የማዕድን ሙስና በኢትዮጵያ

ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም ከነጻነት ለሀገሬ

በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ሙስናን አስመልክቶ ይሀ ለሰባተኛ ጊዜ ያቀረብኩት ትችት በማዕድኑ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በሙስና ላይ ያቀረብኳቸውን ሌሎችን ትችቶች “Al Mariam’s Commentaries” የሚለውን ድረ ገጽ በማየት ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ መዋቅራዊ ባህሪ እየያዘ በመጣው ዘርፈ ብዙ ሙስና ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ነቅቶ እንዲጠብቅ ለማስቻል በጉዳዩ ላይ አሁንም ትችቶቼን ቀጣይነት ባለው መልኩ አቀርባለሁ፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት ገዥው አስተዳደር የሕዝብ ትኩረትንና አድናቆትን ለማግኘት ሲል ጥቂት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣኖችና ከዚሁ ጋር በተያያዘ ንክኪ አላቸው ባላቸው ጥቂት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ላይ የሙስና ክስ በመመስረት የጸረ ሙስና ትግሉን በይፋ እንድታይለት ሰብስቦ በእስር ቤት አጉሮአቸዋል፡፡ እነዚህ በሙስና ተጠርጥረው በይስሙላው ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ቀርቦ እየተሰራ ያለው ድራማ ዓለም አቀፍ አበዳሪዎችና ለጋሽ ድርጅቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ግልጽነትና ተጣያቂነት ያለው ስርዓትን እንዲያሰፍን እያደረጉት ባለው ተጽዕኖ ምክንያት ለታይታ ያህል መንግስት የሚተገብረው የፖለቲካ ትወና ነው፡፡ ለአገር ውስጥ ህዝብ ፍጆታ ተብሎ ገዥው አስተዳደር እየተውነ ያለው ይህ የሙስና ድራማ ጥልቅና ስር ሰድዶ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተዋናይነት ተንሰራፍቶ ያለውን ከፍተኛ የህግ ልዕልና ሂደትን የሚጠይቀውን ያገጠጠና ያፈጠጠ ሙስና አሳንሶ በማቅረብ፤ የማታለል ዘዴ በመጠቀም እርባና የለሽና የጮሌነት ጭንብል በማጥለቅ ዋነኞቹን የሙስና ተዋናዮች ለመደበቅ የተዘየደ ተውኔት ነው፡፡

እውነታው ሲታይ ግን በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ያለው ሙስና እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ታማኝ ያልሆኑና ህገወጥ በሆኑ ባለስልጣናት ጓደኞችና ተባባሪዎቻቸው አማካይነት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የጉምሩክ ቀረጥ ሳይከፈልባቸው በሚገቡ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ በሚደረግ የሙስና መሞዳሞድ ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ሙስና መዋቅራዊ ሲሆን፤ በመላ አገሪቱ የፖለቲካ ሰውነት ላይ በስፋት ተሰራጭቶ የሚገኝ ነቀርሳ ነው፡፡ በመሆኑም የዓለም ባንከ ያዘጋጀውን ትልቅ ሪፖርት  “በኢትዮጵያ ሙስናን መመርመር“ የሚል ርዕስ መስጠቱ የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ ይልቁንም እንዲህ በሚል ሊነበብ ይገባዋል “በኢትዮጵያ በስፋት እየተሰራጨ ያለውን የሙስና ነቀርሳ መመርመር“::

ባለፉት ተከታታይ ትችቶቼ በግልጽ እንዳስቀመጥኩት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የሚገኘው መዋቅራዊ ሙስና እራሱን በተለያዩ መንገዶች ይገልጻል:: ለምሳሌም “መንግስት አቀፍና“ (አድራጊ ፈጣሪና ሀብታም ግለሰቦች፤ ቡድኖች፣ የአገዛዙ ስርዓት  ዘመዶች፤ ተባባሪዎችና ደጋፊዎች፤ የውስጥና የውጭ አጧዦች፣ ህግ አጣማሚዎችና በራዦች፤ የቁጥጥርና አስተዳደራዊ ስርዓቱን ለእራሳቸው ጥቅም የሚያውሉ) የሚያካትት ሲሆን፤ “አስተዳደራዊ ሙስና“ (በቢሮክራሲው ልዩ ዘዴንና ስልጣኖቻቸውን በመጠቀም በገፍ የመንግስት ኃላፊዎችና የበታቾቻቸው፤ ያሉትን ህጎች፤ መመሪያዎች፤ ደንቦችና አሰራሮች በማጣመምና ለእራሳቸው ጥቅም እንዲውሉ በማድረግ)  ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በሙስና አገዛዝ (የፖለቲካ ስርዓቱን በመቆጣጠር ጥቂት ቡድኖች በህዝብ ስቃይ እራሳቸውን ለማበልጸግ በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር በተጣበቁ ደም መጣጮች) የምትገዛ አገር ሆናለች፡፡ የዓለም ባንክ ባቀረበው ዘገባና በተለመደው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቢሮክራሲያዊ ዘወር ያለ አቀራረብ “ሙስና በኢትዮጵያ በማዕድኑ ዘርፍ እንደ መሬት፤ ትምህርት፤ ቴሌኮሙኒኬሽን፤ ኮንስትራክሽን እና ሌሎች ዘርፎች ሁሉ በፈጣንና ተዛማች ነቀርሳ የተወረረ ነው“ በማለት በግልጽ አስቀምጦታል፡፡

