The cycle of failure in Ethiopian politics

A must read piece about the cycle of failure in Ethiopian politics, particularly in regards to the Ethiopian People Revolutionary Party (EPRP), which one Ethiopian scholar referred to as an “organizer of failure.”

[Click here for PDF]

የውድቀት አዙሪት

ከመጸሃፈ ዕዝራስቱኤል

ጸሃይ ትወጣለች፤ ጸሃይ ትገባለች፤ ይህ ዘላለማዊ ህግ ነው:: በዚህም መምሸትና መንጋት ሁልጊዜም ይኖራሉ:: ስለዚህ ጊዜ ይሄዳል:: በዚህም ሰዎች ለመኖር በሚያደርጉት የማያቋርጥ ጉዞ የሚፈጠረው ክስተት ታሪክ ይሆናል:: ታሪክ ለመጥፎ ትውስታም ሆነ ለበጎ ትዝታ የሚደረገው ሁሉ ቅሉ ታሪክ ተብሎ መዘከሩ አይቀርም:: የታሪኩ ባለቤት ከሆነው አካል ደግሞ ታሪክ የሰራውም ታሪክ የተሰራበትም ከታሪክ ጥሩ ጥሩዉን ለራሱ ለመውሰድ ድርጊቱን እንደየፊላጎቱ ከመተርጎም ጀምሮ የማያደርገው የለም:: በዚህም ለታሪክ ሽሚያ በሚደረገው ገመድ ጉተታ ብዙ አይተናል:: ችግሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሂሳብ ቀመር የሚመራ ባለመሆኑ ሁልግዜም የማይሆነው እየሆነ ማንም ገዥ ሀገሪቱን በመልኩ መቅረጽ ሳይችል እየቀረ ነው እንጂ::

በዘመናዊት እትዮጵያ ውስጥ ማለትም ካለፈው አርባ አመት ወዲህ ሁለት ጊዜ አብዮት ተካሂዶአል:: የ1960ዎች እና የምርጫ 97ን የተከተለው መሆኑ ነው:: የመጀመሪያው አብዮት አንቀሳቃሽ ሃይሎች ተማሪውና የወታደሩ ክፍል ሲሆን አብዮቱ በወታደሩ አሸናፊነት ከተጠነቀቀ በኋላ ወታደሩ የራሱን ኑሮ ኖሮ የማይቀረውን ሞት ሞቷዋል:: የታሪክ ሽሚያው ግን አልቆመም:: ከሞት ተርፎ ስደት የገባው እራሱን “ያ ትውልድ” ብሎ የሚጠራው እና በሌላ በኩል “ብሶት የወለደኝ ተራሮችን ያንቀጠቀጥኩ” ብሎ እራሱን የሚጠራው የወያኔው የአማርኛ ክፍል “ኢህዴን” መካክል የተጀመረ ቢመስልም በተለይ ይህ የወያኔ ቅርንጫፍ ለማን እና ለምን አላማ እንደቆመ ወቅቱ በቶሎ የገለጠበት በመሆኑ የቱንም ያህል አልተራመደም:: በመሰሪዎች ጥንሥሥ የሰከረውን ያንን ለጋ ትውልድ ከሁዋላ ነድተው ከፊት ቀድመው ያነደዱት እራሳችው መሆናቸው ያደባባይ ሚስጥር ነው:: ዛሬ አለምም የኢትዮጵያ ህዝብም በራሳቸው የደርግ ባለስልጣናት ላይ ወያኔ የሞተች አይጥና የጥጋበኛ ድመት አይነት ጨዋታ የሚጫወተው በለጋነቱ ተቃጥሎ ለረገፈው ትውልድ ጥብቅና መቆሙ ሳይሆን ያንኑ መከረኛ ታሪክ ለመውረስ ያደረገው ጥረት አካል ነው:: ታሪክ እራሱን ይደግማል የሚባል የተለመደ አነጋገር አለ:: አንዳንድ ሰዎች አንድን ወንዝ ሁለት ጊዜ አይሻገሩትም:: ታሪክም የራሱን ድርሻ ተዎጥቶ ይሄዳል እንጅ አይመለስም ይላሉ:: ያም ሆነ ይህ ካለፈው ውድቀት ሳንማር ተመሳሳይ በሆነ የውድቅት አዙሪት ዉስጥ ተመልሰን የምንገባው ታድያ ለምንድን ነው?

