ዓለም ባንክ ኢህአዴግን በረበረው – ከዚያስ?

ኢህአዴግ የተጭበረበረ ሪፖርት አቅርቦ ነበር

ከ ጎልጉል ድረገጽ

February 19, 2014

world bank foto

ኢህአዴግ “አልመረመርም፣ አልበረበርም” በማለት ሲያንገራግር ከቆየ በኋላ በዓለም ባንክ ቀጭን ትዕዛዝ ለመበርበር መስማማቱን ገልጾ በተለያዩ አካላት ምርመራ ተካሂዶበታል። በተከታታይ ሲካሄድ የነበረው ምርመራ አካል የሆነው የመጨረሻ ምርመራ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ተጠናቋል። የጎልጉል ታማኝ ምንጮች እንደተናገሩት ስድስት አባላትን ያካተተው የዓለም ባንክ የምርመራ ቡድን ኢህአዴግን መርምሮ ተመልሷል። የሚጠበቀው የመጨረሻው ሪፖርትና ሪፖርቱ የሚቀርብለት የዓለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ ነው። በቅርቡ የሚወጣውን ውሳኔ አቅጣጫ ለማስቀየር በማሰብ ኢህአዴግ ለመርማሪው ቡድን ራሱ የፈጠረውን “የተጭበረበረ ሪፖርት” አቅርቦ ነበር፡፡

ኢህአዴግ ምርመራውን በተቀነባበረ የፈጠራ ሪፖርት ለማምለጥ ሞክሮ እንደነበር የጠቆሙት የመረጃው ምንጮች “የመርማሪዎቹ ቡድን ሪፖርቱን አንቀበልም፣ የችግሩ ሰለባዎችና ክሱን የመሰረቱት ክፍሎች በሚኖሩበት ቦታ በመገኘት ነዋሪዎችን በተናጠል ለማነጋገር እንፈልጋለን” በማለት ኢህአዴግን እንደሞገቱት አስታውቀዋል። ኢህአዴግ በልማትና በህዝብ ስም የሚያገኘውን ከፍተኛ የዕርዳታ ገንዘብ የጦር ሃይሉን ለማደራጀት፣ የደህንነትና የፖሊስ ሃይሉን ለማስታጠቅና ርዳታ በሚለመንባቸው ዜጎች ላይ የተለያየ ወንጀል ፈጽሟል፣ አሁንም እየፈጸመ ነው በሚል መወንጀሉ ይታወሳል።

የምርመራው መነሻ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በቀድሞው ጠ/ሚኒስትርና የጦር ሃይሎች ዋና አዛዥ፣ የህወሃትና የኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝና በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚዎች በጋምቤላ ክልል የተከናወነው የጅምላ ጭፋጨፋ ነው። በወቅቱ የተካሄደው ጭፋጨፋ ከ400 በላይ የተማሩ የአኙዋክ ወንዶች ላይ ያተኮረ እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ዓለም አቀፋዊ ሪፖርቶችና የጉዳዩ ሰላባዎች ይፋ ያደረጉት ጉዳይ ነው። አቶ መለስ ሞት ቀደማቸው እንጂ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የቀረበባቸውን የክስ ማስረጃ ተቀብሎ ክስ እንዲመሰረትባቸው ከድምዳሜ መድረሱም ይፋ ሆኖ ነበር። ኢህአዴግ በዚሁ ፍርድ ቤት ላይ የአፍሪካ መሪዎችን የማስተባባርና የፍርድ ቤቱን አካሄድ ማውገዝ የጀመረው አቶ ኦባንግ የሚመሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ አቶ መለስ ላይ የመሰረተው ክስ እንዲከፈት መወሰኑን ተከትሎ እንደሆነ በወቅቱ ከየአቅጣጫው አስተያየት የተሰጠበት ጉዳይ ነው።

