Is Siye a changed person? (Amharic)

ስዬ አብርሃ – አዲስ ወይን ጠጅ ባዲስ አቁማዳ ወይስ አሮጌ ወይን ጠጅ ባዲስ አቁማዳ?

ከተስፋሚካኤል ሳህለስላሴ

Read in PDF

እንደማስጠንቀቂያ፡- እንድታውቁት ያህል

አቶ ስዬ አብርሃ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መግቢያ ላይ በዋሽንግተን አካባቢ ያደረጉትን ውይይት ለመካፈል ስሄድ፣ ማንም የሚረዳውና የሚገምተው ጥርጣሬና ጥያቄ በውስጤ ቋጥሬ ነበር። መቼም እኚህን መከራችንን ካመጡትና ካበዙት አንዱ የሆኑትን ሰው ለማየትና ለመስማት ስሄድ፤ የምደግፋቸውና የምከተላቸው ዶ/ር ያዕቆብ ወይም ብርቱካን ሲመጡ እየዘለልኩና በሙሉ ልብ፣ እንዲሁም በመተማመን እንደተቀበልኳቸው አቶ ስዬንም ገና ለገና ከኢህአዴግ ስለተጣሉ ብቻ ያለምንም ጥያቄ እንድቀበል የሚጠብቅ ያለ አይመስልኝም። ‘አብዮት ልጇን ትበላለች’ የሚለው አባባል የቅርብ ግዜ የሕይወት ማስረጃ የሆኑትን አቶ ስዬ ቀርቶ፣ እነዚያ ስናጨበጭብላቸውና ስናቆላምጣቸው የኖርነው የቅንጅት መሪዎችም ሲመጡ አንዳንዶች በምን መልኩ እንደተቀበሏቸው ያስተዋለ፤ አቶ ስዬ ላይ በሚነሱ ጥርጣሬዎችና ተቃውሞዎች ሊደነግጥም ሊበሳጭም አይገባም።

ስለዚህ አቶ ስዬም ይህንን ተረድተው ነገሮችን እስኪያጸዱ ድረስ፣ ካጸዱም በሁዋላ እንኳን ቢሆን፤ እሳቸውን የሚጠራጠር፣ በክፉ የሚያያቸው፣ እንዲሁም ወደሚያዘጋጁት ስብሰባ በጥርጣሬ ልብ የሚመጣ ታዳሚ ቢኖር፤ ሳይሰለቹና ሳይበሳጩ ማስረዳትና ማሳመን፣ የህዝቡንም አመለካከት በሂደት መለወጥ አለባቸው። እንጂ ‘የለም ዝም ብላችሁ ተቀበሉ’ ሊባል አይገባም። የሆነ ሆነና ጥርጣሬና ጥያቄዎች፣ ትንሽ ትንሽም ተስፋ መቁረጥ እያወዛወዘኝ ነው ከስብሰባቸው የተገኘሁት። እንደፈራሁትም ወይም እንደጠበቅኩትም ብዙ ጥያቄዎቼ ሳይመለሱ፣ ገሚሶቹ ጥያቄዎቼ ተጠናክረው ተመለስኩኝ። ይሄ አስተያየትም/ጽሑፍም የዚህ ይዤ የሄድኩት፣ ይዤም የተመለስኩት ጥርጣሬ ያጠላበት ነውና በዚያ ጠቅላላ ግምት አንብቡት። ያኔ እንዴት እንደነበሩ የምናውቃቸው አቶ ስዬ አሁን እንዲህ ናቸው ለማለት ይቀረናል።

