የኢትዮጵያ አምባገነኖች ጉም ይጨብጣሉ አውሎ ነፋስን ይዎርሳሉ!

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ

የአፍሪካ አምባገነኖች የዉሃ ላይ ቤተመንግስተና የዉሃ ገደብ: ለዘላለም  ለስማቸው መጠሪያ ይሆናል ብለው ሲገነቡና ሲያስገነቡ ኖረዋል:: ትተው ያለፉት በሕያውነት ጀግነውና ሲወደሱ መኖርን ነበር፡፡ ውጤቱ ግን ጉምን መጨበጥ ነፋስን መውረስ ሆኗል፡፡

የጋናው  ክዋሚ ንክሩማ በ1957 ዓም የመጀመሪያዋን የጥቁር  አፍሪካ ሃገር ከቅኝ ገዢዎች በማላቀቅ፤ወደ ነጻነት መራት፡፡ በመንግስት በሚመራ ንኩርማኒዝም በተባለ ፀንሰ ሃሳብ  ኢንዱስትሪ በማዳበር ዘመናዊ ሶሻሊስት ሃገር ለመገንባት አሰበ፡፡ በቮልታ ወንዝም ላይ አኮሶምቦ ግድብን ገነባ:: ያም በወቅቱ ‹‹ታላቁ የጋና የኤኮኖሚ ግንባታ›› ተብሎ ተወደሰ፡፡ የግልን ዝናም በማሰራጨት በሃገሩ ‹‹መሲህ››፤ ‹‹የጋናና የፓን አፍሪካኒዝም አባት›› “የአፍሪካ ብሔርተኝነት አባት›› አያስባለ አራሱን ሰየመ ፡፡ ነጻ ማሕበራትንና የተቃዋሚዎችን ጎራ አፈራረሰ፤ ዳኞችን ለወህኒ ዳረገ፤ የአንድ ሰው አንድ ፓርቲ ስርአትን በመፍጠር እራሱን ‹‹የዕድሜ ልክ ፕሬዜዳንት›› አደረገ፡፡ በ1966 የወታደራዊውን ሃይል እርግጫ ቀመሰ፡፡ እስካሁን ድረስም በሥራ ላይ ያለውን የአፍሪካን አምባገነኖች መመርያ የሆነውን የአንድ ሰው አንድ ፓርቲ ስርአት አዋቅሮላቸው አለፈ፡፡ በዚህም ንከሩማ ባዶ አየር ወርሶ፤ ጉም ዘግኖ በግዞት ዓለም ሞተ፡፡

የግብፅ ጋማል አብድል ናስርም ራሱ ያተረፈው የአረብ ሶሻሊዝምና ብሔርተኝነትን የተቀደሰ “የፓን አረብ” (መላው አረብ) ፍልስፍና በማለት እያስተጋባ አስተዋወቀ፡፡ በርካታ የደህንነት መረቦችና  የፕሮፓጋንዳ ጦር አሰማርቶ እራሱን የ‹‹ሕዝብ ሰው›› በሚል እራሰ አምልኮ ገንባ፡፡ በሶቭየቶች እርዳታም የአሰዋንን ግድብ ገደበ፡፡ በሃገሪቱ ላይ የአንድ ሰው አንድ ፖርቲ ስርአትን ለማቅቆቃም የስለላ መረቡን ዘርግቶ፤ ከሱ ፓርቲ ጋር ስምምነት የሌላቸውን በተለይም የሙስሊም ብራዘር ሁድ አባላትን አጠፋ፡፡ አሁን ባለንበት ዘመንም እንደምናየው የሙስሊም ብራዘርሁድ (የስላም ወንደማማቾች ፓርቲ)  በሥላጥኑ ወንበር ላይ ሲፈናጠጥ “ናሲሪዝም” የቆሻሻ መጣያ  ዉስጥ ወድቁአል፡፡ ናስር ለግብጽ ወታደራዊ አምባገነንትን ትቶ ሲያልፍ፤እራሱም ባዶ አየር ወርሶ፤ ጉም ዘግኖ አልፏል፡፡