እንደ ዓለም ባንክ ዘገባ “በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፉ የለማ አይደለም፤ ነገር ግን አገሪቱ በተፈጥሮ የማዕድን ሀብቷ የበለጸገች ናት” ይላል፡፡  በቅርብ ጊዜ ከታመኑ ምንጮች የወጣ ዘገባ እንደሚያስረዳው “የኢትዮጵያ መንግስት በያዝነው የበጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ 11 ወራት በባህላዊ የማዕድን አምራቾች ተመርቶ ወደ ውጭ ከተላከው የማዕድን ሀብት ውስጥ 419 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል፡፡ በዚሁ በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩት የማዕድን ሀብቶች ውስጥ ወርቅ ትልቁን ድርሻ በመያዝ 409.1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያስገኘ ሲሆን ጌምስቶን (የጌጣጌጥ ድንጋይ) እና ታንታለም እንደ የቅደም ተከተላቸው 9.3 እና 1.6 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አስገኝተዋል፡፡ ይህ ገቢ የተገኘው 7878.3 ኪ/ግ ወርቅ፣ 20126.3 ኪ/ግ ጌምስቶን እና 32.95 ቶን ታንታለም ወደ ውጭ በመላክ ነው… ሚድሮክ የወርቅ ማውጣት ኩባንያ በአገሪቱ ውስጥ በወርቅ ማውጣት የስራ ዘርፍ ብቸኛው ኩባንያ ነው፡፡” ሌሎች መረጃዎች እንደሚጠቁሙት “ወደ ውጭ የሚላከው የማዕድን ሀብት የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ረገድ በአገሪቱ የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ በጠቅላላ አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ወጭ ምርቶች ውስጥ 23 በመቶውን ይሸፍናል፡፡”

የዓለም ባንክ “በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ” ውስጥ “ሰባት ዓይነት የሙስና አደጋዎችን” ነቅሶ ያወጣ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ “ሶስቱ ዋነኛ አደጋዎች” ተብለው የቀረቡት “ፈቃድ በማውጣት፤ በፈቃድ አያያዝ ላይ በሚደረጉ ስምምነቶች እና በማዕድን ገቢዎች ላይ የሚደረገው ነው፡፡” ሌላው አሳሳቢው የሙስና ዓይነት “ከካሳ ክፍያዎችና ከአካባቢ ነዋሪዎች ግዴታ፤ ኮንትራክተሮችና አምራቾች: ከማዕድን ካምፓኒዎች ጋር ከሚያደርጓቸው የስምምነት ውሎች፤ ከካምፓኒዎች ምርቶች ጥራት መዝቀጥ እና የማዕድን ምርቶችንና መሳሪያዎችን ከመዝረፍ” አንጻር የሚደረጉ የሙስና ዓይነቶች ናቸው፡፡

የዓለም ባንክ በግልጽ እንዳስቀመጠው “ፈቃድ በማውጣት ሂደት ጊዜ”  “ባለስልጣኖች ፈቃድ ለማውጣትና ለመስጠት፤ ፈቃድ በቶሎ አውጥቶ ለመስጠት ወይም ደግሞ ብዙ ጉዳት የማያመጡ የፈቃድ ሁኔታዎችን ለመስጠት ከማዕድን ካምፓኒዎች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ ይወስዳሉ ወይም ጉቦ ይቀበላሉ፡፡”  ሌላው ተመሳሳይ አደጋ “ባለስልጣኖች ፈቃድ በሚሰጡበት ወቅት ፈቃድ ከሚሰጡት ካምፓኒ ጋር በስውር ድርሻ እንዲኖራቸው ስምምነት ያደርጋሉ፤ ፈቃድ ለመስጠት የመሬት ባለቤትነትን ሊያገኙ ይችላሉ፤ የተወሰነ ድርሻ በአክሲዮን መልክ ወይም ከትርፍ የተወሰነ ድርሻን ይጠይቃሉ፤ ለእራሳቸው ወይም ለጓደኞቻቸው ቅድሚያ ምዝገባ እንዲያደርጉላቸው ከፈቃድ አውጭዎች ጋር ይሞዳሞዳሉ፡፡” በፈቃድ ስምምነት አያያዝ ጊዜ የማዕድን ካምፓኒ ባለቤቶች ሆን ብለው የማዕድን ስምምነቶችን (ለምሳሌ ያህል የአካባቢ፤ የጤና እና የደህንነት ህጎችን እንዲሁም በአካባቢው የማዕድን ካምፓኒው በኃላፊነት የመጠየቅ ደረጃና ሁኔታን ያካትታል) በስራ አንዳይዉሉ ያጨናግፋሉ::