አቶ ስዬ ከሰላሳ ዓመት በላይ ከቆዩበት ትግራይን ማዕከል ያደረገ የትግልና የፖለቲካ መንፈስ ሙሉ በሙሉ በስድስት ዓመታት እስር እንዳልተላቀቁ ሁሉ፣ እኔም ከዚህ አስራ ሰባት ዓመት ካጨድኩት ኢህአዴግን የመጥላት መንፈስ፣ አቶ ስዬን የመጠራጠር አስተሳሰብ ባንድ ስብሰባ ውይይት፣ በጥቂት መግለጫዎችና በተንጠባጠቡ ማባበያ ሃሳቦች ልወጣ አይችልም። ለጊዜው ግን አቶ ስዬን መጥላት አቁሜያለሁ። አቶ ስዬ በዋሽንግተኑ ስብሰባ እንዳስተዋልኳቸው ከሆኑ፣ የሚጠራጠሯቸው እንጂ የማይጠሏቸው፣ ዕድል የሚሰጣቸው እንጂ የማይተማመኑባቸው፣ አሁንም ቢሆን የመለስና ቡድኖቹ ጥላቻቸው የጨመረ እንጂ ያኔ በሃያ ሁለት ዓመታቸው የገቡበት ወያኔያዊ መንፈስ ያለቀቃቸው፣ ከዚያ በተረፈ ስለኢትዮጵያ ቢናገሩም ስለትግራይ ግን የበለጠ የሚቆረቆሩ፣ ስለታሰሩ የኦሮሞ ተወላጆችና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ቢያነሱም፣ በቅድሚያ ግን የወንድማቸው መፈታት እንቅልፍ የሚነሳቸው፣ አቅማቸውና ጡንቻቸው በእጅጉ የኮሰሰ ምስኪን ሁነው አግኝቼያቸዋለሁ። ነገሬን በመግቢያ ሳልጨርሰው ወደ ዋናው ሀተታዬ ልግባ። እነሆኝ እይታዬ፦

ስለብሰባው፣ ስለውይይቱ፣

ምንኛ ድንቅ ሃሳቦች፣ ሰውየው አቶ ስዬ ባይሆኑ!

ይሄ በዋሽንግተን አካባቢ ከአቶ ስዬ አብርሃ ጋር የተደረገው ውይይት በጥቅሉ መልካም ጅምር ነው። አብዛኛው አቶ ስዬ የተናገሯቸው ሃሳቦች፤ እሳቸው ባይናገሯቸው ኖሮ የሚማርኩ፣ ዕውቀት ከዩኑቨርስቲ ብቻ ሳይሆን ከሕይወት ልምድም እንደሚገኝ ማስረጃ የሆኑ፣ እንከን የማይወጣላቸው፣ ያለምንም ጫቻታ የምንቀበላቸው፣ እንዲሁም ሰውየው የሚናገሩትን የሚያውቁ መሆናቸውን የጠቆሙ፤ ሳይታሰሩ በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬድዮ ብቻ በሩቁ ለሚያውቃቸው ለኔ ቢጤ ሰው – ሰውየው ከቀድሞው “ጦርነትን መሥራትም እናውቅበታለን” ያሰኘ እብሪታቸው እንደተመለሱ የሚጠቁሙ፤ የምስራቅ አፍሪካውን ቀንድ ጠቅላላ ሁኔታ በቅጡ የቃኘ፣ ለመጪው ትግላችንም እንዴት መጓዝ አለብን የሚለውን የጠቆመ፣ ያላሰለቸ፣ ወርቅ ውይይት ነበር።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች እንዳስቀመጡት ግን እንዲሁ በደፈናው አጨብጭበንለት የምናልፈውና አቶ ስዬን ለድህነታችን ትልቅ ብርታት ይዘው እንደመጡ አድርገን የምንወስደው ውይይት አልነበረም። አቶ ስዬ ወደ ትግል ከገቡበት ጊዜ አንስቶ ኢህአዴግ ሥልጣን እስከተቆጣጠረበት፣ ከዚያም እሳቸው ታስረው እስከተፈቱበት ጊዜ ያሳለፉትን የፖለቲካ ሕይወት የዳሰሰና፣ መቼም ውይይቱን የሆነ ቦታ መጀመር አለብንና፤ ለመነሻና ውይይት ለመጀመር ወይም ሲቪል ክርክር ለመጫር ያህል መልካም ነው። ይሁን እንጂ እንደኔ እንደኔ ግምገማ ቀጥሎ በማስቀምጣቸው ምክንያቶች የተነሳ፣ አቶ ስዬ የያዙት አቋም እሳቸውንና ቡድናቸውን ሲታገልና ሲያወግዝ የነበረውን ኃይል ወደ መሀል አምጥቶ (ወይም እኛ እሳቸውን ስንቃወም የነበርነውን ወደመሀል አቅርቦ) አንድ ላይ የሚያሰልፍ ነው ለማለት አያስደፍርም።

