላትነት ብቻ ሳይሆን የአገርና የሕዝህም ጭምር ነው። ስለሆነም ስተሃልና ልብህን ከስድብ መልስ። እነዚህ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በፍፁም አንተ ዘበነ እንዳዋረድካቸው “ሆዳሞች፣ልብስና ቆብ ብቻ፣ አባጨጓሬም ‘አባ’ ይባላል ወዘተ ተብለው መሳለቂያ የሚሆኑ አይደሉም። ለነገሩማ ማንም ቢሆን ያውም በቤተክርስቱያ ቅጽር ግቢ ውስጥ መስድብ፣ ማውረድና መሳለቂያ ማድረግ ክልክል ነው። ቃሉም እንደሚለው “ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል” ሉቃስ 6-45።
በአንድ ወቅት አንድ እንግሊዛዊ ጸሃፊ ስለ አባቶቻችን ካህናትና ሊቃውንት ጥልቅ የእውቀትና የጥበብ ማህደርነት ሲናገር“ በአውሮፓ አንድ ሰው፣ አንድ የትምህርት ዓይነት ያጠናል ወይንም የአንድ የትምህርት ዓይነት ባለቤት ነው። በኢትዮጵያ ግን አንድ ሰው የባለብዙ ዘርፎች ትምህርት ባለቤት ነው። በመሆኑም በአውሮፓ አንድ ሰው ቢሞት ያው የአንድ የሙያ ባለቤት ሞተ ነው የሚባለው። በኢትዮጵያ ግን Aንድ ሰው ቢሞት Aንድ ትልቅ ሙዚየም እንደተቃጠለ ይቆጠራል ብሎ ነበር። ታዲያ እነዚህ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተመሰከረላቸውን መንፈሳዊ ኢትዮጵያዊያን አባቶች መሳደብና መናቅ ምን ይባላል? አንተ ማነህና? ከየትኛውስ የቅኔ፣ የተርጓሜ፣ የድጓና የዜማ ትምህርት ቤት ነው የበቀልከው? ወይንስ ፌሬሰንበት ዘ….. ይሆን? እኛ ግን ጽድቅን ለማግኘትና መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ይህንን ከንቱ ዓለም ንቀውና ተጸይፈው፤ ጤዛ ለብሰው ዳዋ ተንተርሰው በጽድቅ መንገድ የሄዱት ሊቃውንቶቻችንና ካህናቶቻችንን አለኝታዎቻችንና መመኪያዎቻችን ናቸውና እባክህን ከእነሱ ላይ ውረድ።
እንደዚህ ዓይነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደርሱ ችግሮችና እንደ ዘበነ ያሉ አጥፊዎች በጊዜው ባለመታረማቸውና አጥፊዎችም ላይ አግባብነት ያላቸው የሥነሥርዓት እርምጃዎች ባለመወሰዳቸው እነሆ ዛሬ ቤተክርስቲያናችን ከፍተኛ አደጋ ላይ ትገናለች። አንዳንድ የቤተክርስቲያን አባቶችና መምህራን በምእመናቸው ላይ ተነሳስተው በአድማ፣ በጥላቻ፣ በቁጣ፣ ‘በስገዱልኝ’ የሚመሩን መሆን የለባቸውም ። እኛ ለዘበነ የምንለው ከዚህ ከገባህበት “ከሴኬም ጉዞ” ውጣ ሲያልቅ አያምር Aይሁንብህ፣ ከዚህ በፊት ስለቤተክርስቲያን የጮህከውን እስተዋጾ ገደል ከቶታልና በጸሎት እራስህን በመግዛት ወደነበርክበት የፀጋ ስብከት ተመለስ። አንደበትህን ከስድብ፣ ከሽርደዳ፣ ከአሽሙርና ከፌዝ አርቀህ ለቃለ እግዚያብሔር ብቻ አድርገው። በተለይ መምህራን በትእግሥት፣ በግብረገብነት፣ በሥነሥርዓት የሚያስተምሩ መሆን ይኖርባቸዋል። የኋላ የቤተክርስቲያናችን ታሪክ የእነ አቡነ ተክለ ሐይማኖትና የመሳሰሉት የእምነት ጽናት፣ መስዋእትነት፣ ግብረግብነትና ሥነምግባርን አስተምሮን አልፏል። ስድብ፣ ቁጣ፣ ቂም፣በቀልና ወፈግዝት ምእመናንን የሚመርዝና ቤተክርስቲያንን የሚያጠፋ ነውና በአስቸኳይ እርግፍ አድርገህ ተወው። እዚህ ላይ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት የደብረገነት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አለቃና መስራች የነበሩት ትጉህ ና ታታሪው አባታችን መልአከ ገነት ልሳነ ወርቅ ውቡ በህይወት እያሉ ዘበነ ትናንትና እዚህ መጥተህ በዲያቆንነት ቅዳሴ ላይ ስምህን ስታስነሳ አይከብድህም ወይ? አገራችንስ ውስጥ የቤተክርስቲያን አለቃ ካህን እያለ የዲያቆን ስም ቅዳሴ ላይ ተነስቶ ያውቃል ወይ? እኛ ሳናውቀው የቤተክርስቲያን ህግ ተለወጠ ወይንስ ሌላ ምክንያት አለ? በየትኛውም የዓለም ክፍል ያላችሁ እውነተኛ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ምን ትላላችሁ? የተከበሩ አባታችን ቀሲስ አስተርአየ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ? ሳይቃጠል በቅጠል ነውና መላ በሉ!