በማዕድን ገቢ አሰባሰብ ጊዜ የማዕድን ካምፓኒ ባለቤቶች ለመሬት መጠቀሚያና ለታክስ የሚያደርጓቸውን ወጭዎች ለመቀነስ ሲባል ሆን ብለው ያመረቱትን ምርት መጠንና ትርፋቸውን በማሳነስ ወጭዎችን ከፍ ያደርጋሉ፡፡ ገዥው አሰተዳደር ከማዕድን ካምፓኒዎች የሚገኘውን ገቢ በትክክል ለማወቅ ነጻ የሆነ የማረጋገጫ አካል የለውም፡፡ ለመሬት መጠቀሚያና የገቢ ግብር መጠን በአጠቃላይ የሚወሰነው የማዕድን ካምፓኒዎች በአመኑት የምርት መጠንና ትርፍ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ምክንያቱም በፌዴራል፤ በክልልና በከተሞች አስተዳደር ያሉ የፈቃድ ሰጭ ባለስልጣኖች በካምፓኒዎች ስላለው ሀብት የሚገልጽ ዝርዝርና ተጨባጭ መረጃ ስለማይገኝ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የማዕድን ካምፓኒዎች ካፒታላቸውንና የስራ ማስኬጃ ወጫቸውን ከፍ ሲያደርጉ ምርቶቻቸውንና የሚገኘውን ትርፍ ደግሞ ዝቅ ያደርጋሉ፡፡ የማዕድን ፈቃድ አሰጣጥና የገቢ ማጭበርበር ክስተት መኖሩ ሲረጋገጥ የማዕድን ካምፓኒ ባለቤቶች በመንግስት አካላት እርምጃ እንዳይወሰድባቸውና የሚመለከታቸው አይተው እንዳላዩ እንዲያልፏቸው ኃላፊነቱ ላላቸው ባለስልጣኖች ጉቦ ይሰጣሉ፡፡

በማዕድን ዘርፉ እስከ አሁን በተጨባጭ በተግባር የታዩና የተመዘገቡ የሙስና ዓይነቶች የሚከተሉትን ያካተታሉ፡- ጉቦ መቀበል፤ የሀሰት መረጃ መስጠት፤ በህገወጥ መንገድ ከማዕድን ካምፓኒዎች ገንዘብ መውሰድና ነጻነታቸውን ዝቅ አድርጎ ማየት፤ እና የውስጥ ህገወጥ መረጃዎችን በመጠቀምና ነጻነት የሌላቸወን ካምፓኒዎች በማጭበርበር ለአካባቢው ነዋሪዎች የተመደበውን ካሳ መስረቅ ሲሆኑ ሰፋ ባለ መልክ በማዕድን ዘርፉ የሚካሄዱ የሙስና ዓይነቶችንና ይዘታቸውን እንደሚከተለው እንመልከት፤

አንድ የማዕድን ካምፓኒ የስራ ፈቃድ ለማውጣት ከፍ ያለ ገንዝብ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ታላላቅ ባለስልጣኖችና የካምፓኒ ባለቤቶች ይህንን ገንዝብ በሚስጥር ይይዙና ገንዘቡ በውጭ ባንክ አካውንት ለባለስልጣኖች እንዲደርስ ይደረጋል፡፡

አንድ ባለስልጣን የማዕድን ካምፓኒ ባለቤቱን የስራ ፈቃዱ በቶሎ እንዲወጣለት ከፈለገ ለለጋሽ ድርጅት በርከት ያለ ገንዘብ መስጠት እንደሚጠበቅበት ይነግረዋል፡፡ ለጋሽ ድርጅቱ ሀቀኛ መስሎ ቢታይም ለባለስልጣኖች ለግል ወይም ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው ጥቅም ከመዋል ወይም ለፖለቲካ ፓርቲ ክፍያ ሊውል ይችላል፡፡

የማዕድን ካምፓኒ የስራ ፈቃድ ለማውጣት እንዲችል ካለው አሰራር አንጻር የጤናና የደህንነት ዕቅድ እንዲያቀርብ ሊጠየቅ ይችላል፤ ነገር ግን ባለስልጣኑ ለካምፓኒ ባለቤቱ ጉቦ ካልከፈለ በስተቀር ተጨማሪና አላስፈላጊ የጤናና የደህንነት ግዴታዎች እንደሚጫንበት ይነግረዋል፡፡

