በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የሚፈፀመው ኢሰብአዊ ወንጀል

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

እ.ኤ.አ ሜይ 2/2014 ቢቢሲ/BBC እንደዘገበው በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ እንደመዥገር ተጣብቆ የሚገኘው ገዥ አካል የጸጥታ ኃይሎች ከመናገሻ ከተማዋ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በኩል በ80 ማይሎች ርቀት ላይ በምትገኘው የአምቦ ከተማ ላይ ቢያንስ 47 የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ ረሽነዋል፡፡ ስብዕናው በውሸት እና በሀሰት ውንጀላ የበከተው ገዥ አካል ይህንን እልቂት እንደተለመደው ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ “ጥቂት ጸረ ሰላም ኃይሎች በቆሰቆሱት እና በአስተባበሩት አመጽ“ ምክንያት የሚል የሀሰት ፍረጃ በመስጠት በግፍ የተገደሉትን ወገኖቻችንን ቁጥር ለማሳነስ ጥረት አድርጓል፡፡ ይህ በወጣት ተማሪዎች እና ህጻናት ላይ የተፈጸመው የማንአለብኝነት የእብደት አሰቃቂ እልቂት በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ዘንድ ሰፊ ሽፋን አልተሰጠውም፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች/HRW የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት “በአምቦ፣ በነቀምት፣ በጅማ እና በሌሎች ከተሞች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ባሰሙት ንጹሀን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ እና ድብደባ ይቁም“ የሚል መግለጫ በማውጣት እኩይ ድርጊቱን አውግዟል፡፡ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ “በኦሮሚያ የሚገኙ ከ15 በላይ የሚሆኑ ህብረተሰብ አቀፍ ገጠራማ እና ከተማ ቀመስ አካባቢዎችን ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የወሰን ክልል የሚያካትተው እና የኦሮሞ አርሶ አደሮችን እንዲሁም ሌሎች ኗሪዎችን የሚያፈናቅለው የአዲስ አበባ የተቀናጀ መሪ የልማት ዕቅድ ሀሳብ ተዘጋጅቶ ይፋ መሆኑን ተከትሎ የተማሪዎች የተቃውሞ አመጽ ገነፈለ“ ብሏል፡፡ በማስከተልም ሂዩማን ራይትስ ዎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ባሰሙት ተማሪዎች ላይ የገዥው አካል የጸጥታ ኃይሎች እየወሰዱ ያሉትን የኃይል እርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጠይቋል፡፡

በዚህ መረን በለቀቀ ዕኩይ ድርጊት የተሰማኝን ሀዘን በቃላት ለመግለጽ ተስኖኛል ምክንያቱም ልብን ሰብሮ የሚገባው ይህ የአሰቃቂ እልቂት ሀዘን ልሸከመው ከምችለው ከአቅሜ በላይ ሆኖብኛልና፡፡ የብሩህ አዕምሮ ባለቤት እና የነገይቱ ኢትዮጵያ ተረካቢ የሆኑት እምቦቀቅላ ተማሪዎች ገና በወጣትነት ለጋ እድሚያቸው ኃላፊነት በማይሰማው መንግስት ነኝ ባይ የወሮበላ ቡድን ስብስብ በጥይት ውርጅብኝ በመጨፍጨፋቸው ታላቅ ሀዘን ተሰምቶኛል፣ እንዲሁም ቀጣይነት ባለው መልኩ ስሜቴን እየቆጠቆጠኝ ይገኛል፡፡ ተማሪዎቹ የሚሰማቸውን ቅሬታ በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ ህገመንግስታዊ ያልተገደበ መብት ነበራቸው፡፡ ያንን መብት በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን በማሰማታቸው ምክንያት ብቻ የጥይት በረዶ ተርከፍክፎባቸዋል፡፡ እናም ሁላችንም ልናዝንላቸው ይገባል፡፡ ኃላፊነት በጎደለው ገዥ አካል በተፈጸመው እልቂት ምክንያት የምርጥ እና የባለብሩህ አእምሮ ባለቤት የነበሩትን ወጣቶች ኢትዮጵያ በማጣቷ አጅግ በጣም ለኢትዮጵያ አዝናለሁ፡፡ የእልቂቱ ሰለባ ለሆኑት ወጣቶች ወላጆች እና ጓደኞች የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ መጽናናትን እንዲሰጣቸውም ለኃያሉ አምላክ ጸሎቴን አደርሳለሁ፡፡

በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸምን እልቂት አጥብቄ አወግዛሉ፡፡ እ.ኤ.አ የሜይ 2005 የኢትዮጵያን ድህረ ምርጫ ውዝግብ ተከትሎ ምንም ትጥቅ ሳይኖራቸው በሰላማዊ መንገድ ብቻ ተቃውሟቸውን በአደባባይ ለመግለጽ በወጡ ንጹሀን ዜጎች ላይ በተፈጸመው ኃላፊነት የጎደለው እልቂት ምክንያት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እንድሆን ተገድጃለሁ፡፡ ከዚያን ጊዜ በፊት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ አልነበረኝም፡፡ መለስ ዜናዊ የሚለውን ስም “እገሌ ወይስ እገሌ” ከሚባል ሰው ለየቼ አላውቀዉም ነበር፡፡ ከድህረ ምርጫው ውዝግብ ጋር በተያያዘ መልኩ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ በወጡ ያልታጠቁ ሰላማዊ ንጹሀን ዜጎች ላይ በሟቹ በአቶ መለስ ዜናዊ ቁጥጥር እና ልዩ ትዕዛዝ ከአንድ አካባቢ ተሰባስበው በመጡ አግዓዚ እየተባሉ በሚጠሩ ደም የጠማቸው ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች አነጣጥሮ ተኳሽነት  200 የሚሆኑ ወገኖቻችን ሲገደሉ 800 (ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ በላይ እንደሚሆን በማስረጃ ተረጋግጧል) የሚሆኑት ደግሞ የከባድ እና ቀላል ቁስለኛ ሰለባ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ በዚያ እኩይ ምግባር እንደ ሰማሁ አሳብዶኝ ነበር፡፡ መለስ እና በወንጀል የተዘፈቁት ግብረ አበሮቹ እንደዚያ ዓይነት አሰቃቂ ወንጀል ፈጽመው ለህግ ሳይቀርቡ እና ከፍርድ አንዳያመልጡ ጥረቴን ጀመርኩ፡፡ እነሆ ላለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እና የዴሞክራሲ አስተሳሰቦች እንዲጎለብቱ በማሰብ ለአንድም ሳምንት ሳይስተጓጎል የሰኞ ዕለት ትችት/Monday Commentary በሚል ርዕስ በተከታታይ እያዘጋጀሁ በማሰራጨት ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ በመሞገት እና የሰብአዊ መብት ትምህርቶች እንዲስፋፉ ጥረት በማድረግ ላይ እገኛለሁ፡፡

እ.ኤ.አ በሜይ 2005 በወቅቱ የገዥው አካል ቁንጮ በነበረው በአቶ መለስ ልዩ ትዕዛዝ  ከሁለት መቶ በላይ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች በግፍ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ሲገደሉ እንደ እብድ እንደዘለልኩት ሁሉ አሁንም በተመሳሳይ መልኩ በአምቦ እና በሌሎች አካባቢዎችም በደርዘኖች የሚቆጠሩ ያልታጠቁ ሰላማዊ የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በግፍ በዘፈቀደ እንደ ዋዛ ሲጭፈጨፉ ስሰማ እንደ እብድ በመሆን ዘልያለሁ፡፡ ይህ ድርጊት በእውነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ህዝቦች ሊፈጸም የማይችል እና ለመናገር የሚዘገንን አሳፋሪ እና ዕኩይ ድርጊት ነው፡፡ አሁንም እንደ እብድ ሆኘ እንድዘል የሚያደርገኝ ሌላው ነገር የዱር አራዊት መብት እንኳ ተከብሮ በዘፈቀደ በአንድ ሰው ወይም ቡድን ፍላጎት ምንክያት ብቻ በማይገደሉበት ወቅት በኢትዮጵያ ሰላማዊ ዜጎችን፣ የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በህዝብ ገንዘብ በሚገዛ ጥይት እና ክላስተር ቦምብ እንደ ቅጠል እያረገፉ እነዚህን በህዝብ ደም የተጨማለቁ ወንጀለኞች ለህግ ቀርበው ተጠያቂ የሚያደርግ ነባራዊ ሁኔታ ባለመፈጠሩ ማንም በተዘፈቀበት ወንጀል ተጠያቂ ሳይሆን በአዲስ አበባ እና በሌሎች መንገዶች ላይ ደረታቸውን ነፍተው እየተጎማለሉ የአገሪቱን ሀብት በብቸኝነት በመያዝ በመዝረፍ ላይ የመገኘታቸው ሁኔታ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በህግ ተጠያቂ ያለመሆን ለረዥም ጊዜየቆየ አሳፋሪ የባህል ችግር አለ፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም በህዝብ ላይ እልቂትን ፈጽመዋል ሆኖም ግን በሰራው የግፍ ወንጀል እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ ተጠያቂ አልሆነም፡፡ እኒያ የብዙህን እልቂት ፈጻሚ እና አስፈጻሚ የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያወልቅ እንዲሉ በስልጣን ወንበራቸው ላይ በነበረበት ወቅት በሃፍረትቢስ አንደበቱ “ትንኝ እንኳ አልገደልኩም” በማለት ተሳልቆ ነበር፡፡ በተጨባጭ ግን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎችን ገድሏል፣ እንዲገደሉም አድርግዋል፡፡ ስለሆነም በእድሜው የመጨረሻዎቹ ዓመታት ዝምባብዌ በምቾት ተቀምጦ የልብ ወለድ ድርሰት እና በስልጣን ዘመኑ አድርጊያቸዋለሁ የሚ ለውን የተረት ገድሎች ትረካ በመጻፍ ላይ ይገኛል፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ በእብሪት ተሞልቶ ንጹሀን ዜጎችን ሲገድል እና ሲያስገድል የተከበሩ ሰዎችን ሲዘልፉ እና ሲያዋርድ ቆይቶ በታላቁ አምላክ ፈቃድ ፍትህ ተበይኖበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የቀሩት ደቀመዝሙሮቻቸው  እና የምግባር ጓደኞቻቸው በፍትህ ላይ አፍንጫቸውን ነፍተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. የ2005 ድህረ ምርጫ ውዝግብን ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት ሰላማዊ እና ንጹሀን ዜጎችን በአደባባይ ግንባር ግንባራቸውን እና ደረታቸውን በጥይት እየሰነጠቁ ይረኩ የነበሩት ወሮበላ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች በአሁኑ ጊዜ ያለምንም ተጠያቂነት በአዲስ አበባ መንገዶች ደረታውን ነፍተው ሲንገዋለሉ ይውላሉ፡፡ በአንድ ወቅት ፍትህ በዓለማዊ ወይም በሰማያዊ ኃይል የማትመጣ መስሏቸው ልባቸው ደንድኗል፡፡ በዚያ እልቂት ላይ መሪ ተዋንያን የነበሩትን ወሮበላ “የፌዴራል ፖሊስ” እና አግዓዚ እየተባሉ የሚጠሩትን መንደርተኛ አነጣጥሮ ተኳሾችን ስም ዝርዘር ከነመልካቸው አንድ በአንድ እናውቃለን፡፡ “የኢትዮጵያን የውስጥ ደህንነት ጉዳይ ዘመናዊ ማድረግ” በሚል ርዕስ  የእንግሊዝ ጦር የጸረ ሽብር ባለሙያ የሆኑት ኮ/ል ሚካኤል ዴዋር ስለዚሁ ጉዳይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ወርቅነህ ገበየሁ የነገሯቸውን በመጥቀስ እንዲህ በማለት ገልጸዋል፣ “እ.ኤ.አ የ2005 ድህረ ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት እጃቸው አለበት ተብሎ የተጠረጠሩ 237 የፖሊስ አባላትን በቀጥታ ከስራ አባረናል“ ተባለ፡፡ ድንቄም ማባረር! ከእነዚህ ወንጀሉን ፈጽመው በወንጀል ተዘፍቀው ከሚገኙት ወይም ደግሞ ከወንጀለኞቹ አለቆች አንዳቸውም ቢሆኑ እስከ አሁን ድረስ የፍትህ በሯን የረገጠ ማንም የለም፡፡ የሰውን ልጅ ያህል ክቡር ፍጡር ህይወት በቀን ብርሀን እና በይፋ በአደባባይ በጥይት እየቀጠፉ ላሉ የአዕምሮ በሽተኛ ወንጀለኞች ከስራ አባረርናቸው ብሎ ከመናገር የበለጠ መሳለቅ ያለ አይመስለኝም፡፡