ሞአመር ጋዳፊ ‹‹የሊቢያ ሶሻሊስት አረብ ጃምሂሪያ››ን በማወጅ፤የብዙሃን መንግሥት ዘመን (ጃምሂሪያ) ደረሰ አለ፡፡ የሊቢያን ሕብረተሰብ  ‹‹ሕዝባዊ ኮሚቴ›› በሚባል ስብስብ አቀናጅቶ ለጭቆናው አደራጀ፡፡ ከመሰረተው እርባና ቢስ አደረጃጀት ጋር ያልተስማሙትን ሁሉ በግፍ ጭቆና ውስጥ ከትቶ፤ የሃገሪቱን ብሔራዊ ሃብት እንዳሻው አዘዘበት በከንቱ አባከነው፡፡ ታላቁን ሰውሰራሽ ወንዝ በመቀየስ፤በዓለም ታላቁ የመስኖ ፕሮጄክት ‹‹የዓለም ስምንተኛው አስደናቂ ነገር›› በማለት ሰየመው፡፡ ከኣራት አሰርት ዓመታት አገዛዝ በኋላ ‹‹ወንድም መሪው››  ‹‹የአረንጓዴው መጽሃፍ ደራሲ›› ለፉካ አይጥ ሞት ተዳርጎ አለፈ፡፡ የመከፋፈልና የጥፋት ውርስ ትቶ ሲያልፍ፤ለራሱ ግን ባዶ አየር ወርሶ፤ ጉም ዘገነ፡፡

ኢዲ አሚን ዳዳ ከሁሉም አፍሪካውያን ግፈኛ ገዢዎች የከፋው ‹‹የኡጋንዳው ሰው በላ››  በኡኡጋንዳ ሕዝብ ላይ የሽብር ዘመን በመጫን፤ በጭካኔያዊ ስሜት ለዓለም መገናኛ ብዙሃን አምባገነናዊ ስልጣኑን በይፋ አሳየ፡፡ ጉራ በተመላበት ድንፋታም እራሱን ‹‹የተከበሩ የዘልዓለም ፕሬዜዳንት፤ ፊልድ ማርሻል፤አል ሃጂ ዶክተር  ኢዲ አሚን ዳዳ  VC, DSO, MC,  የምድር አራዊትና የባህር አሳዎች ጌታ ፤ በአጠቃላይ የአፍሪካ የብሪቲሽ (አንግሊዝ )ግዛት ድል አድራጊ፤ በተለይም የኡጋንዳ ነኝ አለ::‹‹ ግድብ አልገነባም ግን የኡጋንዳን ሕዝብ ለ8 ዓመታት ለኩነኔ በመዳረግ በመጨረሻው ተባሮ ለስደት ተዳርጓል፡፡ የሞት ውርስ ካወረሰ በኋላ ለራሱ ግን፤ ባዶ አየር ወርሶ፤ ጉም ዘገነ፡፡

ያ ‹‹ታላቁ መሪ››?