ወደስብሰባው የደረስኩት ዘግይቼ ነበር። ስላጀማመሩ እንደሰማሁት፣ ከደረስኩ በኋላም እንደተገነዘብኩት ግን፤ አልፎ አልፎ ተከሰተ ያሉትን በኢህአዴግ የተፈጸመ በደል በተለይ ከሳቸው መታሰር አንጻር ቢያነሱም፤ ብዙዎች እንደጓጉት (እኔ እንኩዋን ግድ የለኝም) ቀደም ሲል በነበረው የፖለቲካ ሕይወታቸው ውስጥ እንደኢህአዴግ ባለሥልጣን ሲሠሩ ለተፈጸሙ በደሎች በዝርዝር ይቅርታ የጠየቁበት ሁኔታ የለም። መቼም ነገር እንደተረጂው ነውና፣ እንዲያውም እኔ እንደተረዳሁት ስብሰባው ሌሎችን የከሰሱበት እንጂ፤ እሳቸው በግልጽና በዝርዝር ኃላፊነት የወሰዱበት አይደለም። እንደውም እንደውም ስላለፈው ሥራቸው ኃላፊነት ከመውሰድ አንጻር ከእስር እንደተፈቱ በአሜሪካ ድምፅ የተናገሩትን የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ያኔ የያዙትን በህወሓት ክፉ ሥራ ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ በትግራይ ተወላጆች ላይ ቂም ሊይዝ ይችላል የሚለውን አቋማቸውን አሁን በዘመድ አዝማድ ምክር ትተው ‘የትግራይ ህዝብም እስረኛ ነው! ተበድሏል! የትግራይ ተወላጆችም ቂም ለሕወሀት ጥፋት የተለየ ትብብር አላደረጉምና ቂም ሊያዝባቸው አይገባም!’ አይነት አቋም አንጸባርቀዋል።

በጥቅሉ ስለብሔራዊ እርቅ አስፈላጊነት፣ ስለፍቅርና ኢትዮጵያዊነት፣ ስላፍሪካው ቀንድ ችግር፣ ስለመጪው ትግል አስቸጋሪነት፣ ስለኢትዮጵያ ችግር ውስብስብነትና ሁሉንአቀፍ መፍትሔ ስለማፈላለግ፣ በውጭ ስለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የገንዘብና የፖለቲካ አቅም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው አደገኛ የፖለቲካ አፈና፣ በጋራ ስለመሥራትና የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች መመካከር አስፈላጊነት፣ ስለመገናኛ ብዙኀን አጠቃቀም፣ በኢትዮጵያ እውነተኛ ፌደራሊዝምና የብሔር መብት ስላለመኖሩ የተናገሩት መሬት ጠብ የማይል ቢሆንም፤ አንደኛ ነገር አቶ ስዬ ህወሓት የተመሰረተለት ዓላማ ስህተት ስለመሆኑ ምንም የተናገሩት ነገር የለም። እንዲያውም ችግሩ እነመለስ ጋር እንጂ ህወሓት ትክክል ነው የሚሉ ይመስላሉ።

ሁለተኛ እሳቸው በዚህ ስርዓት ላይ ያላቸው ተቃውሞ የመነጨው በተለይ ከኤርትራ ጦርነት መጀመርና ከሳቸውና ቤተሰቦቻቸው መታሰር ጋር ተያይዞ እንደሆነ አጥብበው ይናገራሉ። ሦስተኛ አቶ ስዬ ስላለፈው አንስተን እንድንወቃቀስና እንድንወያይ አይፈልጉም። አራተኛ ከምንም በላይ የመጀመሪያ ትግላቸው የወንድማቸው መፈታት እንደሆነ ይናገራሉ። አምስተኛ የኢትዮ-ኤርትራ ችግርም ይሁን፣ አሁን ኢህአዴግ ሶማሊያ ውስጥ የገባበት ጣጣ እውነተኛ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሆነ አድርገው ተናግረዋል (የኤርትራው ጉዳይ የድንበር፣ የሶማሊያው ደግሞ ኢህአዴግ የተጠቀመበት ስልት እንጂ በተቀረ ትክክል ነው ይላሉ)።