እ.ኤ.አ ከ2005 ምርጫ ጋር ተያይዞ የተፈጸመውን እልቂት አጣርቶ ዘገባ እዲያቀርብ በአቶ መለስ ትዕዛዝ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ2007 ባቀረበው ዘገባ መሰረት ፖሊስ ከመጠን በላይ ኃይል መጠቀሙን፣ በሰላማዊ መንገድ ምንም ዓይነት ትጥቅ ሳይዙ ተቃውሟቸውን ለማሰማት አደባባይ በወጡ ንጹሀን ዜጎች ላይ ግድያ የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ ለተቃውሞ የወጡ ዜጎች ምንም ዓይነት ጥፋት የሌለባቸው መሆኑን ግልጽ አድርጓል፡፡

እ.ኤ.አ ዴሴምበር 2003 የአቶ መለስ ጦር የጋምቤላ ከተማን በመውረር ተከታታይ ጥቃቶችን በማድረግ 400 የአኙዋክ ብሄረሰብ ተወላጆችን የገደለ ሲሆን 1000 ቤቶች ደግሞ እንዲወድሙ ተደርጓ፤፡፡ የአቶ መለስ አገዛዝ በቀጣይ በድርጊቱ ላይ በግንባርቀደምትነት ተሳታፊ እንዳልነበረ እና ከሰለባዎቹ ጎን የቆመ ለማስመሰል እንዲሁም ፍትህ የሚሰጥ በማስመሰል ይቅርታ አዘል መግለጫ ቶ ነበር:: በዚያን ጊዜ ገዥው አካል በደርዘኖች የሚቆጠሩ የአኙዋክ ተጠርጣሪዎች እንደሚያዙ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ እስከ አሁን ድረስ አንድም ወታደር፣ ፖሊስ ወይም ደግሞ የደህንነት ባለስልጣን ለፍርድ አልቀረበም፣ እናም ተጠያቂ አልተደረገም ወይም ደግሞ በጋምቤላ በሰው ልጆች ላይ ለተፈጸሙት ወንጀሎች በወንጀል ፈጻሚዎች ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች የሉም፡፡

እ.ኤ.አ ከኦክቶበር 2007 መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ አቶ መለስ ዜናዊ በኦጋዴን አካባቢ የሚንቀሳቀሱትን ሽምቅ ተዋጊዎች ለመደምሰስ በሚል ሀሳብ ሰፊ የጥቃት ዘመቻ ከከፈተ በኋላ ወዲያውኑ የጥቃት አድማሱን በማስፋት የኦጋዴንን ሰላማዊ ህዝብ የጥቃቱ ሰለባ የሚያደርግ ጥቅል የጥቃት ፕሮግራም በመንደፍ ዘመቻውን አጠናክረው ቀጠለበት፡፡ የአቶ መለስ ጦር በጠቅላላ ያገኛቸውን መንደሮች ሁሉ ደመሰሰ፣ አስገድዶ የመድፈር እና የንብረት ዘረፋ ወንጀሎቸን መፈጸም ጀመረ፡፡ ህዝቡን ለማስፈራራት እና ለሌሎች መቀጣጫ ይሆናል በሚል የደንቆሮ አስተሳሰብ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን እየያዙ በአደባባይ መስቀል እና ጭንቅላታቸውን ቆርጠው ለህዝብ እይታ ማቅረብ እንደብልሀት ወሰዱት፡፡ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘጋቢ ለዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ የውጭ ጉዳይ ንኡስ ኮሚቴ እና ለዓለም ጤና ድርጅት እንደጠቆመው “ኦጋዴን ዳርፉር ሱዳን አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በኦጋዴን እየተደረገ ያለው ሁኔታ ሲታይ ከዳርፉር ጋር በሚመሳስል የዘር ማጥፋት መልኩ በአስፈሪ ሁኔታ ከዳርፉር ባልተለየ መልኩ ተከታታይ ድርጊቶች እየተፈጸሙ በመምጣት ላይ ናቸው“ ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙት ጀኔራል እና የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞው የመንግስት ቃል አቀባይ የነበሩት ኮሊን ፓውል በዳርፉር የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመ ነው በማለት አውጀው ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እ.ኤ.አ ከ2007 -08 በአጋዴን “መጠኑ አነስ ያለ የዘር ማጥፋት ወንጀል” ተፈጽሟል፡፡ በኦጋዴን ለተፈጸመው እልቂት ማንም ለፍትህ አካል የቀረበ ወንጀለኛ የለም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል የእልቂት ተግባራት ዝርዝር እጅግ በጣም ግዙፍ ነው፡፡