እንደማንኛቸውም የአፍሪካ ግፈኛ ገዢዎች በቅርቡ ያለፈው መለስ ዜናዊም፤ እራሱን ከሕይወት ባሻገር አድርጎ በማግዘፍ አስቀምጦ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መዳኛ  (መድሃኔ ዓለም) ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ጭምር ነኝ እያለ ያስፎከር ነበር፡፡ እራሱን ‹‹ሕልመኛ መሪ፤ የአፍሪካ መኩሪያ አፈ ጉባኤ፤ እና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ከፍተኛው ተግባሪ›› አድርጎ አስቀምጦም ነበር፡፡ ባለፈው  በጋ ወቅት ህልፈቱን ተከትሎ መነዛት የጀመረው ቅጥፈተ ፕሮፓጋንዳ፤ ጥንታዊነትን፤ ውዳሴን፤ አይረሳነትን፤ ተመላኪነት፤ የዘበት ተውኔት (የቀልድ ትያትር) ሆኖ አየታየ ነው፡፡ በመለስ ዜናዊ ፍቃድና ምርጫ የተሰየመው፤ የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ፤ ታማኞች በተሰገሰጉበት ፓርላማ ባደረገው ንግግር መለስን ከክርስቶስ በታች ብቸኛ በማድረግ ምርቃቱንና የራሱንም ታማኝነት መግለጫ መካቢያ ንግግሩን ሲያደርግ: ‹‹ዘልዓለማዊ ክብር ለታላቁ መሪያችን›› በማለት ነበር፡፡ ዋነኛው ታላቁ መሪ የሚባለው የሰሜን ኮርያው ኪም ኢልሱንግ እንኳ፤ ‹‹የሕዝብ ልጅ›› ከመባል ያለፈ ከበሬታ አልተቸረውም ነበር፡፡ ሃይለማርያም የተጣለበትን የፍጥምጥሞሽ መለኮታዊ ውክልና ተልእኮ እንደሃይማኖት ሰባኪ ለመወጣት ከፍተኛ ጉጉት እንዳለው በንግግሩ ቃለ መሃላ ሰጥቷል፡፡ ‹‹ አሁን ያለብኝ ሃላፊነት፤ ……. የማይረሳውን ታላቁን መሪያችንን ዓላማ፤ ምኞት፤ በተሳካ ሁኔታ መፈጸም ነው፡፡……….የታላቁ መሪያችን የእግር ኮቴ በመከተል፤ በአህጉር፤በዓለም አቀፍ ደረጃ ያን ተደማጭነት ያለውን ድምጽ ቀጣይ ማድረግ ነው፡፡ ታላቁ መሪያችን ተደናቂ የሃሳብ አፍላቂያችን ሞተር ብቻ ሳይሆን  እራሱን በመሰዋት አርአያነትን ያስተማረም መሪ ነበር…….››

ታዲያ ሃይለማርያም ደሳለኝ ይሀን ሲናገር የተናገረው ስለመለስ ነበር ወይስ ስለ ገሊላው ሰው?

‹‹የሕልመኛው ታላቅ መሪ›› ሕልምና ውርስ

ከሱ በፊት እንደነበሩት የአፍሪካ አምባገነን ጨቋኝ ገዢዎች መለስም ቅዠት ነበረው፡፡ ከንቱ ስሜት፤ምስጠትም ነበረው፡፡ ታላቅ ሕልም ግን አልነበረውም:: የነበረው፤እራስን የማግዘፍ ራዕይ ነበር፡፡ ከሱ ቀደም ብሎ እንደነበረው ሞቡቱ ሴ ሴ ሴኮ በአፍሪካ ትልቁን ግድብ የመገንባት ሕልም ነበረው፡፡ ታላቁ የተሃድሶ ግድብ የሚባለው፤በአባይ ላይ በቀዳሚ ባጀት ሂሳብ (ላልተጠበቁ አጋጣሚዎች በጀት ሳይቀመጥለት) በ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የመገንባት (ላም አለኝ  በሰማይ) ሕልም ነበረው፡፡ ባለሙያዎች እንዳስቀመጡት፤ይህን መሰሉ ግድብ ከተገነባ፤ ‹‹በሰሜናዊ ምአራብ ኢትዮጵያ ላይ ያለውን  1680 ካሬ ኪሎሜትር ደን፤ በሱዳን ድንበር የሚገኘውን ቦታ ከአባይ ሁለት ጊዜ በሚበልጥ መጠን ሰው ሰራሽ ሀይቅ ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ባሸገርም ‹‹ግድቡ፤ወደ ግብጽ የሚፈሰውን የውሃ መጠን በግድቡ ሙሌት ጊዜ በ25 በመቶ በመቀነስ የአስዋን ግድብን የውሃ ማከማቸት አቅም ያዳክመዋል፡፡ ሱዳኑ መሪ ኦማር አል በሺር ለግብጽ የዓየር ማረፊያ ጣቢያ በሃገራቸው ደቡብ ግዛት ለመገንባት  ተስማምተዋል፡፡የግድቡ ሁኔታ በዲፕሎማቲክ ንግግሩ ደረጃ የማይፈታ ሆኖ ከተገኘ ግድቡን ባየር ጦር ሃይል ላማጥቃት የሚያስችል ጣቢያ ይሆናል::››  የመለስ ችሮታ ከጎረቤት አገር ሁከትና ጦርነት?