ከዚህ “ዘግናኝ” እንደሆነ ከሚነገርለት ጭፍጨፋ በኋላም በጋምቤላ ሰፋፊ ለም መሬትን በኢንቨስትመንት ስም ነዋሪዎችን በሃይል እያፈናቀለ በመሸጡ ኢህአዴግ ይከሳሳል። በተለይም የኦክላንድ ተቋምና (Oakland Institute) ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት (Human Rights Watch) ያቀረቡዋቸው ሪፖርቶች ኢህአዴግ በስድብና “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንገድ ተጻራሪዎች፣ ርዕዮተ ዓለሙ ላይ የተነሱ፣ አይኗ እየበራ ያለችውን ኢትዮጵያን ለማጥፋትና ወደኋላ ለመጎተት ልዩ ተልዕኮ ያላቸው፣ የነፍጠኛውን ስርዓት መልሶ ለመትከል የሚሰሩ፣ ጸረ ልማቶች፣ ወዘተ” በማለት ቢያጣጥላቸውም ቀን ጠብቀው ስራቸውን እየሰሩ ስለመሆናቸው እየተነገረ ነው።

ጎልጉል ጥቅምት2፤ 2005 ዓም /October 12, 2012/ ኢህአዴግ ከዓለም ባንክ ያገኘውን 600 ሚሊዮን ዶላርና በተመሳሳይ ፕሮጀክት ወደፊት ሊያገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ገንዘብ በተመለከተ አደጋ ላይ መውደቁን፣ ኢህአዴግ የቀረበበት ውንጀላ ከተረጋገጠ የሚያጣው inspection panelገንዘብ በቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ፣ ዓለምአቀፉ ሁሉን ያካተተ የልማት ተቋም /Inclusive Development International (IDI)/ የተባለውን ተቋም ጠቅሰን “ኢህአዴግ በ600 ሚሊዮን ዶላር አጣብቂኝ ውስጥ ገባ” በሚል ርዕስ መዘገባችን ይታወሳል።

ግፍ የሚፈጽሙ መንግስታትን፣ በልማት ስም የሰብዓዊ መብት በመጣስ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ማስረጃ በመያዝ፤ በስፍራው በመገኘትና ከመሠረቱ ዘልቆ በመግባት አደራጅቶ በመሰብሰብ ተጠያቂ የሚያደርገው IDI ከሰለባዎቹ ውክልና የተሰጠው ተቋሙም በውክልናው መሰረት ለኢንስፔክሽን ፓናል በዝርዝር የሰለባዎቹን በደል በማተት አሳውቆም ነበር፡፡

የኢህአዴግ መከላከያ ሠራዊት የሚያደርሰውን እስራት፣ ግርፋት፣ አስገድዶ መድፈር፣ ከመኖሪያ ቦታ ማፈናቀል፣ የግዳጅ ሰፈራ ወዘተ በማምለጥ ወደ ኬንያ የተሰደዱ የጋምቤላ ነዋሪዎች ይህ ሁሉ ግፍ የሚፈጽምባቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በልማት ስም ከዓለም ባንክ በሚያገኘው የዕርዳታ ገንዘብ በመሆኑ ለባንኩ በላኩት የአቤቱታ ደብዳቤ ተመልክቷል። ዝርዝሩ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡

አቤቱታው ከቀረበ በኋላ ሁኔታውን ለማጣራትና ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያመች ዘንድ ኢንስፔክሽን ፓናል በኢትዮጵያ በመገኘት ምርመራውን አካሂዶ ነበር፡፡ በክሱ መሠረት ፓናሉ በእርግጥ “የዓለም ባንክ ለልማት ሥራዎች የሚሰጠው የእርዳታ ገንዘብ በኢትዮጵያ በተለይም በጋምቤላ ክልል የሚኖሩትን ዜጎች ሰብዓዊ መብት በመጣስ ላይ” እና ለደኅንነትና ወታደራዊ ጥቅሞች ላይ አውሎታል በማለት የምርመራውን ውጤት የዓለም ባንክ ቦርድ ውሳኔ እንዲሰጥበት አቀረበ፡፡ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የውሳኔውና ሃሳብ አስመልክቶ “ኢህአዴግ በሩን እንዲከፍት የዓለም ባንክ አዘዘ” በሚል ሐምሌ 11፤ 2005ዓም /July 18, 2013/ በዘገብንበት ወቅት ከውጪ በሚመጣ ዕርዳታ ላይ ህልውናው የተመሰረተው ኢህአዴግ ገመዱ እየከረረበት መምጣቱን ጠቁመን ነበር፡፡