ምርጫ 97ን ተከትሎ የተሰራውን የታሪክ ሽሚያ እንመልከት:: በፓቲዎች ጥምረት ከምርጫው ጥቂት ቀደም ብሎ ቅንጅት ተወለደ:: የሰባ ሚሊዮኖችን አጀንዳ በለጋ እድሜው ተሸክሞ ዳር ባደርስም የሃገሪቱን የፖለቲካ መልከአምድር ግን እንዳይመለስ አድርጎ ለጭርሱ መቀየሩን አለም ባይኑ ብሌን ያየው ነው:: ሆኖም ቀጣዩ የትግል ጉዞ ወደየት እንሚወስደን ገና ጠርቶ ባልወጣበት ሁኔታ ግን የቅንጅትን ገድል ለመውረስ በያቅጣጫው የተያዘው ገመድ ጉተታ ደግሞ እንግዲህ ሁለተኛው አብዮት ውስጥ የታየ ሌላው ዙር የታሪክ ሽሚያ መሆኑ ነው::

አንደኛው በነሃይሉ ሻውል የሚመራው ቡድን ጡረተኛ ሚሊሻዎች የበዙበትና በቅንጅት መፈጠር ተክለሰውነታቸው አንሶባቸው ከወደቀባቸው ጥላ ለመሸሽ ጥረት የሚያደርጉ እና መጭውን የትግል አጀንዳ ለመሸከም አልችል ብለው ቀንበሩ ትከሻቸውን የሰበራቸው ናቸው::

ሁለተኛዎቹ ወያኔ ክንዱን ያንተራሳቸው ሲሆኑ አንዱ ስሙን (አየለ ጫሚሶ) አንዱ ምልክቱን (ልደቱ አያሌው) ይዘው በትርጉም አልባው ምክርቤት ውስጥ ‘የታሪክ አተላ” ሆነው የቀሩት ናችው::

ለግዜው ፓርላማ የገባው የነተመስገን ዘውዴ ቡድን በምርጫ ቦርድ መስፈርት ምን ትርጉም እንዳለው ባይታወቅም ከነብርቱካን ሚደቅሳ ጋር አብሮ ለመጓዝ በጀመረው መንገድ ለመቀጠል ፈተናው ይከብደዋል:: በቅንጅት ስም ፓርላማ የገባ ስብስብ እንደገና ‘እውቅና’ ካላገኘ ፓርቲ ጋር መዋሃድ ለወያኔው ምርጫ ቦርድ የሚዋጥ አይሆንም:: ስለዚህ ወይ ከጫሚሶ ጋር አብሮ እንዲሰራ አማራጭ ይሰጠዋል:: ወይም ካልተቀበለ እንደ ቀድሞዎቹ የህዎሃት ባለስልጣናት በሃሰት በተሰበሰበ ፊርማ ከፓርላማ ያባርራቸዋል::

የነብርቱካን ሚደቅሳ ቡድን በገመድ ጉተታው ውስጥ ገብቶ የታሪክ ባልተቤትነቱን ይዞ ለመቆየት የሚያጠፋው ግዜ ትርጉም አልባ ስለሆነበት ብዙዎች የተሰውለትን የቃልኪዳን ምልክት ቢያጣውም መንፈሱንና አላማዉን ይዞ ምናልባት ወያኔ ደግ ሆኖ ’የማሪያም መንገድ’ ቢለቅለት ትግሉን ለመቀጠል መወሰኑ ቢያንስ ከሶስቱም የተሻለ የሞራል መሰረት ላይ ያስቀምጠዋል:: ምክንያቱም በኢትዮጵያ የወቅቱ የፍርድ ቤት ተጨባጭ ሁኔታ ወያኔን እንኩዋን ብንተወው ከሃይሉ ሻውል ቡድን ጋር ለሚነሳው የባልተቤትነት ክርክር ስንት አመት ማጥፋት ይኖርባቸው ነበር? ያ ባይሆንማ ኖሮ ያለፈውን አስር ወር ስሙን ከማስከበር ጀምሮ ለሚፈለገው የዲሞክራሲ ጥያቄ ሁለ-ፈርጀ ብዙ ትግል ማድረግ ይቻል ነበር::

ከላይ በቁጥር አንድ የተጠቀሰው የነሃይሉ ሻወል ቡድን ብቻውን አይደለም:: የ “ያ ትውልድ” አካል ነን ብለው እራሳቸውን የሚጠሩ ጥቂት ግለሰቦች ከጀርባው መሽገዋል:: እኒህ የቀድሞው ኢህአፓ አባላት የኢትዮጵያ ትግል ብቸኛ ባለርስት ነን ባዮች ናቸው:: ትናንት በነበየነ ጴጥሮስ ጀርባ በ”ህብረት” ስም ነበሩ:: ዛሬ ያ የትም አላደረሰም:: አሁን ደግሞ በሃይሉ ጀርባ ተደብቀው ምንጣፍ ጉተታ ጀምረዋል:: ትናንት የሰላምን ትግል ሲያወግዙ የነበሩ እኒህ የጨለማ ዘመን ሰዎች ዛሬ የመሳሪያን ትግል አማራጭ የደረጉትን በማውገዝ የሰላም ዘማሪ በመምሰል የሃይሉ ሻወል አወዳሽ ሆነዋል:: የሚገርመው ይህ የትም እንደማይደርስ ብዙ ምልክት እየታየበት ያለው ዲያቢሎሳዊ ጋብቻቸው ለጊዜውም ቢሆን እንዴት እንደተፈጠረ ግን ማሰቡ ሚስጥረ-ስላሴ ነው::