መለስ የዕድገት ትራንስፎረሜሽን እቅድ አልነበረውም:: ይልቅስ ከንቱና ስሜታዊ የሆነ የማይጨበጥ የኤኮኖሚ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ቅዠት ነበረው፡፡ ቀደም ሲል፤ ‹‹የመለስ ዜናዊ የጥንቆላ ኤኮኖሚ›› በሚል ጦማሬ ላይ እንዳስገነዘብኩት፡ መለስ በኢትዮጵያ ስላለው የኤኮኖሚ እድገት ሆን ብሎ በተጋነነ መልኩ በተፈጠረና፤ በታገመ እምነት ያወራ ነበር፡፡ በሃገሪቱ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማጥፋትና በመካከለኛ ኤኮኖሚ ውስጥ ያሉትን ሃገራት በመቅደም ሕዝቡም ኑሮውን በማሻሻል ደረጃ ሃገሪቱ ከችግር ለመላቀቅ ክፍተኛ ጉዞ ላይ ነች በማለት ያውጅ ነበር፡፡ (የመለስ ሙት ዓመት ገና ሳይከበር የመለስ ስሪት የሆነው አዲሱ ሰም ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም እድገቱን ወደ ታች አዘቅዝቆ መግለጫ መስጠት ጀምሯል:: አይገርምም!) የአሜሪካን መንግስት አማካይ የዋጋ ግሽበትን አስመልክቶ 36 በመቶ ሆነ ሲል፤ መለስ በ2009/10 በጥንቆላው የኤኮኖሚ ስሌቱ 3.9 በመቶ ብቻ ነው ብሏል፡፡ የዕድገትና ትራንስፎረሜሽን እቅዱ (እኔ ዜናዊኖሚክስ የምለው) በ ጁን 2011 አስተያቴ እንደገለጽኩት ‹‹የመለስ ዜናዊ ቅጥፈኮኖሚክስ›› የይሁንልኝ ምኞት ዝባዝንኬ ነው፡፡  ‹‹በረጂም ወቅት ማይጨበጥ ተስፋ ላይ የተገነባ ኢትዮጵያን የዴሞክራሲ፤ የመልካም አስተዳደር፤ የህግ የበላይነት የተከበረባት ሃገር የማድረግ የማስመሰያና የማወናበጅያ ሃሳብ ነው፡፡ የመለስ የኤኮኖሚ ተረት: ‹‹ዘመናዊና ውጤታማ ኤኮኖሚ በመገንባት የእርሻውን የኤኮኖሚ ዘርፍ፤በአዲስ ቴክኖሎጂ በማገዝ ልማቱን አፋጥኖ የሕዝቡን የኑሮ ደራጃ ከፍተኛ ቦታ ላይ ለማድረስ የሚል የማይጨበጥ ሕልም››  ‹‹የእርሻውን ክፍለ ኤኮኖሚ መሰረት ያደረገ›› የኢንዱስትሪውን ክፍል ለማጎልበት አመቺ ሁኔታ በመፍጠር፤በኢኮኖሚው ላይ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ማድረግ: የአቅም ግንባታን በማሳደግ፤ ወጣቱን፤ ሴቶችን፤ በማሳተፍና ተጠቃሚ በማድረግ መልካም አስተዳደርን መገንባት ነው፡፡ የትራንስፎርሜሽን እቅዱ ‹‹ማስመሰያ ኤኮኖሚክስ›› (sham-o-nomics) ብቻ ነው፡፡  የመለስ ችሮታው የዋጋ ግሽበት፤የኤኮኖሚ ብልሹ አስተዳደር፤የውጭ እዳን መከመርና አካባባዊ ጥፋት?