ኢህአዴግ የዓለም ባንክ ቦርድ ውሳኔውን እንዳያስተላልፍ የተለያዩ የውስወሳ (ሎቢ) ሥራዎችን ሲሰራ እንዲሁም የዓለም ባንክ የራሱን ማጣራት እንዳያደርግ ለማደናቀፍ ሲሞክርና ሲከላከል አምስት ወራት አስቆጠረ፡፡ በመጨረሻም ሐምሌ 11፤ 2005ዓም (July 18) ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ከአዲስ አበባ፤ እንዲሁም በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው ኤምባሲ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በመሆን የዓለም ባንክን አመራሮች ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው እያለ ባንኩ ከአንድ ቀን በፊት ሙሉ ምርመራ እንዲካሄድ አዘዘ። ውሳኔው ባንኩ በራሱ ገንዘብ ማንም ሊያዝበት እንደማይችል ያሳየበትና ለኢህአዴግም እጅግ አሳፋሪ ውሳኔ መሆኑ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተለው ዓለምአቀፉ ሁሉን ያካተተ የልማት ተቋም Inclusive Development International (IDI) እና ሌሎች ክፍሎች አስተያየት ሰንዝረው ነበር። የዜናው ዝርዝር እዚህ ላይ ይገኛል፡፡world-bank

ከዚህ ውሳኔ በኋላ የኅልውናው ጉዳይ ያሰጋው ኢህአዴግ የባንኩ መርማሪ ቡድን ሙሉ ምርመራ እንዳያካሂድ የተቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቶ ነበር፡፡ ምርመራው ተካሂዶ ኢህአዴግ በእርግጥ ከዓለም ባንክ የሚሠጠውን ገንዘብ ለሰብዓዊ መብት ረገጣ ማዋሉን ቡድኑ ካረጋገጠ፤ ኢህአዴግ በትንሹ 600 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያጣ፣ ጉዳቱ ከከፋም እስከ ቢሊዮኖች እንደሚደርስ ጎልጉል በዚሁ ዜናው ምንጮቹን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ከሁለት ሳምንት በፊት ላይ ወደ አዲስ አበባ አቅንቶ የነበረው የዓለም ባንክ የምርመራ ቡድን ሥራውን በትክክል እንዳያካሂድ ኢህአዴግ የራሱን “የተጭበረበረ ሪፖርት አዘጋጅቶ” እንደጠበቃቸው ለጎልጉል መረጃ ደርሶታል። በዚሁ ሪፖርት መሰረት “ችግሩ ካለበት ጋምቤላ ክልል መሔድ አያስፈልግም” በማለት ኢህአዴግ የባንኩን መርማሪ ቡድን ተከራክሮ ነበር። የምርመራው ቡድን አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት አገር ጥለው የኮበለሉትን የቀድሞ የጋምቤላ ክልል መሪ አቶ ኦሞት ኦባንግን የተኩት አዲሱ ፕሬዚዳንትም ረዳቶቻቸውን በመያዝ አዲስ አበባ ተገኝተው ኢህአዴግ የያዘውን አቋም “እኛን እመኑ፤ ነዋሪውን ማነጋገር አያስፈልግም” በማለት ለዓለም ባንክ ቡድን አባላት አቅርበው ነበር።

ለጊዜው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉና ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ከአዲስ አበባ ለጎልጉል እንዳሉት ሶስት ቀን የፈጀ ክርክር ከተደረገ በኋላ የዓለም ባንክ መርማሪ ቡድን በቅድመ ሁኔታ ጋምቤላ የተፈቀደለት ቦታ ብቻ እንዲሄድ ከስምምነት ላይ ተደረሰ። ኢህአዴግ ባዘጋጀው “የተጭበረበረ ሪፖርት” ላይ እንደገለጸው አስቀድሞ ሰፈራን የሚያካሂደው የጤና አገልግሎት፣ ትምህርት ቤት፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ መንገድ፣ የመኖሪያ ቤትና አስፈላጊ መስረተ ልማቶችን እንዳሟላ በስፋት ዘርዝሮ ነበር። በተመረጡት ቦታዎች ምስክርነት እንዲሰጡ የራሱን ሰዎች አዘጋጅቶ እንደነበርና በእድሜ የገፉ አባቶችና እናቶች አስተያየት እንዳይሰጡ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ነበር። በእድሜ የገፉት ሰላባዎች “የመጣው ይምጣ በማለት እውነቱን ለመናገር አይፈሩም፣ በቀላሉም አይደለሉም” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን የሚናገሩት እኚሁ ሰው “የመርማሪው ቡድን በቀላሉ የሚታለል አልነበረም” በማለት የዓለም ባንክ ቡድን በቅርቡ ከሚያወጣው የውሳኔ ሪፖርት በፊት ዝርዝር ጉዳዮችን ከመናገር ተቆጥበዋል።