በአንድ ትውልድ ሁለት አብዮት የተካሄደበት የታሪክ አጋጣሚ የለም:: ወይም ከባድ ነው:: የዛሬውን ትግል ከፊት የተጋፈጡት ትናንት ወያኔ አዲስ አበባ ሲገባ የአንደኛ ደረጀ ተማሪ የነበሩ ናችው:: ኢህፓን አያዉቁም:: ካወቁም የተረት ያህል ነው:: ይህ በያመቱ ሻማ ሲያበራ እና ሲያጠፋ ሰላሳ ስድስት አመት ያስቆጠረው ቡድን እድሜውን ሙሉ ዉጪ ሃገር ተቀምጦ ትግሉን በቀላጤ መቆጣጠር የሚፈልግ ነው:: አባላቱ ትናንት በቅንነት የሞቱ ወንድሞቻችንን ስም መነገጃ አድርገው የትናንት ታሪክ ብቻ ሲያወሩ የራሳቸው እድሜ ሶስት እሩቡን አገባዶባቸው አያት እስከመሆን ደርሰዋል:: ስለሆነም እኒህን ጽንፈኛ የኮሙኒስት እርዝራዦች ጨምሮ ሁሉም የቅንጅትን ስም አና ታሪክ ለመዉረስ የሚያደርጉት የጠራራ ፀሀይ ሩጫ የክርስቶስን ልብሱን ተቃደው እጣ ከተጣጣሉበት አይሁዳውያን ምን ልዩነት አለው?

ቁም ነገሩ ይህ የትግል መንፈስ ከማን ጋር እንደቀረ ኣና በቀጣዩ ጉዞ መከራ መስቀሉን ለመሸከም ማን ብቃቱም ቅድስናውም እንዳለው ዘመኑ ገልጦታልና በሰው አገር ተቀምጠው በአንድ የትውልድ ዘመን ሁለት አብዮት በማካሄድ የታሪክ ባለቤት ለመሆን መሞከራቸው የቀን ቅዠት ነው::

እግዚአብሄር ያሳያችሂሁ፤ የካናዳው እና የለንድን የድጋፍ ድርጅቶች የጠሩትን እና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የተጋበዘበትን ስብሰባ እንደዜጋ ገብቶ ሃሳብ ከመለዋወጥ ይልቅ ስብስባዎቹን ለማሰረዝ የተደረገው ያን ሁሉ እሩጫ ምን እንበለው? ባለፈው 17 አመት ተፈጥረው ለነበሩት (ቅንጅትን ጨምሮ) ተቃዋሚ ድርጅቶች ሁሉ ኢህአፓ ተዋናይ ሆኖ ለማጥፋት ያልሞከረው ማን አለ? ትናንት በቅንነት እና በተቃጠለ ብሄራዊ ስሜት ለዚህች መከረኛ ሃገር የተሰውት ታላላቆቻችን ዛሬ ቀና ብለው በስማቸው እየነገደ የተቃዋሚውን ጎራ እየገደለ ሃገሪቱን ለወያኔ ያልጋ ባልጋ መንገድ ያደረገው ይህ ጉድ መሆኑን ቢያዩ ምን ይሰማቸው ይሆን? ይህስ የኛ ትውልድ ትግሉን በወያኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በዚህ ጽንፈኛ ኮሚኒስት ላይም ጭምር የሚያደርገው መቼ ነው?

ትናንት ታላላቆቻችን ለእንደዚህ ያለ እርካሽ አላማ አልሞቱም እና በስማቸው መነገድ ይብቃ! በፍጥነት እየተለወጠ ካለው አለም እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር አብሮ መጉዋዝ አልችል ያለውንና የትግሉ ዳይናሚክስ አልፎት የሄደውን ጨለምተኛ ሁሉ ከመንገድ እየለቀሙ አገሪቱን ማድማቱ ይብቃ! ሰላሳ ስድስት አመት ሙሉ ሻማ ሲያበሩ ወያኔ ከጫካ ተነስቶ ዛሬ ባለታሪክ፤ አገር በጅምላም በችርቻሮም እየሸጠ፤ ህዝቡንም ያለከልካይ ሲገድል ቢያንስ የት ላይ እንደቀራችሁ ብትመረምሩ በጎ ነበር:: እናንተ ዘመን ያለቀባችሁ፤ ወሬ የሻገተባችሁ፤ አሮጌ ማስታወሻ የሰረዛችሁ ከንቱ የሙት አለም ትዝታ ሆናችኋል፤ በራሳችሁ ትውልድ እድል ቀልዳችሁ እንደገና በዚህ ትውልድ እድል እና እጣ ፋንታ ለመቀለድ እድል የሚሰጣችሁ የለም::

የኢትዮጵያን ትንሳኤ የሚናይበት ቀን እሩቅ አይደለም