ስድስተኛ የኤርትራ ጉዳይ በሬፈረንደም ይፈታ ማለታቸውና አፈታቱም ትክክል እንደነበረ ይናገራሉ። ሰባተኛ እሳቸው አገር አቀፍ የሆነ ፖለቲካ ድርጅት ቢመርጡም፣ በብሔር መደራጀትን እንደሚደግፉም ተናግረዋል (ይሄ መጥፎ ነው ማለቴ ሳይሆን፣ ችግራችን ህወሓት ከመሆኑ አንጻር እንዲታይ ፈልጌ ነው)። ስምንተኛ እስር ቤቱን 99 ከመቶ የሞላው ኦሮሞ ነው ያሉትና በኋላ ላይ በጻፈው ጽሁፍ አቶ ፈቃደ ሸዋቀና ያጸደቀላቸውን አባባልም በበጎ አልተመለከትኩትም (የኦሮሞ ተወላጆችን በከፍተኛ ቁጥር መታሰር ለመግለጽ የሌላውን ብሔር እስረኛ ቁጥር መሻማት የለብንም። ይሄንን ቤቱ ይቁጠረው ለማለት ነው)።

ስለሠላማዊ ትግል፣ ስለትጥቅ ትግል እና ስለቅንጅት

አቶ ስዬ አልገፋበትም እንጂ ስለሠላማዊ ትግል ያላቸው አቋም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ የተደረጉትን ሰላማዊ ትግሎች የሚያጣጥልና የሠላማዊ ትግሉን በወራት ብቻ የገደበ ነው። አቶ ስዬ በሠላማዊ ትግል ብቻ እንደሚያምኑ ቁልጭ አድርገው መናገራቸው መልካም ነው። ነገር ግን ለዚህ ካቀረቧቸው ምክንያቶች ዋነኛው ሠላማዊ ትግሉ ገና መች ተሞከረና የሚለው አሳማኝ አይደለም። እንዲያውም የቅንጅትን ድል የስድስት ወር ትግል ብቻ ያደርጉታል። በመሰረቱ ቅንጅት የ2005ቱ ምርጫ ሊደረግ ሰሞን እንደ ቅንጅት ይቀናጅ እንጂ፤ በትንሹ የብዙ ኢትዮጵያዊያን የ16 ዓመት የትግል ውጤት እንደሆነ መዘንጋት የለበትም።

ቅንጅትን የመሰረቱት ድርጅቶች ባንድ ሌሊት ለምርጫ የተወለዱ ሳይሆኑ፣ የቀድሞው ስዬና ቡድኑ የሚደነቅርባቸውን ፈተናና መሰናክል እያለፉ፣ እየታሰሩና እየተፈቱ፣ እሞቱና እየተረገጡ ከዚያ የደረሱ ድርጅቶች ናቸውና የቅንጅና ሠላማዊ ትግሉ በስድስት ወር መተመን የለበትም። ይነስም ይብዛም እነስዬ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ እስከዚህች ሰዓት ድረስ ሠላማዊ ትግሉ – ሠላማዊ ትግሉን በሚያምኑበት ሰዎች እና ሠላማዊ ትግሉ በማይገባው ኢህአዴግ መካከል አለ። ስለዚህ የአቶ ስዬ ‘ሠላማዊ ትግሉ አልተሞከረም’ ትችት አያስኬድም። ስለሠላማዊ ትግልና ስለወንድማቸው መፈታት ከተናገሩት ውስጥ የተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ እሳቸው አሁንም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት ፍርድ ቤቶች የሚተማመኑ ይመስላል።

እንደግለሰብ ቢያንስ ወያኔን ወደ ድርድር ለማምጣትም ቢሆን፣ የትጥቅ ትግል አስፈላጊ ነው ብዬ ባምንም፤ የትጥቅ ትግልና በትጥቅ ትግል የሚመጣ ለውጥ የማይመልሳቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉና፤ ምናልባት ከትጥቅ ትግል ጋር በተያያዘ የተናገሩትና አቶ ስዬ በዕለቱ ሊጠቀሱላቸው ከሚችሉት ንግግሮቻቸው የማረከኝ፣ “የትጥቅ ትግልን የምትሉ ‘እኔን እዩ!’ …” ያሉት ነው። የኢህአዴግ ኢ-ዴሞክራሲያዊነት የመነጨው ወደ ሥልጣን ለመምጣት ከተጠቀመበት የትጥቅ ትግል ስልት ነው ይላሉ አቶ ስዬ። ኢህአዴግ ወታደርም፣ ጦር ሠራዊትም፣ የፖለቲካ ድርጅትም ነበር። በትግላቸው ሰዓት የሚከተሉት ወታደራዊ ስነስርዓት – የፖለቲካ ስርዓቱም ውስጥ ገባባቸው። ለምሳሌ፡- በወታደራዊ ሕግ እስኪ መጀመሪያ እንወያይና በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ወስነን ወደግንባር እንሂድ እስከዚያው ግን ውጊያ እናቁም አትልም። በወታደራዊ ሕግ ባትደግፈውም መመሪያውን ትቀበላለህ። ትፈጽማለህ። በወታደራዊ ስነስርዓቱና በትግሉ ወታደራዊ ግቡን መታን፤ ፖለቲካዊ ግቡን ግን አልመታንም ነው የሚሉት እሳቸው። አንዴ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ስር ሰዶ ስለገባብን፣ ከፖለቲካዊ ሕይወታችን ውስጥ ነቅለን ልንጥለው አልቻልንም አይነት ነገር። ስሜት ይሰጣል። ጸቡ ግን እሳቸው ይሄን ያስተዋሉት፡ ወይም ተከሰተ ያሉት እሳቸው ላይ ደረሰ የሚሉት ሲከሰት እንጂ፤ እስከዚያው ግን የሠሯቸው ሥራዎች ሁሉ መልካም እንደሆኑ ይመሰክራሉ። ለዚህም ወደኋላ ሄደን ሂሳብ አናወራርድ የሚሉት ነገር አላቸው።