ከምርመራው ቡድን አባላት መካከል ሁለቱ በኬኒያና በደቡብ ሱዳን ስደት ላይ የሚገኙ የአኙዋክ ተወላጆችን በግንባር ተገኝተው ማነጋገራቸውን ጎልጉል አረጋግጧል፡፡ በተለይ አንደኛዋ እንስት መርማሪ ጭፍጨፋውን አምልጠው የተሰደዱትን ሰዎች ባነጋገሩበት ወቅት እንባቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ሲያለቅሱ እንደነበር የሚያስታውሱት የጎልጉል የመረጃ ምንጮች፣ “ኢህአዴግ displaced anuaksለማጭበርበር ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት፣ የመርማሪዎቹ ቡድን አስፈላጊው መረጃ እንደነበረው፣ ጉዳዩን አስቀድመው ለዚህ ሂደት እንዲበቃ ያደረጉት ክፍሎች የያዙት እውነትና ውክልናውን ወስዶ የክስ ማመልከቻውን ያዘጋጀው ተቋም በቂ ልምድና ሚዛን የደፋ ተግባር ያከናወነ በመሆኑ ኢህአዴግ በተለያዩ ጊዜያት የተዘገቡት ኪሳራዎች ይደርስበታል፣ አሊያም በቀድሞው መንገድ የመቀጠሉ ጉዳይ አሳሳቢ ይሆናል” ሲሉ ግምታቸውን ሰጥተዋል።

ከተለያየ አቅጣጫ አጣብቂኝ ውስጥ እየገባ ያለው ኢህአዴግ፤ አሜሪካ እንደ ቀድሞው ባዶ ቼክ እንደማትሰጥና ካሁን በኋላ ሁኔታዎችን እየመረመረች ገንዘብ እንደምትለቅ መወሰኗ ይህንንም በህግ ማጽናቷ በቅርቡ ሊያካሂድ ካሰበው “ምርጫ” አኳያ የሰሞኑ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ ይህ የአሜሪካ ውሳኔ በአውሮጳውያኑም ዘንድ ተግባራዊ እንዲሆን እየተሰራ ባለበት ባሁኑ ወቅት ኢህአዴግ ፊቱን ወደ ቻይና የማዞር አዝማሚያ ሊያሳይ የፈለገ ቢመስልም የማያዋጣው እንደሆነ በስፋት ይታመናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አቅጣጫው የጠፋበት አካሄድና ውጥረት በአገዛዙ ውስጥ ራሱን የቻለ የፖለቲካ ገመድ ጉተታ ፈጥሮ ችግሩን ሊያባብስ ይችላል እየተባለ ባለበት ወቅት የዓለም ባንክ ከዕርዳታና ድጎማ ጋር በተያያዘ የሚሰጠው ውሳኔ ሊፈጥር የሚችለውን ውጥረት ለመገመት ኢህአዴግ ምርመራው እንዳይካሄድ የተጠቀመውን ማደናቀፊያ መመልከቱ ብቻ በቂ እንደሆነ ይታመናል፡፡