የማዕድን ካምፓኒ የስራ ፈቃድ ለማውጣት የአካባቢ ጥበቃ ዕቅድ እንዲያቀርብ ሊጠየቅ ይችላል፤ ይህም የሚያቀርበው ዕቅድ የአካባቢውን የውኃ አቅርቦት ከመርዛማ ኬሚካሎች በአስተማማኝ ሁኔታ ላያስወግድ ይችላል፡፡ አስተማማኝ የመርዛማ ኬሚካሎች ቁጥጥር ለማድረግ ወጭው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰለዚህ የተጓደለውን የቁጥጥር ስርዓት በመከተል ካምፓኒው ብዙ ወጭ ላለማውጣትና በተጓደለው ሁኔታ ለመስራት እንዲችል የስራ ፈቃዱን ለሚሰጠው ባለስልጣን ጉቦ ይሰጣል፡፡

ባለስልጣኖች ከማዕድን ካምፓኒው ትርፍ ድርሻ እንዲኖራቸው ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ የማዕድን ካምፓኒው ባለቤት የስራ ፈቃድ በባለስልጣኑ ውሳኔ መሰረት አገኛለሁ በሚል እምነት ለባለስልጣኑ ዘመድ ከማዕድን ፕሮጀክቱ ነጻ የትርፍ ድርሻ ሊሰጠው ይችላል፡፡

ባለስልጣኖች በድብቅ በእራሳቸው ለተያዙ ካምፓኒዎች የስራ ፈቃድ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ባለስልጣኖች የስራ ፈቃድ ሊጠየቅበት የሚችል መሬት በድብቅ ያገኛሉ፡፡

አንድ ባለስልጣን የአንድ የማዕድን ቦታ የስራ ፈቃድ ይወጣበታል የሚል ግንዛቤ ካለው ባለስልጣኑ የስራ ፈቃዱ ከመውጣቱ በፊት መሬቱን ቅድሚያ ሊያከራየው ይችላል፡፡ የስራ ፈቃዱ ከተሰጠ በኋላ ግን የመሬቱ ዋጋ ሊጨምር ይችላል፡፡ በዚህም መሰረት ባለስልጣኑ ወይም ባለስልጣኗ በመሬቱ ላይ ያለውን ወይም ያላትን የመሬት ባለቤትነት መብት በመጠቀም ለመሸጥ ወይም ለካምፓኒው የስራ ፈቃድ በመስጠት ለማከራት ይችላሉ፡፡

ካምፓኒዎች የተሰጣቸውን የስራ ፈቃድ ሊሸጡ ይችላሉ፡፡ ባለስልጣኖች የስራ ፈቃድ የምዝገባ ስራን ማጭበርበር ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡

አንድ በመንግስት መ/ቤት መምሪያ የማዕድን ስራ ፈቃድ ለማውጣት የሚያስችል ባለስልጣን አንድ ካምፓኒ የስራ ፈቃድ ማውጣት እንደሚፈልግ አስቀድሞ ሊያውቅ ይችላል፡፡ በመሆኑም ባለስልጣኑ ካለው ግንኙነት አንጻር የቢዝነሱ ሰው በዚያ ቦታ ላይ በፍጥነት የስራ ፈቃድ ማውጣት እንዲችል ሊያሳስበው ይችላል፡፡ ባለስልጣኑ ለቢዝነሱ ሰው የስራ ፈቃዱን ሊሰጠው ይችላል፡፡ ከዚያም የማዕድን ካምፓኒው ከቢዝነሱ ሰው ጋ የስራ ፈቃዱን ይገዛውና የቢዝነሱ ሰው ከባለስልጣኑ ጋር ትርፍ ሊጋራ ይችላል፡፡

አንድ አሳሽ ማዕድን ያለበትን ቦታ ሊያገኝ ይችላል፡፡ በቦታውም ላይ ምልክት በማድረግ ጉዳዩ ወደሚመለከተው የስራ ፈቃድ ሰጭ አካል ጋ በመቅረብ የባለቤትነት ሰርቲፊኬት ማግኘት እንዲችል ሊያመለክት ይችላል፡፡ ሙሰኛ ባለስልጣን ግን ይህንን ግኝት ተቀብሎ አስሶ ባገኘው ስም አይመዘግብም፤ ይልቁንም የቢዝነስ ጓደኛ በመፈለግ በቢዝነስ ጓደኛው ስም እንዲመዘገብ ያደርጋል፡፡ ይኸ ሙሰኛ ባለስልጣን በመጀመሪያ አስሶ ያገኘውን ሰው ሀሰት በመንገር የማዕድኑን ሀብት ከእርሱ በፊት ሌላ እንዳገኘው ይነግረዋል፡፡

ባለስልጣኖች ዘመዶቻቸው የኮንትራት ስምምነት በመፈራረም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ህገወጥ በሆነ መልኩ ከማዕድን ካምፓኒ ባለቤቶች ጋር እንዲፈራረሙ ያደርጋሉ፡፡ ፈቃድ ሰጭው አካል ኮንትራቱን ከመስጠት አንጻር ወይም ማህበረሰባዊ የልማት ዕቅድን ከማምጣት አኳያ በካምፓኒው ሙሉ ወጭ ብዙ የመሰረተ ልማት ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅበት ለካምፓኒው ይነግረዋል፡፡ ለምሳሌ ካምፓኒው መንገድ፤ ትምህርት ቤት ወይም ሆስፒታል እንዲገነባ ወይም አንዲጠግን ሊገደድ ይችላል፡፡ በዚህ መሰረት የመንግስት ባለስልጣኑ አንዱን ወይም ከዚያ በላይ የሆኑትን የመሰረተ ልማት ስራዎች ኮንትራት በድብቅ ለባለስልጣኑ ዘመድ በኮንተራት እንዲሰጥ ይነገረዋል፡፡