መቼም የኛ ነገር የምንደግፋቸው ሰዎች ሲናገሩ በየጣልቃው ማጨብጨብ እንወዳለንና፣ ይሄንን “ሂሳብ አናወራርድ!” ቃለአጋኖ ሲያስቀምጡ በከፍተኛ ሁኔታ ተጨብጭቦላቸዋል። (በነገራችን ላይ ይሄ የጭብጨባ ጉዳይ ልናስብበት ይገባል። ባለፈው ዓመት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ባደረገው የአንድ ሰዓት ተኩል ስብሰባ ውስጥ ወደሀያ ምናምን ግዜ ተጨብጭቦለታል። ጭብጨባ ትኩረት ሊሰጣቸውና ሊመረመሩ የሚገባቸው ነጥቦች ተለባብሰው እንዲያልፉ የሚያደርግ አካሄድ ነውና ሊመጠን ይገባል።)

ስላለፈውና ስለመጪው – “ታሪክን የሚረሱ ስህተታቸውን ይደግማሉ” አይነት ነገር

አሁን የተሰበሰብነው ስላለፈው ለመነጋገርና በራሳቸው አንደበት ደጋግመው እንደተናገሩት “ሂሳብ ለማወራረድ” አይደለም ብለው ከኢህአዴግና ከሳቸው ጥፋት አንጻር የሚነሱትን ጥያቄዎች በውይይቱ ላይ ሁሉ ዘወር እያደረጓቸው አልፈዋል። ለምሳሌ በሳቸው አገዛዝ ዘመን ከወሎና ጎንደር መሬት ተቆርሶ ለትግራይ ስለመሰጠቱ እና የተወረሱ ቤቶች ለትግራይ ተወላጆች ሲመለሱ፤ በትግራይ ይኖሩ ለነበሩ የአማራ ተወላጆች አለመመለሱን በተመለከተ ሲጠየቁ፤ … አሁን የተሰበሰብነው ስለዚያ ለመነጋገር አይደለም፣ እሱን አታንሱ … ብለው አልፈውታል። በዚህም ትኩረት መደረግ ያለበት ስላለፈው ጥፋትና ስህተት እያነሱ በመነጋገሩ ላይ ሳይሆን፣ ስለወደፊቱ በመወያየት ላይ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። ስላለፈው መነጋገር የለብንም እንዴ? በርግጥ እሳቸውን ሀጥያታቸውና ጥፋተኝነታቸው ገዝፎ እንዲሰማቸው በሚያደርግ መልኩ፣ በመወቃቀስና በመነታረክ እንዲሁም ለወደፊቱ አንድ ላይ እንዳንሰለፍ በሚያደርግ መልኩ ስላለፈው አንስተን እንውቀሳቸው አልልም። ይሁን እንጂ ያለፈው ስህተታችን ምን ነበር? የቱ ጋር ጠፋ? የቱስ ጋር ነገሮች ተበለሻሹ? በሚለው ላይ ካልተወያየን፤ ነገሮችን አድበስብሰን ማለፉ ብዙ ይጎዳናል። ጎድቶናልም። ቅንጅትን አሁን እያንገላታው ያለው ትናንት ከትናንት ወዲያ የተሠሩ ስህተቶችን እየሸፋፈንን ማለፋችን ነው። ይሄ ያለፉትን ስህተቶች አንስቶ መወያቱ ብዙ ጠቀሜታ አለው። በተለይ ግን ዘወትርም የተቃራኒ ወገንን ትንታኔ መስማት ራስን ከባላንጣ አንጻር ለማዘጋጀት መልካም ነውና፣ በሳቸው ዘመን ተሠሩ ስለሚባሉ ስህተቶች አንስተን ብንወያይ እውነተኛውን የኢህአዴግን ባህርይና መልክ እንድናውቅ፣ ራሳችንንም ከዚያ አንጻር እንድናዘጋጅ ይረዳናል።