የዓለም ባንክ የምርመራ ቡድን ለምርመራ አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት ኢህአዴግ የቀድሞውን የክልሉን መሪ አቶ ኦሞት ኦባንግን በቁጥጥር ስር በማዋል ለሚከሰስበት ጉዳይ መስዋዕት አድርጎ ሊያቀርባቸው ዝግጅቱን አጠናቆ እንደነበር፣ አቶ ኦሞት ከደህንነትና ከቀድሞ ታጋይና የአሁኑ “ልማታዊ ኢንቨስተሮች” ጋር ባላቸው ትስስር የተነሳ መረጃ ደርሷቸው እንደኮበለሉ ጠቅሰን መዘገባችንይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት አውሮጳ እንደሚገኙ የሚነገረው አቶ ኦሞት ኦባንግ ከዓለም ባንክ ጋር በመገናኘት ከአኙዋኮች ጭፍጨፋ ጀምሮ እስከ አሁኑ ጊዜ ድረስ ለዘመናት የሚያውቁትን ምስጢር ሁሉ ለዓለም ባንክ በማጋለጥ ለራሳቸው ርካሽ የስደተኛ ጉዳይ መጠቀሚያነት ያውሉታል እየተባለ ከቅርብ ወገኖቻቸው ዘንድ ይሰማል፡፡

ኢህአዴግ በየመንደሩና በየክልሉ በተመሳሳይ የሚፈጽማቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና ህገወጥ ተግባራት በተደራጀ መልኩ በማሰባሰብ ዱካውን እየተከተሉ መታገል፣ ዓለም አቀፍ መስመሮችን በመከተል ትግልን ማሳለጥ፣ ኢህአዴግ በሚፈልገው መልኩ ደረጃን ዝቅ በማድረግ አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ አለመግባትና አልሞና አስተውሎ መራመድ የወቅቱ ጥያቄ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚናገሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መሪ አቶ ኦባንግ ሜቶ የዓለም ባንክ እዚህ ደረጃ የመድረሱ ዜና የአንድ ቀን ሥራ ውጤት እንዳልሆነ ሲናገሩ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

ሐምሌ 11፤2005ዓም /July 18, 2013/ “ኢህአዴግ በሩን እንዲከፍት የዓለም ባንክ አዘዘ” በሚል በዘገብንበት ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ኦባንግ “እኛ በመሠረቱ ልማትን አንቃወምም፤ ሆኖም ግን በልማት ስም የሚሠጠው ዕርዳታ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለመርገጥ የሚውል ከሆነ ህወሃት/ኢህአዴግ ተጠያቂ መሆን ይገባዋል፤ የግልጽነትና ተጠያቂነት ዕጥረት እንዲሁም የሙስና በሽታ እንዳጠቃው በራሱ መሪዎች የሚነገርለት ኢህአዴግ፤ የፈለገውን ነገር እንደፈለገው የማድረግ አምባገነናዊ አሠራሩ ራሱን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከተው” በመጥቀስ ድርጅታቸው በጥናትና በዕቅድ ከሚያካሂደው ሁሉን ዓቀፍ ትግል መካከል ይህ አንዱ እንደሆነና “በተጠናከረ መልኩ በመንቀሳቀስ ጉዳዩን ዳር በማድረስ የተጎዱ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን መከራ” እንደሚታደጉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ይህንን የዓለም ባንክ ጉዳይ አስመልክቶ ከአንድ ዓመት በላይ ሲዘግብበት የቆየ ሲሆን በየጊዜው የወጡት የዜና መዘርዝሮች ለአንባቢው ግንዛቤ መስጠት ይችሉ ዘንድ በቅደምተከተል አቅርበናቸዋል፡፡

ኢህአዴግ 600 ሚሊዮን ዶላር አጣብቂኝ ውስጥ ገባ!!

ብያኔው ከጸና ኪሣራው በቢሊዮን ዶላር ሊደርስም ይችላል! ጥቅምት 2፤2005ዓም/October 12, 2012

ኢህአዴግ አንገቱን ታንቋል

ዓለም ባንክ ርምጃ ለመውሰድ ጫፍ ደርሷል – የካቲት 9፤2005ዓም/February 16, 2013

ኢህአዴግ በሩን እንዲከፍት የዓለም ባንክ አዘዘ

የማነቂያው ገመድ ከርሯል፤ “ትግሉ ይቀጥላል” ኦባንግ ሜቶ – ሐምሌ 11፤2005ዓም/July 18, 2013

FORUM | AMHARIC