ባለስልጣኖችና የአካባቢ ማህበረሰብ መሪዎች ለአካባቢው ማህበረሰብ አባላት መድረስ ያለባቸውን ካሳዎች ይበላሉ፡፡ የማዕድን ስራ ካምፓኒዎች ለማህበረሰቡ የሚሰጡ ካሳዎች ዋጋ ከትክክለኛው ግምት በታች ዝቅ እንዲል ለባለስልጣኖች ጉቦ ይሰጣሉ፡፡

የአካባቢ ኗሪ ማህበረሰብ አባላት በመሬት የስራ ፈቃዱ መሰረት በሀሰት መሬቱን እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡ ኮንትራክተሮችና አምራቾች በተጭበረበሩ የጨረታ፣ ይዞታዎችና ችግር ያለባቸውን ስራዎች በመደበቅና በማጽደቅ ይሰማራሉ፡፡

የማዕድን ካምፓኒዎች ስለማዕድኖች ዓይነትና ጥራት ወይም ደግሞ ለአጽዳቂዎች ጉቦ በመስጠት የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ሙስና ይሰራሉ፡፡ በአሁኑ ጊዙ ይህ ዓይነቱን ሙስና በሚመለከት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የዓለም ባንክ ዘገባ በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ላይ የሚታየውን የገዥውን አስተዳደር ከፊል ችግሮች በመጥቀስ ብቃት የለሽነት ማለትም በማሰባሰብ፤ በማሰማራትና የባለሙያውንና የቴክኒካዊ የሰው ኃይሉን፤ የመመሪያዎችን ቁጥጥርና የአስተዳደራዊ ስርዓቱን ደካማነት አጉልቶ አሳይቷል፡፡ ገዥው ስርዓት ከፈቃድ አሰጣጥ ሁኔታዎች ጋር በተያያዙ ውስብስብ ሁኔታዎች አንጻርና የፈቃድ ጥያቄዎች እየበዙ ከመምጣት አኳያ ጥያቄውን በተገቢው ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል በብቃት የሰለጠነ ፈቃድ የሚሰጥ የሰራተኛ ኃይል የለውም፡፡ ፈቃድ ከመስጠት አኳያና ገቢን ከማስላት አንጻር የማዕድን ስራውን ሂደት የሚገመግሙና በፈቃድ ስምምነት ሁኔታዎች ላይ ክትትል የሚያደርጉ እንዲሁም ካምፓኒዎች በትክክል ለመሬት ኪራይ የሚከፈለውንና በምርትና በትርፍ ላይ የሚጣለውን የገቢ ግብር የሚገመግሙና ቁጥጥር የሚያደርጉ ባለሙያዎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ አካባቢን፤ ጤናንና ደህንነትን እንዲሁም ማህበራዊ ሁኔታዎችን የሚያስቃኙ የስራ ፈቃድ ከመስጠት ጋር በተያያዘ መልኩ የተዘጋጁ ዝርዝር መመሪያዎች የሉም፡፡ የዝርዝር መመሪያዎች አለመኖር በፈቃድ አሰጣጥና ክትትል ወቅት እርግጠኛ አለመሆንን በማስከተል ለሙስና በር ይከፍታል፡፡

የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት በሁለተኛነት ደረጃ የሚይዘው እንዲሁም ዘርፉን በበላይነት የሚቆጣጠረውና የሚያስተዳድረው የማዕድን ሚኒስቴር በጠቅላላ ቁጥጥር የስራ ክፍሉ ውስጥ 13 ብቻ ሰራተኞችና በመላ ሀገሪቱ ተሰራጭተው የሚገኙትን 160 የፌዴራል የስራ ፈቃዶች የሚቆጣጠሩ 3 የአካባቢ ተቆጣጣሪዎች ብቻ መኖራቸው ለማመን የሚያስቸግር እንደሆነ ያመለክታል፡፡

የጸረ-ሙስና ጦርነት ወይም የይስሙላ ሙስና?