እኔ የዚህ ጽሁፍ ፀሐፊ፣ “የኢትዮጵያ ህዝብ … የኢትዮጵያ ህዝብ” እያልኩ እንዳልናገር የኢትዮጵያ ህዝብ ውክልና የለኝም። ነገር ግን ብዙ ኢትዮጵያውያን ኢህአዴግን ከመጥላታቸውና ከኢህአዴግ ምንም እውነት እንደማይገኝ አጠንክረው ከማመናቸው የተነሳ፣ የኤርትራ ቴሌቪዥንና ሬድዮ ሲያዳምጡ፤ እኔ አቶ ስዬ መጥተው ኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ላይ የሰለቸኝን የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ እንዲደግሙልኝ አልፈልግም። ለምሳሌ የኤርትራን መንግስትን በተመለከተ የተናገሩትን እንውሰድ። አቶ ስዬ የኤርትራን ሽብርተኝነት የተናገርነው ገና የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሳያልቅ ነው ይላሉ። በዚያው ልክ ግን የኤርትራ ነጻ መውጣት ትክክለኛ ፖለቲካ ውሳኔ እንደሆነ ይናገራሉ። መቼም የኤርትራ ጉዳይ ያከተመለት ቢሆንም፤ አሁንም ትግራይን ነጻ ለማውጣት የተቋቋመበትን ዓላማና ስም ያልለወጠ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ አመራር ሆነው ያገለገሉ ሰው ከመንደራችን መጥተው እንወያይ ሲሉ፣ በሳቸው ዘመን ስለተላለፉ አንገብጋቢ ውሳኔዎች ሁሉ አንስተን መወያየት የምንደራደርበት ጉዳይ አይደለም። ከዚህ አንጻር እኛ ስርዓት ባለው መልኩ እስካቀረብነው ድረስ፣ አቶ ስዬ ሂሳብ ማወራረድ አያስፈልግም ብለው የሚዘሉት የፖለቲካ ጥያቄ ሊኖር አይገባም። ከአቶ ስዬ ከምንም በላይ የምንፈልገው የኢህአዴግን እውነተኛ ባህርይና ማንነት እንደቀድሞ የኢህአዴግ ባለሥልጣን ማጋለጥ ነው። ያለበለዚያማ እኛ ስንል የነበረውን ቢደግሙልኝ፣ መርጠው መርጠው እሳቸው የሚፈልጉትን ብቻ ቢያወሩልኝ ምን ጠቀመኝ? ከዚያ ወደ ትግራይ ህዝብ ተመልሰው የተናገሩት ለመቀበል የሚያዳግት ነው።

ስለትግራይ ህዝብ፡- “የትግራይ ህዝብ የሚናገርለት ያጣ ህዝብ”?

ይህን ያልኩት እኔ አይደለሁም። አቶ ስዬ በውይይታቸው ውስጥ ሁሉ የትግራይም ህዝብ በዚህ ስርዓት እንደተበደለና ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚለየው ምንም ነገር እንደሌለ ይናገራሉ። የትግራይ ህዝብ መጫወቻ ነው የሆነው። የትግራይ ህዝብ የሚናገርት ያጣና የታፈነ፣ በእንግሊዘኛ ደግሞ “demobilized” ህዝብ ነው ይላሉ። የዚህ የትግራይ ነገር ዘወትርም እንዳነታረከን ሊዘልቅ ነው። እንግዲህ መቼም በዚህ ዘመን ነገሮችን በፍጥነት መርሳት ልማድ ሆኗልና ካልዘነጋሁት በስተቀር፣ በዚህ አስራ አምስት ዓመት ውስጥ ከመሀል አገር ሄደው ካልሆነ በስተቀር ተቃዋሚዎች ታሰሩ፣ ተቃዋሚዎች ተገደሉ፣ ተቃዋሚዎች ተሰለፉ፣ ኢህዴግን አወገዙ የሚባል ዜና ከአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጪ ያልሰማሁበት ክልል ትግራይ ነው። የትግራይ ህዝብም እስረኛ ነው አይነት ጨዋታ ከቶም አልገባኝም።