መለስ ብሔራዊ ራዕይ ጨርሶ አልነበረውም፡፡ ሕልሙና ቅዠቱ የጎሳ መከፋፈልና ማበጣበጥ ነበር፡፡‹‹የብሔር ፌዴራሊዝም›› በሚል የመርዝ መጠቅለያ የተዋጠው ሃሳቡ የሞተውን የአፓርታይድ ስርአት አለሳልሶ በኢትዮጵያ ትንሳኤውን ለማምጣት የታቀደ ቅዠቱ ነበር፡፡ ላለፉት ዓመታት የመለስ ጭንቀትና ጥበት፤ እንቅልፍ አልባው ጥረቱ ወጥ የሆነውን የኢትዮጵያን የአንድነት አቋም አፈራርሶ፤በብሔር፤ዘር፤ ጎሳ የመከፋፈያ ቅርጽ መሰረት ለማደራጀት ነበር፡፡ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 46 (2) ላይ ‹‹ክልሎች የሚገነቡት እንደአቀማመጣቸው ሁኔታ በቋንቋቸው፤ በማንነታቸው፤ በተመሳሳይነታቸው፤ እና በሕዝቡ ፈቃደኛነት ላይ በመመስረት›› ይላል፡፡ ማለትም ‹‹ክልሎች›› (በውስጡ የሚኖሩት ሕዝቦች) ልክ በደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ዘመን እንደነበረው ስርአት በባንቱስታን ላይ ያደርግ እንነበረው፤ ከከብት ባልተለየ ሁኔታ በአይነታቸው ለይቶ በጋጣ ውስጥ እንደማጎር ያለ ስርአት መፍጠር ነው፡፡ እነዚህ የጎሳዎች መኖርያዎች በአፓርታይድ አጠራር ባንቱስታን ወይም በኢትዮጵያ ደግሞ ክልል  (ክልእስታን) ይባላሉ፡፡ በአጠቃላይ የመለስ ምኞት አንድ የነበረውን ሕዝብ በዘር፤ በብሔር፤ በጎሳ፤ በቋንቋ በማለይየት በባብሎንያውያን በቋንቋ ባለመግባባት እንደፈራረሱት አይነት ለመበታተንና ሰላምና አንድነት በማጥፋት እርስ በእርስ በማቆራቆስ ኢትዮጵያ የምትባለውን መሰረቷ የጸናውን ሃገር እንዳልነበረች ለማድረግና ታሪኳን ሕዝቧን የመከራ ገፊት ቀማሾች አድርጎ ማጠፋፋት ነበር፡፡ የመለስ ችሮታ በፖለቲካ፤በተጻራሪ ቡድን፤በጭካኔና  በወገንተኝነት በመበታተን የሁከት አምባ መፍጠር?

በመለስ ሥር ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ምጽዋትና ችሮታ ጠባቂ የለማኝ ለማኝ ሃገር ሆነች፡፡ በሁለቱ አሰርት ዓመታት ኢትዮጵያዊያኖች ቁጥር አንድ የዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ እርደታ፤ የልማት እርዳታ፤ የወታደራዊ እርዳታ፤ ኤድስ መከላከያ እርዳታ፤በዓለም ቀዳሚ ተመጽዋች ሆነች፡፡ ‹‹ የኢትዮጵያ ቦንድአይድ›› በሚለው ጦማሬ ላይ እንዳስቀመጥኩት: መለስ በተሳካለት መልኩ የዓለም አቀፉን ችሮታና ምጽዋት፤ብድር በተለይም የአሜሪካንን መንግስት እርዳታ፤የራሱን የጭቆናና  የግፍ አገዛዝ መረብ ለማጠናከሪያነት በተሳካ ስልት አውሎታል፡፡ የዓለም አቀፍ እርዳታ ሱሰኝነት እና የልመና ባህል የመለስ ችሮታ?

በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ዘመን ሙስና ኢትዮጵያን በሞት አፋፍ ላይ ጥሏታል፡፡ በቅርቡ የዓለም ባንክ 448 ገጽ ያለው የኢትዮጵያን የሙስና ሁኔታ  መመርመር (“የኢትዮጵያን የሙሴና ህመም  ምርመራ”) በሚል ርእስ ዘገባ አውጥቷል፡፡ የዓለም ባንክ አንደሚለው: ሙስና የኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልገሎት ቦርቡሮ በልቶታል:: “በቅርቡ በሰፊው ከተደረገው የቴሌኮሙኒኬሽን ማጠናከሪያ ወጪ ፍሰት አኳያ ሲታይም በአፍሪካ በጣም ዝቀተኛ የቴሌፎን አገልግሎት ፍሰት ያለባት ሀገር ነች፡፡ አንድ ወቅት ላይ ዘመነኛውን የፋይበር ኦብቲክ ገመዶች በማስገባቱ ረገድ ቀደምት ለመሆን በቅታ የነበረች ቢሆንም በአነስተኛና ደካማ ባንድ ዊድዝ፤ አስተማማኝነት ማጣት ችግር ውስጥ ኢትዮጵያ ተዘፍቃለች፡፡ ተጠያቂነት የሌለበት ሁኔታ በመደርጀቱና መንግስትም ጥቅሙን እንጂ ግልጋሎቱ ላይ እጅግም አይኑን ስለጋረደ፤ በሃገርም ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሙስና የተዘፈቀ ድርጅት ሆኗል፡፡”

በግንባታውም (ኮንስትረክሽን) ዘርፍ፤ ያለው ሙስና ‹‹ኢትዮጵያ በሙስና ችግር፤ ደረጃው ዝቅ ባለ ግንባታ፤የተጋነነ የግንባታ ዋጋ ተመን፤ ተግባራዊ ማድረጊያው ዘመን የተጓተተ›› ነው ብሏል ያለም ባንክ፡፡

በፍርድ ስርአቱም ዘርፍ ሙስና “(ሀ) በፍርዱ ሂደትና በተጓዳኝ ዘርፎቹ የፖለቲካው ጣልቃ ገብነት (ለ) ውሳኔዎችን ለማስገልበጥ የጉቦ መቀባበል አጠያየቁ መናር›› ከሁለቱ በአንደኛው ሳቢያ ይመራል፡፡ በማንኛውም ዘረፍ ቢሆን ስለ እድገት፤ ስለልማት፤ ስለ ጤና ስለትምህርት ለፖለቲካ መጠቀሚያ ሲባል ይታወጃል ይለፈፋል እንጂ ማናኛቸውም ተግባር ለሃገርና ለሕዝብ ሊያገኝ ከሚችለው ጠቀሜታ ይልቅ ለስልጣን፤ ለግል መጠቀሚያነት፤ አገልጋዮች ለመግዣ እንዲሆን ተብሎ የሚተገበር ብቻ ነው፡፡  መቋጫ የሌለው የመለስ የሙስና በሽታ ችሮታና ልግስና ?

የመለስ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ከመፈክርነትና ከቃላት ማጭበርበሪያነት ያለፈ አይደለም፡፡ ምንግዜም የአብዮተኛነት ዛሩ ሲነሳበት የሚያውጠነጥነውና የሚደሰኩረው ብቻ ነው፡፡ በቦርዶ ፈረንሳይ ነዋሪ የሆነው ምሁር ጃን-ኒኮላስ ባህ ሲጥፍ: ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ አብዮታዊም ያልሆነ አለያም ዴሞክራሲያዊም ለመሆን የማይችል የሌኒኒስት፤ የማርክሲስት፤ ማኦኢስት፤ እና የሊብራሊዝም ቅንጭብጫቢ በመለስ ዙርያ በሚገኙ የፓርቲ ፖለቲካ ዘይቤኞች እና በጥቂት ኤጀንሲዎች የተፈጠረ ‹‹ዝባዝንኬና ትርኪምርኪ›› ብሎታል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንደ የፖለቲካ ዘይቤ አገልጋይነቱ በኢህአዴግ በሚመራው የአገዛዝ ስርአት ውስጥ የሚከናወነውን ሕገ ወጥነት፤ ስርአት አልበኝነት፤የኤኮኖሚ ሃይlን ማጠናከሪያነትን ሕጋዊ ለማድረጊያነት መገልገያ ብቻ ነው፡፡ የተለያዩ ፓርቲዎች ልሳኖችና በራሪ ወረቀቶች አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሊበራሊዝም  አሻሚ ሕግ በመሆኑ የውስጥንም የውጭንም ተቃዋሚዎች ከጨዋታው ውጪ ለማድረጊያ በመሳሪያነት የሚያገለግል ነው፡፡” በአንድ ወቅት  አንድ አስተያየት ሰጪ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ከኮሚኒዝምና ፋሺዝም ጋር የተቆራኝ ብሎታል::