ገዥው ስርዓት በወረቀት ላይ ሙስናን በውል ለመለየት፤ ለመከላከል፤ በህግ ለመዳኘትና ቅጣት መቅጣት የሚያስችሉ ህጎች አሉት፡፡ “የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 235/2001 እና A33/2005” ሲቋቋም የወንጀለኛ ህግ መቅጫ በሙስና እና ከሙስና ጋ ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች በሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች ላይ ከፍተኛ ቅጣትን ጥሏል፡፡ እነዚህ ህጎች ግን የተጻፉበትን ወረቀት ያህል ዋጋ የላቸውም፡፡ ህጎቹ እየተመረጡ የገዥው ስርዓት ባለስልጣናት የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥቂያነት እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ በህይወት የተለዩት የገዥው ስርዓት ቁንጮ የጸረ ሙስና ህጎችን የፓርቲው የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረሩትን (ታምራት ላይኔ)፤ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን (ስዬ አብርሀ) እና ሌሎች በስርዓቱ የተጠሉትን ሰራተኞች ለማጥቂያነት በዘዴ  ተጠቅመውባቸዋል፡፡ በቅርቡ በሙስና በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያለው ቡድን በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረው ቡድናዊ ያለመግባባት ትግል መገለጫ እንጅ በእውነትና የጸረ-ሙስና ህጉን በጽናት ለመተርጎም ታስቦ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህን በቁጥጥር ስር ማዋል ደግሞ ዋና መልዕክቱ ገዥውን ስርዓት ወደፊት ይቃወማሉ ብለው ለሚጠረጥሯቸው ተቃዋሚ ኃይሎች ማስፈራሪያና አፍ ማስያዣ ነው፡፡

የሙስና የፍርድ ሂደት ለገዥው ስርዓት ጠንካራ አርጩሜና በአገሪቱ ያሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ አባላትንና የንግዱን ማህበረሰብ አንገት በሸምቀቆ ለማስገባት የተዘየደ ነው፡፡ እውነታው ግን በአሁኑ ጊዜ በሙስና ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን ኃላፊዎች በእርግጥ ጥፋተኞች ናቸው ከተባሉ የእነርሱ አሳሪዎችም ከእነርሱ እኩል የወይም በለጠ ጥፋተኞች ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በአንክሮ እንደተመለከትኩት ወደ ኋላ መለስ ብለን የኢትዮጵያን አባባል በመጥቀስ “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምኗን ይመርርጧል” የሚለውን አባባል እንድናስታውስ እንገደዳለን፡፡

የዓለም ባንከ የ2008 ዓመታዊ የስነምግባርና የጸረ- ሙስና ኮሚሽን የስራ ሪፖርት መሰረት በማድረግ የገዥውን ስርዓት በጠራራ ፀሐይ በሚሊዮኖች የሚያወጣ አስደንጋጭ የወርቅ ዘረፋ አስመልከቶ የሚከተለውን አስፍሯል፡፡

በበጀት ዓመቱ በብሔራዊ ባንክ የተፈጸመ ሌላም ታላቅ ቅሌት ተስተናግዷል፡፡ ይህም ክስተት በብዙዎች ዘንድ “የዓመቱ ታላቁ ቅሌት” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል፡፡ ማጭበርበሩ እንዲህ ተከስቷል፤ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ ማስቀመጥና መግዛት በአዋጅ የተሰጠው ስልጣን ነው፡፡ ለብሔራዊ ባንክ ወርቅ እንዲያቀርቡ የተፈቀደላቸው ጥቂት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ወርቅ በማቅረብ ፈንታ ብዙ ኪሎ ግራም የሚመዝን የተጠፈጠፈ ብረት ወርቅ ቀለም ቀብተው አቀረቡ፡፡ በዚህ አደገኛና አስቀያሚ ቅሌት ውስጥ የባንኩ ጥቂት ሰራተኞች፤ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፤ ማኔጀሮችና ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች ተሳትፎ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ታማኝነት በጎደለው የወርቅ ማጭበርበር ቅሌት ምክንያት መንግስት 16 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዲያጣ ተደርጓልል፡፡

አገዛዙ ሙስናን ለመዋጋት የሚያደርጋቸውን የይስሙላ እንቅስቃሴዎች መንግስት እራሱ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች እውነታውን ይናገራሉ፡፡ ከመንግስት በተገኙ ዘገባዎች መሰረት በጠቅላላ በፌዴራል ደረጃ 422 ሙስና ጉዳዮች ፋይል ተከፍቶላቸው: ከእነዚህ ውስጥ 57ቱ ወይም 13.5 በመቶው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡ አገዛዙ በስነ ምግባርና በጸረ-ሙስና ኮሚሽን የስራ እንቅስቃሴ ላይ ጣልቃገብነት ስለሚያደርግ የኮሚሽኑ ግኝቶችና ዕቅዶች ብዙ ጊዜ በተግባር ላይ ሲውሉ አይታዩም፡፡ የአገዛዙ የሚጠበቀው ምላሽ በሙስና የተጠረጠሩበትን ሁኔታ መካድና  የቀረቡትን ትችቶች ባልሰለጠነ መልኩ መልሶ መተቸት ነው፡፡ እውነታው ግን የጸረ-ሙስና ትግሉ እየተባለ የሚደሰኮረው ዓለም አቀፍ አበዳሪዎችንና ለጋሽ ድርጅቶችን ለማታለልና እውነተኛ ትግል በማስመሰል እርዳታ ለማግኘት የተቀነባበረ የመድረክ ትወና ነው፡፡ የበርቴልስማን ፋውንዴሽን የ2012 የኢትዮጵያ አገራዊ ሪፖርት የአገዛዙን የጸረ-ሙስና ጦርነት ባዶነት በግልጽ ያስረዳል፡-