በአምቦ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም  በሌሎች ተቋማት እና ከተሞች የተፈጸሙትን አሰቃቂ እልቂቶች በተግባር ላይ ያዋሉትን እና መሪ ተዋንያን የነበሩትን ግፈኛ ወንጀለኞች በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ ያላው ገዥ አካል ለህግ ያቀርባቸዋል የሚል ሀሳብ የለኝም፡፡ እነዚህን ወንጀለኞች ለህግ አለማቅረብ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም አሁን በህይወት የሌለው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ለታዕያታ ያህል ለማስመሰል ያደረገዉን የይስሙላ የማጣራት ምርመራ እንኳ አያስደርግም፡፡ የህዝቡ ጫና እያየለ ከመጣ እና የሚገደድ ከሆነ ገዥው አካል ሊያደርግ የሚችለው በአሻንጉሊቱ የፖሊስ ምርመራ ለታዕይታ የዝንጀሮ ምርመራ እንዲደረግ ማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ ይህም ሊደረግ የሚችለው ለማስመሰያነት እንጅ ከልብ ታምኖበት በወንጀለኞች ላይ ፍትህ የሚያስገኝ የዳኝነት ስራ እንዲሰራ ታስቦ አይደለም፡፡ የዚያ የዝንጀሮ የምርመራ ውጤት የመጨረሻ ዘገባ “ጥቂት ጸረ ሰላም ኃይሎች የቆሰቆሱት እና ያስተባበሩት ብጥብጥ” በማለት ማጠቃለያውን የሚሰጥ ይሆናል፡፡

በአገር ውስጥ ያሉት የተቃዋሚ አመራሮች እና በውጭ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በአምቦ እና በሌሎች አካባቢዎች በገዥው አካል ታጣቂ ኃይሎች የተፈጸሙትን ግድያዎች በአስቸኳይ የሚያጣራ ገለልተኛ የሆነ አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ተጨባጭነት ያለው ዘገባ እንዲያቀርብ እና የንጹሀን ዜጎች ደም በከንቱ ፈስሶ እንዳይቀር በአንድ ድምጽ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከሞራል ውግዘት ባሻገር ከፍ ብለን በመሄድ ጉዳዩ በዝንጀሮው የይስሙላ ፍርድ ቤት እና በዓለም አቀፍ የፍትህ ችሎቶች አደባባይ ላይ እንዲቀርብ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ የእልቂት ወንጀሉን በኢትዮጵያ ላለው ለገዥው አካል የዝንጀሮው የይስሙላ ፍርድ ቤት በማቅረብ በዓለም አቀፍ ሀብረተሰብ ዘንድ እንዲጋለጥ ማድረግ አለብን፡፡ በለጋሽ መንግስታት  በዓለም አቀፍ አካላት እና በፖለቲካ ተቋማት የሚገኙትን መፍትሄዎች የመጠቀም ብልጠት የተሞለባት አካሄድን መምረጥ ይኖርብናል፡፡

በአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና በሌሎች ሰላማዊ ተቃውሞ ባካሄዱ የነቀምት፣ የጅማ እና የሌሎች አካባቢዎች ዜጎች ላይ የተፈጸመውን እልቂት የሚያጣራ ገለልተኛ ተቋም በማቋቋም ስራው በአስቸኳይ እንዲጀመር በኢትዮጵያ ያለውን ገዥ አካል እጠይቃለሁ፡፡ ገዥው አካል የማ ቀረበውን ሀሳብም ሆነ ምክር ይቀበላል የሚል እምነትም ሆነ የተስፋ ጭላንጭል ኖሮኝ አይደለም፡፡ ለእያንዳንዷ ለወረወርኳት ምክር ሁሉ ቅንጣትም ያህል ትኩረት እንደማይሰጡ አውቃለሁ፡፡ ነጻ እና ገለልተኛ የሆነ አጣሪ አካል መቋቋም አለበት የምልበት የእራሴ ምክንያት ስላለኝ ነው፡፡ ይኸውም እንደ መርህ ይዘው (የአንድ ሰው መሞት አሳዘኝ ድርጊት ነው፣ የብዙ ሰዎች መሞት ግን የቁጥር ጉዳይ ነው) በማለት በኢትዮጵያ በስልጣን ወንበር ላይ ተንፈራጥጦ በመቀመጥ የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የሆኑትን ምርጥ ዜጎች እየጨፈጨፈ እየተመለከቱ በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን የሚለግሱትን የኦባማን አስተዳደር፣ የእንግሊዙን የዲቪድ ካሜሩን መንግስት፣ የአውሮፓ ህብረትን፣ የዓለም ባንክን፣ የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት እና ሌሎችን (ከቻይና በስተቀር) ያሉትን አንድ በአንድ ስም በመጥራት (ሀፍረተ ቢሶችን) ለማሳፈር ፈልጌ ነው፡፡ በአሜሪካ፣ እግሊዝ እና አውሮፓ ከሚኖሩ ግብር ከፋዮች ኪስ እየተሰበሰበ በሚመጣ ገንዘብ በኢትዮጵያ ለሚገኙት ወጣቶች መግደያ ጥይት መግዣ እየዋለ እንደሆነ እንዲያውቁት ለማስገንዘብ በማሰብ አምባገነኑን ገዥ አካል ከመርዳት እንዲቆጠቡ ለማድረግ ከንቱ  ጥሪ ለማቅረብ ነው፡፡ ይህንን ጥሪ የማቀርብበት ዋናው ምክንያት እንደዚህ ያለ አሰቃቂ ድርጊት በትምህርት ቤት ልጆች እና በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ እየተፈጸመ የምዕራቡ ዓለም በጠባ በነጋ ቁጥር በልጆች ላይ የሚፈጸም ሰብአዊ ወንጀል እና ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደረግ የሰብአዊ መብት ጥሰት በማስመልከት ጧት ማታ የሚያላዝኑለትን የይስሙላ ጩኸት በመጠቆም ትኩረት እንዲያገኝ ለማስቻል ነው፡፡

በአምቦ የትምህርት ቤት ልጆች እና በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ በፖሊስ እና በደህንነት ኃላፊዎች የተፈጸመውን እልቂት እንዲሁም ይህንን እርኩስ ተግባር እንዲፈጽሙ ያዘዟቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ወደ ፍትህ አደባባይ ለማምጣት እንዲቻል ነጻ እና ገለልተኛ የሆነ አጣሪ አካል እንዲሰየም ለማድረግ የገንዘብ ጡንቻው እና የመጠየቅ አቅሙም ያላቸው የምዕራቡ ዓለም ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች ብቻ ናቸው፡፡ ለገዥው አካል ገንዘብ የሚለግሱት የምዕራብ ገንዘብ ለጋሽ ድርጅቶች ኃላፊነት በማይሰማው የወሮበላ ቡድን ለተጨፈጨፉት ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቻችን ነጻ እና ገለልተኛ የሆነ አጣሪ አካል እንዲቋቋም ጥረት ያደርጋሉ የሚል ሀሳብ እንደማይኖረኝ አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ምክንያቱም ለኢትዮጵያ ልጆች ደንታ የላቸውምና፡፡ ይኸኔ እንኳን ይህን ያህል ብዛት ያለው ሰላማዊ ዜጋ ይገደል ይቅርና አንድ ዜጋ እንኳን በዚህ አይነት አሳፋሪ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ መብቱን በመጠየቁ ብቻ በእነርሱ አገር ቢሞት ኖሮ ዓለምን ሁሉ ያናውጡት ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን ጥሪየን ከማቅረብ ወደ ኋላ አላፈገፍግም!!!

አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም በማቀርበው ጥያቄ የኦባማን አስተዳደር፣ የካሜሮንን መንግስት፣ የአውሮፓ ህብረትን፣ የዓለም ባንክን እና የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ከስሻቸዋለሁ፣ ምክንያቱም በኢትዮጵያ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸመውን የየእለት ወንጀል እየተመለከቱ ለገዥው አካል እርዳታ መለገሱን ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለውበታል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሰው ልጆች ላይ ወንጀል የሚፈጽሙ ወንጀለኞችን የሚረዱ ሁሉ እነርሱም ጥፋተኛ ተብለው ወንጀሉን እንደፈጸሙት ወንጀለኞች ይፈረጃሉ የሚለውን ህጋቸውን በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ጆርጅ ቡሽ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ይህንን የወንጀል ድርጊት በፈጸሙት አሸባሪዎች እና ለእነዚህ አሸባሪዎች ከለላ በሚሰጡት አካላት መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለውም”፡፡ አኛም ገዳዮችንና የገዳዮቺን ደጋፊዎች አንለይም::