አብዮታዊ ዴሞክራሲ በ2010 በተካሄደው ምርጫ ወቅት 99.6 በመቶ ድል ለመለስ ለማስረከብ ያገለገለ ነው፡፡ ለተጭበረበረና፤ ለተሰረቀ ሕገወጥ ምርጫና መጥፎ አስተዳደር የመለስ  ልግስና?

መለሲዝሞ (መለሳዊነት) ፡ የመለስ ታላቁ ውርስ

የመለስ ዋናው ውርስ ቅርስ መለሳዊነት ብቻ ነው፡፡ ጥሬው የጉልበት ትምክህተኝነት በሚለው በዲሴምበር 2009 ባቀረብኩት ጽሁፌ ላይ እንዳስቀመጥኩት ነው፡፡ መለስ መለሳዊነትን በሚገባ ተክኖታል አስልቶ ተግብሮታል፡፡ የሱም የፖለቲካ ቅያሱና አካሄዱ፤ ‹‹የኔ መንገድ፤ የአውራ ጎዳና፤ መንገድ አልባ……አለያም ወህኒ!” ነው::

መለስ የሚያረጋግጠው ጀብደኝነት ትክክለኛ ያደርጋል የሚለውን አካሄዱን ነው፡፡ ልክ የገሊላው ሰው ደቀ መዝሙሮች እንደሚሉት ሁሉ የመለስም ተከታይ አገልጋዮች አምላኪዎቹ፤ በመለስ የእግር ኮቴ  ላይ እንደሚረማመዱና ያን ብቻ እንደሚከተሉ ይደሰኩራሉ፡፡  የመለስን መለኮታዊ ሃይል ጉልበታቸውን ለማጠናከር ያልማሉ ይሰግዳሉ፡፡ ከነገሥታት መለኮታዊ ሃይል ልግስና ወደ አነስተኛ አምላክነት መለኮታዊ አመራር! ሆኗል የኢትዮጵያ ዕድል (አያሳዝንም!)::