የኢትዮጵያ የስነ ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በመንግስት ተመስርቶ እስከ አሁንም ድረስ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለ ተቋም ነው፡፡ ቀልጣፋነቱ ትልቅ ነው የሚባል ተቋምም አይደለም፡፡ ህጉን የሚጥሱትና የሙስና ድረጊቶችን የሚፈጽሙ የመንግስት ባለስልጣናት ጉዳይ ለህግ አይቀርብም፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ለመንግስት ታማኝ ያልሆኑ የመንግስት ሰራተኞችን በሙስና ሰበብ በመያዝ ለብዙሀን መገናኛ ፍጆታ ያውሉታል፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት የሚፈጽሙት ሙስና በውል እንዲመረመር አይፈለግም፤ ወይም በማንኛውም ደረጃ ጉዳያቸው በፍርድ እንዲታይ አይደረግም፡፡ ጥቂት የኢህአዴግ አባላትና ቤተሰቦቻቸው በህገወጥ መንገድና በሙስና አማካይነት ሀብት አካብተዋል፡፡ ግልጽነት የጎደላቸውና በሙስና የተዘፈቁ ሆኖም ግን ለመንግስትና ለገዥው ፓርቲ ቅርብ የሆኑ በርካታ ካምፓኒዎች አሉ፡፡ የጸረ-ሙስና ፖሊሲው በምንም መልኩ ስኬታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ የቁጥጥርና ሚዛኑን ስልት ፍጹም በሆነ መልክ አጥፍቶ የሚዋቀር የፖለቲካ ስርዓት በምንም ዓይነት መልኩ የፖለቲካ መቻቻልንና ፍትሀዊነትን የተላበሰ ባህል ሊያጎናጽፍ አይችልም፡፡ የሕወሀትና የኢህአዴግ አራቱ ተጣማሪ ፓርቲዎች አመለካከት በታማኝነት እሴት ባህል የተሞላና ጊዜው ባለፈበት የጦርነት የአስተሳሰብ ባህል የተዘጋ ነው፡፡

እነሱ ዎርቅ ያፍሳሉ፣ ኢትዮጵያውያን አፈር    

አቅም በሌለው አገዛዝ መሪነትና የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም አምራች ድርጅቶች በቅልጥፍና በማይሰሩና ጠንካራ የአስተዳደር ስርዓት ዝርጋታ በሌለበት ሁኔታ የማዕድን ዘርፉ በቀላሉ ለሙስና ዒላማ የተጋለጠ ይሆናል፡፡ ይህ ቢባልም ማንም ሊስተው የማይችለው እውነታ ግን የአገዛዙ አቅመቢስ መሆን በበቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል የተጠናከረ አለመሆን የማዕድን ዘርፉ ተጠያቂነትና ክትትል የማይደረግበት ውስብስብ እና የተሰላ ስልት ነው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የአገዛዙ ባለስልጣኖችና ተባባሪዎቻቸው በሙስና መረብ ውስጥ አስካሉ ድረስ ሙስናን ለመለየት፤ በሙስና የተዘፈቁትን ባለስልጣኖችና ተባባሪዎቻቸውን እንዲሁም በማዕድን ዘርፉ የተሰማሩትን የውጭ ተወካዮችን ይዞ ሙሰኞቹን በህግ ለመጠየቅና ቅጣት ለመስጠት ፈጽሞ የሚቻል አይሆንም፡፡