የትግራይ ህዝብ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር ይህንን ስርዓት በመቃወም የሚያሰልፈው ምን ችግር አለበት? የተቀረው ኢትዮጵያዊ ልጆቹ ሞተውበታል፣ ታስረውበታል፣ አፈናና ግድያን ፍራቻ ተሰደውበታል፡፡ በዚህ አስራ ስድስት ዓመት ውስጥ በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት ወይንም ሰልፍ ወጥቶ ተሰልፎ ወይንም ስርዓቱን ተቃውሞ በመውጣቱ ምክንያት የተገደለ የትግራይ ተወላጅ ስለመኖሩ ማስረጃ የለኝም።

በመሰረቱ የትግራይን ህዝብ በዚህ ስርዓት ላይ የሚያሰልፍ ምን ምክንያት አለ? የኢትዮጵያ ህዝብ (ትግራይንና አብዛኛውን የትግራይ ተወላጆች ሳይጨምር) በየዓመቱ ሰልፍ እየወጣ የተገደለው የሰልፍና ፍልሚያ ሱስ ኖሮበት ወይንም ሰልፍና መንግሥትን መቃወም ሆቢው ሆኖ አይደለም። የሚያንገሸግሽና አደባባይ የሚያስወጣ ብሶት ፈንቅሎት እንጂ። ስለዚህ ጥያቄዬ የሚያስከፋ ብሶትና ምሬት ቢኖርበት ኖሮ፣ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ በየወቅቱ የኢህአዴግን ግድያ እየተቋቋመ ተቃውሞ እንደሚወጣው ሁሉ፤ የትግራይም ህዝብ ያንን ያደርግ ነበር። ስለዚህ ይሄ የትግራይም ህዝብ እስረኛ ነው አይነት ሙግት ብዙ አያሳምንም። ያ ማለት ግን የትግራይ ህዝብ ደስተኛ ነው ወይም ለኢህአዴግ ሥራ ተጠያቂ ነው ከማለት ተለይቶ መታየት አለበት። ይሄንን ጽሁፍ በማረም እንዲተባበረኝ የሰጠሁት አስተዋይ ወዳጄ፡ “የትግራይ ህዝብ ስትል በክልሉ የሚኖረውን ለማለት ነው ወይንስ በሌሎች ክልሎችም የሚኖሩትን ለማለት ነው? እንደገባኝ ከሆነ የትግራይ ክልል የሚኖሩትን የትግራይ ተወላጆች መሆን አለበት። እንዲያ ከሆነ አንዳንድ ቃላቶች ጨምርበትና ስፔሲፋይ አድርገው። ቅንጅትን አዲስ አበባ ላይ የመረጡት የትግራይ ተወላጆች አሉም አይደል።” ተቀብዋለሁ። ስለዚህ በዚህ በትግራይ ጉዳይ ላይ ይሄ ጓደኛዬ ያከለበትን አክላችሁ አንብቡት። ተርጉሙት። ይሄ የትግራይ ነገር፡ ራሱ ሕወሐት እንዳመጣው ካልወሰደው በስተቀር በዚህ ጽሁፍ ካብራራሁት በላይ ላብራራው አልችልም።

በመሰረቱ ያንድ ህዝብ ደስተኛነት የሚወሰነው በዲሞክራሲ መኖር አለመኖር ብቻ አይደለም። ለምሳሌ አሜሪካንን ወይም አውሮፓን ውሰዱ። በነዚህ አገሮች ዲሞክራሲ ስላለ የአሜሪካና የአውሮፓ ህዝብ ደስተኛ ነው ማለት አይደለም። የዚያን ህዝብ ደስታ የሚወስኑት ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ለምሳሌ ኢኮኖሚው ነው። በአሜሪካ ውስጥ አስተማማኝ የጤና አገልግሎት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር አያሌ ነው። በአሜሪካ ውስጥ ከወር እስከወር በመከራ የሚደርሱ በዝቀተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ድሆች ቁጥር ብዙ ነው።

ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ባይደሰት ምንም ለነሱ የሚቆረቆርና በሌላው ኢትዮጵያዊ ኪሳራ እነሱን ለማስደሰት የሚተጋ መንግሥት ቢኖርም፤ ዞሮ ዞሮ የዚህ መንግሥት አቅም የሆነ ቦታ ላይ ይወሰናልና ሁሉንም የተመኙትን ሁሉ ሊያገኙ አይችሉም። ከዚያ በተረፈ ግን እንዳንድ ፀሐፊዎች እንደሚያደርጉት እኛ የላቸውም ብለን ካልጫንባቸው በስተቀር፤ የትግራይ ህዝብ የተቀረው ህዝብ እንደተከፋበት በልጆቻቸው የቆመውን ይሄንን መንግስት የሚያስጠላና የሚያስቀውም አጥጋቢ ምክንያት የላቸውም። ከዚህ አንጻር አቶ ስዬ ይሄ ጸጥ ብሎ እርከኑንና ግድቡን፣ የመሰረተ ልማት አውታሮቹንና መንገዶቹን፣ ሥልጣኑንና አገዛዙን እያጠናቀረ ያለ የትግራይ ህዝብም ከኢህአዴግ አገዛዝ ነጻ አውጪ የሚፈልግ ህዝብ ነው የሚሉት ነገር የማይመስል ነው። ለትግራይ ህዝብ ከህወሓት የተሻለ ነጻ አውጪ መጥቶ አያውቅም። ሊመጣም አይችልም። ለማንኛውም እሳቸው የትግራይ ህዝብ ያምነኛል፣ ይሰማኛል፣ ያውቀናል ያሉት ነገር አለና፤ በዚህ ረገድ የትግራይ ህዝብ እሳቸውን ሰምቶ የተነሳ ዕለት ለመታረም የተዘጋጀሁ ነኝ።

እንደመደምደሚያ – እንደማሳሰቢያም

አቶ ስዬ ብዙ ይቀራቸዋል። ብዙ የሚናገሩበት ዕድልም ልንሰጣቸው ይገባል። ዞሮ ዞሮ ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ እሳቸውም እንዳሉት ችክ ማለታቸው አይቀርም። በቀጣዮቹ ስብሰባዎቻቸው፣ ስለህወሓትና ዓላማው፣ ስለኢህአዴግና ሥራው፣ ቀደም ሲል ስለተሠሩ ጥፋቶችና አሁን መከተል ስለሚገባን መንገድ፣ ስለኢትዮጵያ አንድነትና ስለብሔረሰቦች ነጻነት ያላቸውን አመለካከት ጥርት አድርገው ሊያስረዱን ያስፈልጋል። ከላይ እንደጠቀስኩት እሳቸውን ጥፋተኝነት እንዲሰማቸው ለማድረግ ሳይሆን፤ የሚመጣውን ሥራ በመተማመንና ያለጥርጣሬ እንድንሠራ የሳቸው ከዚህ በፊት በተደረጉት ነገሮች ላይ ግልጽ ሆኖ መምጣት/መውጣት ወሳኝ ነው። አቶ ስዬ የድሮውን ህወሓታዊ አስተሳሰብ በአዲስ ኢትዮጵያዊ ጨርቅ ሸፋፍነው ይምጡ፤ ህወሓታዊ አስተሳሰባቸውን ትተው እውነተኛ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ይዘው ይምጡ ልናውቅ የምንችለው በሂደት ነው። እስከዚያው ግን በትህትናና በስርዓት እስከቀረበ ድረስ በሚያደርጉት ውይይት ላይ ሁሉ የሚሸሹት ጥያቄና አስተያየት ሊኖር አይገባም። የትግራይን ተወላጆች ጉዳይ ግን እመለስበታለሁ። እስከዚያው ግን፡ ይሄ ሕወሐት የተያያዘውን የትግራይ ተወላጆችን በኢኮኖሚ፡ በስልጣን፡ በትምህርትና፡ በመሳሰሉት ነገሮች በተቀረው ኢትዮጵያዊያ ላይ የመጫንና አገዛዙን ለዘመናት ለመትከል ተግቶ የመስራት ዘመቻ ሁላችንም አጢነን፡ ልንወያይበት፡ ልንቃጠልበትና ሰላም ሊነሳን የሚገባ ጉዳይ ነው።

ተስፋሚካኤል ሳህለስላሴ፡ ካናዳ