የመለስ አምላኪዎች ማምለኪያ ጣኦት ሙት ማወደሻነት፤ ፈጣሪነት ሊያሳድጉትና ሊያሳልሙን ይዳዳቸዋል፡፡ የሆነው ቢሆን ያሻቸውን ያህል ቢደነባበሩና ቢፍጨረጨሩ መለስን መመለስ አይቻልም፡፡ እንኳን መለስ ታላቁ ኔልሰን ማንዴላም ለእርገትና ሞቶ ለመነሳት ምኞትም ሃሳብም የላቸው፡፡ ማንዴላ ስለራሳቸው ሲናገሩ ‹‹እኔ እናንተ ደጋግሞ ሃጢአተኛዉን  መልአክ ማደረግ ካልፈለጋችሁ በስተቀር እኔ መልአክ አይደለሁም››  ነው ያሉት፡፡ ጻድቃንም ሆኑ  ዲያቢሎሶች ‹‹ዘልአለማዊ ሕይወት›› አይገባቸውም፡፡  መለስም በስተመጨረሻው እንደማንኛውም የአፍሪካ ከንቱ  አምባገነን መቀመጫው የቆሻሻ መጣያ ነው የሚሆነው፡፡   የመለስ ታላቁ ልግስናው ሊሆን ይችል የነበረው፤ ልግስናዬ ብሎ የሚመኘው ነበር፡፡ በ2007 መለስ ሲናገር ‹‹ተስፋዬና ፍላጎቴ፤ የኔ ችሮታ የተስተካከለና የተረጋጋ የልማት አድገት ኢትዮጵያን ከድህነት የሚያላቅቅና ኢትዮጵያውያንን ከተዘፈቁበት የችጋር አረንቋ ማውጣት ብቻ ሳይሆን፤ በሃገሪቱ ላይ አፋጣኝ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን በአውን ማስፈን ነው›› ብሎ ነበር፡፡ በመለስ አምላኪዎች አፋጣኝ የዴሞክራሲ ግንባታ ካልተጣለ በስተቀር መለስ ለወደፊቱ በታሪክ የሚታወሰው እንደ መላ ቢስ የአፍሪካ ግፈኛ የለውጥና የእድገት ተቃዋሚ ሰው ብቻ ነው፡፡ ከመለስስ በኋላ መለሳዊያኖች መቆሚያቸው መሰረት ያለው ይሆናል? መለሳውያንስ መለስን ሊተኩት ይችላሉ?

ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው የፕሬስ ነጻነት መመልከቻ ተምሳሌት የሆነውና  በመለስ ለወህኒ የተዳረገው ወዳጄ እስክንድር ነጋ የኢህአዴግን ክስረት ሲተነብይ አንደዚህ ብሎ ነበር:: ‹‹ ከሚታየው በስተጀርባ ያለውን ፋቅ ፋቅ አድርገን መመልከት ብንችል ኢህአዴግ እንደሚተረክለትና የማይለወጥ ሃሳብ ያለውና ትልቁ “ዳይናሶርም” (ከድንጋይ ጊዜ በፊት የኖረ አራዊት) አይደለም:: ተዋቅረዋል ከሚባሉት አራቱ አንጃዎች ጋርም ቢሆን የሕወሃት የበላይ ገዢነት ግራ መጋባትና መደነባበር ቅሬታ እንዳቋጠረ ነው፡፡ የአማራ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አስቸጋሪና ስር የሰደደ ጥርጣሬ፤ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አፍራሽ ባህሪ፤  ያዘለ ስብስብ ነው::››

መለስ ራዕይን ከተልእኮ ጋር ግራ ያጋባ ተልእኮ ነበረው፡፡ ያን ተልእኮውንም ጨርሷል፡፡ ታሪክም ልግስናውን ከሰብአዊ መብት ገፈፋ ጋር፤ የፕሬስ ነጻነትን ከማፈን ጋር፤ የዘር መከፋፈልን፤ የማይድን የሙስና በሽታን፤ ከማሰራጭት ጋር አዛምዶ፤ በደሙ ውስጥ በተሰራጨው የተጠያቂነት ሽሽት፤ግልጽነትን በመፍራቱ ያስታውሳዋል፡፡ ሼክስፒር እንዳለው ‹‹ሰዎች የሚፈጽሙት ጥፋት ተንኮላቸው  ከመቃብር  በላይ ይኖራል: መልካሙስራቸው ከአጥንታቸው ጋር ይቀበራል::››  ጸሃፍት እንደሚያስተምሩትም ‹‹የራሱን ቤት ሰላም የነሳ፤ በምልሰቱ ነፋስን ከመጨበጥ አያልፍም፡ ሞኝ ለልበ ብልሁ አገልጋይ ይሆናል::›› መለስና አምላኪዎቹ የኢትዮጵያን ቤቶች ሁላ በጥብጠዋልና ጉም ይጨብጣሉ አውሎ ነፋስን ይዎርሳሉ!

*የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):

http://open.salon.com/blog/almariam/2013/02/03/ethiopia_they_shall_inherit_the_wind

(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::) ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ::

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic

http://ethioforum.org/?cat=24