ማጭበርበር፤ በህገወጥ መንገድ ወይም ሀይልን በመጠቀም ጥቅም ለማግኘት መሞከር፤ በሙስና ገንዘብ ማግኘት፤ እምነተ ቢስ መሆን፣ ሁለት ምላስ መጠቀም፤ በማስፈራራት ገንዘብ መውሰድ፤ ማዋረድ እና የመሳሰሉት በማዕድን ዘርፉ በዝቅተኛ ከፍታ ላይ የተንጠለጠሉ የሙስና ፍራፍሬዎች ናቸው፡፡ የዓለም ባንክ ዘገባ እንደሚያሳየው በማዕድን ዘርፉ ተሳትፎ ያላቸው የአገዛዙ ባለስልጣኖች በፈቃድ አሰጣጥ ላይ፤ ስምምነት በመዋዋልና ገቢን በማረጋገጥ ሂደት ላይ የተፈጠሩትን ድክመቶች በመጠቀም ለሙስና ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ፡፡ በአጠቃላይ አገዛዙ ተጠያቂነት በሌለውና ድብቅ በሆነ መልኩ የሚሰራ ስለሆነ የትክክለኛ ሪፖርት መቅረብ ጥየቄዎችን ያስነሳል፡፡ ለምሳሌ ከማዕድን ዘርፉ ወደውጭ ተልኮ የተገኘው 419 ሚሊዮን ዶላር ከማዕድን ዘርፉ የተገኘ መሆን አለመሆኑን በእርግጠኝነት የሚያረጋግጥ የለም፡፡ የዚህን መጠን እጥፍ ወይም 3 ጊዜ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ቁጥሩ ለህዝብ ከመገለጹ በፊት ከላይ ያሉ ባለስልጣኖች የራሳቸውን ድርሻ ይቆርጣሉ፡፡ አገዛዙ ነጻ የሆነ ኦዲተር ስማይታገስ ከማዕድን ዘርፉ የሚገኘው ገቢ አስተማማኝ መሆኑን ለማረጋገጥ ነጻ በሆነ ኦዲተር መረጋገጥ አለበት፡፡ ለማስተዋስ ያህል   በእ.አ.አ 2006 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዋናው ኦዲተር 4.8 ቢሊዮን ብር በፌዴራል መንግስቱ በጀት ድልድል  ውስጥ ያልተካተተ ነው ብለው ሪፖርት ሲያቀርቡ ከሰራ ተባረዋል፡፡ በበእ.አ.አ 2009 ተተኪው ዋና ኦዲተር የመንግስትን በከፍተኛ ደረጃ መበደር እና አየጨመረ በመጣው የዋጋ ግሽበት ላይ ትችት በማቅረባቸው እንዲባረሩ ተደርጓል፡፡

በበእ.አ.አ 2011 ላይ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቴ የተባለው ድርጅት ባዘጋጀው ሪፖርት ኢትየጵያ 11.7 ቢሊዮን ዶላር በ2000 እና በ2009 ባሉት ዓመታት መካከል በህገወጥ መልክ ከሀገር ውጭ ሄዷል ብሎ አትቷል፡፡ ሪፖርቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ተዘርፏል በማለት አጠቃሏል፡፡ ኢትዮጵያ ከከፋና ከከረፋ የድህነት አረንቋ ለመውጣት ጥረት እያደረገች ቢሆንም በህገወጥ የካፒታል መውጣት እየዋኘች ትገኛለች፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ቀደም ሲል “ኢትዮጵያ እየተዘረፈች ያለች ሀገር“  በሚል ርዕስ ትችት ማቅረቤ ይታወሳል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በ2001 በግልጽ እንዳስቀመጡት የሙስናው ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ የመንግስት ድርጅቶችን እያጠቃ እንደሚገኝ ጠቅሰው መንግስት በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ብቸኛ መለያ እየሆነ የመጣውን ሙስናና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ለማስቆም በርትቶ መስራት እንዳለበት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ በ2013 የሙስናው እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ወቅት ሲሆን መንግስት ለስለስ ባለ መልኩ እየተከላከለው ይገኛል፡፡

አገዛዙ ጥቂት የንግዱን ማህበረሰብ አባላትና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናትን በማጥመድ የጸረ-ሙስና ትግሉን እያጠናከረ መሆኑን ለህዝብ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ አገዛዙ ለሙስና ምንም ዓይነት ትዕግስት እንደሌለው ለማሳየት መሞከር አለበት፡፡ ይህም ማለት መንግስት የተቀነባበር የሙስና ማስወገጃ ዘዴዎችን (ህጎችን፤ ደንቦችን እና መመሪያዎችን) ግልጽነት ባለው ሁኔታ በማውጣት፤ ጠንካራ የምርመራ ስርዓትን በመጠቀምና የፍርድ ሂደቱን በማጠናከር እንዲሁም የሲቪሉን ማህበረሰብ ተሳትፎ በማሳደግና የቁጥጥርና ክትትል ስርዓቱን በማጎልበት የባለስልጣናቱን ሙስና ማጋለጥ አለበት፡፡ ይህም ሆኖ በሙስና በምትዳክረው ሪፑብሊክ ኢትዮጵያ: ሙስና በቅርብ ጊዜ የመጥፋቱ ሁኔታ በጣም አጠራጣሪ ነው፡፡ የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን የተቆጣጠረችው የመጀመሬዋ ሴት የህንድ ፕሬዚዳንት ፕራቲብሃ ፓቲል በግልጽ እንዳስቀመጠችው “ሙስና የመልካም አስተዳደርና የልማት ጸር ነው፤ መወገድ አለበት፤ መንግስትና በአጠቀላይም ህዝቡ በአንድ ላይ ተባብሮ ሙስናን የማስወገዱን አገር አቀፋዊ ዓላማ ማሳካት ይኖርበታል“ በማለት ሀሳቧን አጠቃላለች፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሙስናን ለማስወገድ ፍላጎቱም፤ ችሎታውም፤ ዝግጁነቱም አለው፡፡ ነገር ግን ስራውን በብቃት ለማከናወን ብቃት ያለው መንግስት ያስፈለገዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሙስናን ማዕድን ለማውጣት የለገደንቢን ብጫ የወርቅ መንገድ ተከተል!