አንድ የግል የሆነ ነገር ግልጥ ላድርግ ላንብያብዬ፡፡ ምናልባትም በአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና በትምህርት ቤት ልጆች እንዲሁም በሌሎች ዜጎች ላይ በተፈጸመው እልቂት ለምን እንደ እብድ እዳደርገኝ  ላብራራ፡፡ ለኔ የአምቦ እልቂቶች ዝም ብሎ ለሰብአዊ መብት ጥበቃ ተብለው የሚታዩ ጉዳዮች ብቻ አይደሉም፡፡ እነዚህ እልቂቶች ለኔ ልዩ ናቸው፡፡ ነገሮችን እንደማስበው በተለየ ጊዜ በተለየ ቦታ ሆኖ ነው እንጂ የተጨፈጨፉት ተማሪዎች የእኔን ተማሪዎች ሊሆኑ ይችል ነበር፡፡ በእኔ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ወይንም ደግሞ በእኔ ከፍ ወዳለው ልዩ የሆነው የሴሚናር ክፍል ውስጥ ገብተው ተቀምጠው ሊማሩ ይችል ነበር፡፡ እያንዳንዳቸውን በስም ለይቸ ላውቃቸው እችል ነበር፡፡ ያዘጋጇቸውን የጽሁፍ ስራዎች ገምግሜ የስራ ውጤት መለያ የሆነውን ዋጋ እና ፈተናቸውንም አርሜ ማግኘት የሚገባቸውን ውጤት ልሰጣቸው እችል ነበር፡፡ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ አስቁሚያቸው እና ለምንድን ነው በትምህርት ሰዓት ሳትገኙ የቀራችሁ እና የትምህርት ጊዜ ያባከናችሁ ብዬ ጠይቂያቸው ይቅርታ ለመጠየቅ ያደርጉ የነበረውን ስሜታዊነት የተሞላበት ሂደት እየተመለከትኩ እስቅም ነበር፡፡ በትምህርታቸው ብልጫ እንዲያሳዩ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ተጽእኖ አሳድር ነበር፡፡ የእኔ ተመካርዎቺም  ሊሆኑ ይችሉ ነበር፡፡ በህግ ሙያ ለማሰልጠን እና ሙያቸውን በዚያው መስክ ወይም ደግሞ በህዝብ አስተዳደር ፖሊሲ ማድረግ እንዲችሉ ክትትል አድርግላቸውም ነበር፡፡ የምስክር ደብዳቤዎችንም ለትምርት  ቤት ለሰራ መፈለጊያ እፅፍላቸው ነበር፡፡ ከዚህም በላይ በጣም ለየት ያለ ችሎታ ያላቸውን ተማሪዎች በዓለም ላይ በጣም የተሻሉ እና ምርጥ የተባሉ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም የሚያካሂዱ ዩኒቨርስቲዎችን እንዲቀላቀሉ ድጋፍ አድርግላቸው ነበር፡፡ የእኔ ተማሪዎች እኮ ሊሆኑ ይችሉ ነበር!!!

እነዚህን በግፈኛው ስርዓት የተጨፈጨፉት ተማሪዎች የእኔ ተማሪዎች ቢሆኑ ኖሮ እጅግ በጣም የምኮራባቸው ይሆን ነበር፡፡ በተመስጦ እና በጥንቃቄ እንዲያስቡ ተጽእኖ አደርግባቸው ነበር፡፡ ከሳጥኑ ውጭ እንዲያስቡ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የእራሳቸውን የሀሳብ ሳጥን መፍጠር እንዲችሉ አደርግ ነበር፡፡ ቀኖናዊ እና ሊገሩ የማይችሉ አስተሳሰቦቸን እንዲተው እና ሁልጊዜ ግትር የሆኑ ደንቃራ አስተሳሰቦችን ተጠራጣሪ እንዲሆኑ አስተምራቸው ነበር፡፡ ግልጽ እና በእራሳቸው የሚተማመኑ ዜጎች ሆነው እንዲወጡ እና በመላምት እና ባልተጨበጠ ነገር ላይ መሰረት አድረገው ከመወሰን ይልቅ በተጨባጭ መረጃ ላይ መሰረት አድርገው መወሰን እንዲችሉ አስተምራቸው ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለአመኑበት ዓላማ ያለምንም ማወላወል በጽናት እንዲቆሙ እና በምንም ዓይነት መልኩ ለአምባገነኖች የማይበገሩ እውነትን ከመናገር ለአንዲት ሰከንድ እንኳ ወደ ኋላ የማይሉ ጠንካሮች እንዲሆኑ አስተምራቸው ነበር፡፡ የእነርሱ መምህርና አለማማጅ መሆን ምን ያህል የሚያኮራኝ ይሆን ነበር!

የኢትዮጵያ ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ተረካቢዎች መሆናቸውን እንደማመኔ ሁሉ የአሜሪካ ወጣቶችም የወደፊቷ አሜሪካ አገር ተረካቢ አለኝታዎች ናቸው፡፡ የአሜሪካ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች የማህበራዊ እና የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት በጦር ዛቢያ ላይ ያሉ የጦር ጫፍ ብረቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችም በተመሳሳይ መልኩ እንደዚሁ ናቸው፡፡ በበርክለይ ከንግግር ነጻነት ንቅናቄ ጀምሮ እስከ 1960ዎቹ ጸረ ጦርነት ንቅናቄ ድረስ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በማህበራዊ እና የፖለቲካ ለውጦች እንቅስቃሴ ላይ የማይበገሩ ጠንካሮች ሆነው ዘልቀዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ተማሪዎችም ከዘውዳዊው አገዛዝ ጀምረው የማይበገሩ የማህበራዊ እና የለውጥ አራማጆች ሆነው ቀጥለዋል፡፡

እ.ኤ.አ ሜይ 7/1970 በኦሃዮ ግዛት የኦሃዮ ብሄራዊ የጥበቃ አባላት በኬንት ስቴት ዩኒቨርስቲ ባልታጠቁ የኮሌጅ ተማሪዎቸ ላይ ተኩስ በመክፈት ለ13 ሰከንዶች ያህል 67 ዙር የፈጀ ተኩስ ባደረጉ ጊዜ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ግቢዎች ነገሮቸ ሁሉ ከመቅጽበት መለዋወጥ ጀመሩ፡፡ እነዚያ ተማሪዎች ፕሬዚዳንት ኒክሰን ከቬትናም ወደ ካምፖዲያ የሚያካሂዱትን የመስፋፋት ፖሊሲ ጦርነት በመቃወም አመጹ፡፡ የኬንት ስቴት ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች እልቂት በአሜሪካ ታሪክ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተሳተፉበት ተቃውሞ በመሆን የትምህርት ተቋማት በሙሉ የተዘጉበት ብቸኛው እና የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የኬንት ስቴት የተማሪዎች እልቂት የግመሏን ጀርባ የየሰበረ  ገለባ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1973 አሜሪካ የታጠቀ ጦሯን ከቬትናም ማስወጣት ስትጀምር የቬትናም ጦርነት በእርግጠኝነት መጠናቀቅ ጀመረ፡፡

ባለፉት 44 ዓመታት የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ መንግስት የኬንት ስቴት ዩኒቨርስቲ ግድያን በሚመለከት ኃላፊነት ለመውሰድ እንቢተኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህ ድርጊት ግን ጀግኖቹን የአሜሪካ አርበኞች መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ የአሜሪካ መንግስት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚቴ ፊት ተጠያቂ እንዲሆን ጥረታቸውን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ የኬንት ስቴት እልቂት ፈጻሚዎች ወደ ፍትህ አደባባይ በፍጹም አይቀርቡም ሆኖም ግን አሁን እየተደረገ ያለው ጥረት ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እምነታቸውን በመግለጸቻው ብቻ የአሜሪካ መንግስት የታጠቀ የጦር ኃይሉን ወይም ሰው አልባ አጥቂ አውሮፕላኖቹን (ድሮኖችን) በመጠቀም ሰላማዊ ህዝብ መግደል ወይም ደግሞ ሰላማዊ የህዝብ ተቃውሞን መደፍጠጥ እንደማይችል ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል፡፡፡

የአምቦ ዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ቢያንስ እንደ ኬንት ስቴት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሄዱበትን መንገድ በመከተል ተጠያቂነት እንዲኖር ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ በንጹሀን ወገኖቻችን ላይ ጥይት ያርከፈከፉት ህሊናቢስ ጭራቆች በአገር ውስጥ ባሉ ፍድቤቶች እና በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለፍትህ እንዲቀርቡ የተቀነባበረ ትግል ከማድረግ በፍጹም ለአንዲት ደቂቃም ቢሆን ማቋረጥ አይኖርብንም፡፡ ለተፈጸመው እልቂት አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጥሪ የማቀርበው የገዥውን አካል ዓለም አቀፋዊ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ለማሳፈር ብቻ  ብዬ አይደለም ሆኖም ግን ጀምስ ሩሴል ሎዌል እንዳሉት “እውነት ለዘላለም ተቀብራ አትቀርም ወይም አምባገነን ሸፍጠኞች ለዘላለም በዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው አይኖሩም “ በሚለው መርህ ላይ ሙሉ እምነት ያለኝ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ “የማይታየውን ረቂቅ ድብቅ ነገር በጨለማ ውስጥ መርምሮ የራሱን ውሳኔ የሚሰጥ አምላክ“ እንዳለ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ ማንም ይህን የረከሰውን ምድራዊ ስጋ ተሸክሞ በግፍ ተሞልቶ እና በደም ተጨማልቆ ከህዝብም ሆነ ከአምላክ ተሰውሮ ማምለጥ አይችልም፡፡

በአምቦ ዩኒቨርስቲ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲሁም በሌሎች ወገኖቻችን ላይ የግፍ እልቂት የፈጸሙት ወሮበላ ጭራቆች ወደ ፍትህ አደባባይ እንዲቀርቡ ድምጻችንን ከፍ አድርገን እናሰማ፣ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡም እንጠይቅ!

በአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ ኃላፊነት የማይሰማው ወሮበላ አገዛዝ እልቂትን ሲፈጽም ሁሉም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ድርጊቱን ለመቃወም አልወጡም፡፡ ብዙዎቹ ጸጥታን መርጠዋል፡፡ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ድርጊቱን ለማውገዝ ለተቃውሞ አልወጡም፡፡ ዝም ብለው ተቀምጠው ጊዚያቸውን አሳልፈዋል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በባህርዳር፣ ጎንደር፣ ድሬዳዋ እና በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ያሉ ተማሪዎች ሁሉ ጸጥታን መርጠው አሳልፈዋል፡፡

በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸምን ወንጀል እያየን ዝም ማለት — የእኔ ዝምታ፣ የእናንተ ዝምታ፣ የኦባማ አስተዳደር ዝምታ፣ የዴቪድ ካሜሩን መንግስት ዝምታ፣ የአውሮፓ ህብረት ዝምታ፣ የዓለም ባንክ ዝምታ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዝምታ እና የአፍሪካ ህብረት ዝምታ — የጀርመንን ጸረ ናዚ አቋም ሲያራምዱ የነበሩት የነገረ መለኮት እና የሉተራን ፓስተር የነበሩት ማርቲን ኔሞለር የተባሉት ምሁር ከቀመሩት እንደተማርነው ሁሉ ሁላችንም ከወንጀለኛነት አናመልጥም:፡ ኔሞለር እንዳሉት:-

ናዚዎች ኮሙኒስቶችን ሲያጠቁ ዝም አልኩ፣ ኮሙኒስት አልነበርኩምና፡፡
ሶሻል ዴሞክራቶችን ወደ እስር ቤት እያጋዙ ሲያጉሯቸው ዝም አልኩ፣
የሶሻል ዴሞክራት አባል አልነበርኩምና፡፡

የሰራተኛ ማህበራትን ሲያጠቁ አንድም ቃል ትንፍሽ አላልኩም፣
የሰራተኛ ማህበራት አባል አልነበርኩምና፡፡

አይሁዶችን ነጥለው ሲያጠቁ እንደተለመደው ጸጥ ብዬ ተመለከትኩ፣
ከአይሁድ ዝርያ አልነበርኩምና፡፡

በመጨረሻ ወደ እኔ መጥተው ጥቃት ሲሰነዝሩብኝ
ለእኔ የሚጮህ እና ድምጹን የሚያሰማልኝ አንድም ሰው አልነበረም፡፡

እኔም  እንደ ኔሞለር ተመሳሳይ ስሜት ይሰማኛል፡፡

ገዥው አካል በቤንች ማጅ “ከምስራቅ ጎጃም በመጡ አማራዎች” ላይ አገራችሁ አይደለም
ጨርቄ ማቄን ሳትሉ አሁኑኑ ከአካባቢው ለቃችሁ ውጡ የሚል ጥቃት በሰነዘሩ ጊዜ፣
እንዲሁም አማራዎችን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ የዘር ማጥራት እኩይ ምግባር ሲፈጸምባቸው
ዝም አልኩ፣
አማራ አልነበርኩምና፡፡

በጋምቤላ የአኙዋክ ብሄረሰብ ተወላጆችን አየነጠሉ ለይተው
እንደ ድሮው የአውሬ ግድያ ባህል እያደኑ ሲገድሏቸው፣ ሲጨፈጭፏቸው እና
በዶዘር እየዛቁ በአንድ ጉድጓድ ሲከምሯቸው እያየሁ ዝም አልኩ፣
አኙዋክ አልነበርኩምና፡፡

በኦጋዴን ህዝብ ላይ ጥላቻን በመፈልፈል በቦምብ ሲያጋዩ እና መንደሮቻቸውን በእሳት ሲያቃጥሉ ዝም አልኩ፣
ኦጋዴናዊ አይደለሁምና፡፡

የኦሞቲክ ህዝቦች ለዘመናት ከኖሩበት ቦታቸው በግድብ ስራ ሰበብ ምክንያት
መብታቸው  በግፍ ተጨፍልቆ ሲባረሩ ዝም አልኩ፣
ሙርሲ ሱሪ ያንጋቶም ዲዚ ወይም ሚን አልነበርኩምና፡፡

በአምቦ የኦሮሞ ተማሪዎቸን ሲጨፈጭፉ ዝም አልኩ፣
የኦሮሞ ተማሪ አልነበርኩምና፡፡

በመጨረሻ ወደ እኔ በመምጣት ጥቃት ሲሰነዝሩብኝ
ለእኔ የሚጩህ ወይም ድምጹን የሚያሰማልኝ አንድም ሰው አልነበረም፡፡

ኦሮሞ ብትሆን፣ ትገሬ ብትሆን፣ አኙዋክ ብትሆን፣ ጉራጌ ብትሆን፣ አማራ ብትሆን፣ ኦጋዴኒያዊ ብትሆን፣ ሙርሲ ብትሆን ለእኔ ጉዳዬ አይደለም… ለእኔ አንተ ኢትዮጵያዊ ነህ፡፡ ባለህበት ሁኔታ እወድሃለሁ አከብርሀለሁ! በሰብአዊ መብት ደፍጣጮች መብትህ በሚደፈርበት ጊዜ እና የጉዳቱ ሰለባ በምትሆንበት ጊዜ በፍጹም በፍጹም ዝም አልልም!

በቅርቡ ከባራክ ኦባማ ተለያይቻለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 የእርሳቸው ታማኝ ደጋፊ እንደነበርኩ ሁሉ አሁን በ2014 ደግሞ በአፍሪካ ላይ በሚከተሉት የተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት ታማኝ ትችት አቅራቢያቸው ሆኛለሁ፡፡ ሆኖም ግን በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ላይ በያዟቸው መሰረታዊ እሴቶች ላይ ምንጊዜም ቢሆን እስማማለሁ፡፡ “ወግ ለቀቅ አሜሪካ እና ወግ አጥባቂ አሜሪካ የለም – ያለችው ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ናት፡፡ ጥቁር አሜሪካ እና ነጭ አሜሪካ የለም፣ እንዲሁም ላቲኖ አሜሪካ እና የኢስያ አሜሪካ የለም – ያለችው ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ናት፡፡“

በእኔ እምነት አሮሞ፣ ትግራዋይ፣ አማራ፣ ጋምቤላዊ፣ ኦጋዴናዊ፣ ሙርሲ ጉራጌ… የሚባል ነገር የለም – ያለችው የተከበረች እና በፍቅር ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያ ናት፡፡ ለእኔ የእኛ ስብዕና በኢትጵያዊነት ጥላ ስር የተዋቀረው የአንድነት እና የፍቅር ቀንዲል በጎሳ ላይ ከተመሰረተው ማንነት በላይ መጨረሻ በሌለው መልኩ የበለጠ ጠቃሚነት አለው፡፡ ይህ ለእኔ ቀላሉ እምነትም መርሄ ነው!!!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ግንቦት 19 ቀን 2006 .

 

 

FORUM | AMHARIC