ከአቶ ምትኩ ይመር ለቀረበ ጽሁፍ የተሰጠ ምላሽ

ከሙታን ሰፈር ከሚሰማ የቅኔ ዘረፋ ይልቅ የሕያው አምላክን ተግሳጽ መርጠናል

ከአቤል ጋሼ

[pdf]

(“ሥልጣነ-ክህነት የቂም መወጫ በትር አይደለም” በሚል ርዕስ ከአቶ ምትኩ ይመር ለቀረበ ጽሁፍ የተሰጠ ምላሽ)

አቶ “ምትኩ ይመር” የተባሉ የዋሽንግቶን ዲ.ሲ ነዋሪ በሰሞንኛው “(“ሥልጣነ-ክህነት የቂም መወጫ በትር አይደለም”) በሚል ርዕስ ባስነበቡን ጽሁፋቸው በአሜሪካን ሀገር በሜሪላንድ ክፍለ-ግዛት፣ በቴምፒል ሂል ወረዳ በደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ሁለት የቤተ ክርስቲያኗን ታዋቂ ሰዎች ማለትም የእናታችን የወ/ሮ ውድነሽ አምሳሉንና የቀሲስ መምህር ዘበነ ለማን ስሞች ጠቅሰው በእሳቸው አስተሳሰብና፣ ቁጣና በቀል በተመላ ስሜታዊነት የሚያውቁትንና የመሰላቸውን የሞት ቃላቸውን ሰብከውናል፣ የቤልሖር መንፈስ የሞላው የጠብ ግብዣቸውን ጋብዘውናል፣ በልዩነትና ባለመግባባት እንድንተራመስ በራዕይ 6 የተጠቀሰውን ዓይነት ባለጥቁር ሰንደቅ የሀመር ፈረሳቸውን እየጋለቡ ፊታውራሪ ሆነው ለጦርነት ሊያሰልፉን “ሳይቃጠል በቅጠል” በሚል ቋንቋ በአዝማችነት ተነሳስተዋል። ጽሁፉ ለኢትዮጵያውያን ስለሚሰጠው ማህበረሰባዊ ጠቀሜታ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክርስቲያን ያለባትን ፈተና ለማቃለል የሚኖረው አስተዋጽኦና ‘እውነትን እፈልጋለሁ” ከሚል፣ የሀገር ተቆርቋሪ ተዘግቦ እንደሆነ አንባቢ ሁሉ በራሱ አስተያየትና ሚዛን እንዲመዝነው እተዋለሁ። ሆኖም አንባቢው ለመመዘን እንዲችል ብዬ በማሰብ በተወራው ጉዳይ ላይ ብርሃን የሚፈነጥቅ የአጸፋ መልስ እንደሚያስፈልገው አምኜበታለሁ። ለዚህም ያነሳሱኝ ቢያንስ ሶስት አበይት ምክንያቶች ስላሉ እነሱን ልግለጽ።

1ኛ) አቶ “ምትኩ ይመር” በደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተፈጠሩ ያሏቸው ክስተቶች ተፈጸሙ በተባሉበት ወቅት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር ውስጥ አገልጋይ ሆኜ እሰራ ነበር።፣ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ስብሰባ አደረጉ በተባለበት ወቅት ስብሰባውን በመምራት በቀጥታ በጉዳዩ ውስጥ ስለተሳተፍኩ የጠቅላላውን ጉዳይ አስተዳደራዊ ነክና መሰረታዊ የክስተቶችን አንኳር ጉዳዮች ሁሉ በቦርድ ጸሐፊነቴ ከሞላ ጎደል እውቅና ነበረኝ። ስለዚህም የገጠመኞችን ግራና ቀኝ ለመመልከት እድልም ስላጋጠመኝ እንዲሁ በጥራዝ ነጠቅነት፣ “እውነት”ና “ሰላም” በአደባባይ እንደ ሰንጋ ሲታረዱ ስመለከትና ትክክል ባልሆነ ወሬና አሉባልታ ሕዝብ እንዲተራመስ፣ ሰላም እንዲጠፋ፣ የኢትዮጵያውያንን የህብረት ተስፋ የበለጠ እንዲቀብጽ የሚያደርግ መልዕክት ያዘለ ጽሁፍ በዘመኑ የድረ-ገጽ መስኮት ተበትኖ ስመለከት፣ “ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይመስክር የነበረ” እንዲሉ አስፈላጊውን መረጃ ለአንባብያን በማቅረብ ስለሚገባው ነገር መስክሮ የተሰነዘረውን የሰብቅ ጦርነት በእምነት ጥሩር መመከትና መፋለም አስፈላጊ መሆኑን ስላመንኩበት ነው።

2ኛ) በሁለተኛ ደረጃ ዛሬ (ጉዳዩ ከተፈጸመ ከ6 ወር በኋላ) በእግዚአብሔር የተባረከ የሰላም መንፈስ በቤተ ክርስቲያናችን እንዳለን የደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ምዕመናን የምናምነውና በግልጽ የምናየው ነገር ነው። አልፎ ተርፎም አቶ “ምትኩ ይመር” ከጠቀሱት ገጠመኝ ወዲህ በርካታ ለቤተ ክርስቲያናችንንና ለሌሎችም የሚጠቅሙ ጉዳዮች በቤተ ክርስቲያናችን እየተፈጸሙ መሆኑ በግልጽ የሚታይበት፣ የቤተ ክርስቲያኗ ጠቅላላ ሰላምና አካሄድ በአይነቱ የላቀ መሆኑ በአብነት የሚጠቀስና ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ከቤተ ክርስቲያኗ አሰራር ሊማሩ የሚያጠይቁበት ወቅት ነው። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን ይኸንን የመሰለ ዕቡይ መንፈስ የተጠናወተው ጽሁፍ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚተላለፍ ድረ-ገጽ ላይ አስፍሮ የግለሰቦችን፣ የቤተ ክርስቲያናችንንና አልፎ ተርፎም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ክብርና ገመና በአደባባይ ለአፈርሳታ ማውጣት በግለሰብ ላይ የተቃጣ ይምሰል እንጂ የኦርቶዶክስ አማኝነትንና የኢትዮጵያዊነትን ክብርና መንፈስ የሚጻረር ስለሆነ እንዲህ እውነታውን አንጋዶና በውሸትና በአሉባልታ በክሎ “ድንጋይ ዳቦ ነው” የሚል ሲመጣ ዝም ማለት ሕሊና ስለሚቆጠቁጥና በተለይም ባለማወቅ ከሙታን ምድር የተላኩ ደብዳቤዎችን አንብበው ውዥንብር ውስጥ የሚገቡ ወገኖች ሊኖሩ ስለሚችሉ በጉዳዩ ላይ ብርሃንን መፈንጠቅና የአቶ “ምትኩ”ን ጽሁፍ ማህበራዊ እሴቱን ማሳየት ለማህበረሰባችን የሚጠቅምና፣ የቤተ ክርስቲያናችንንም ክብር መጠበቅ የሚራዳ እንደሆነ ስላመንኩበት ነው።

3ኛ) በጠቅላላው ዛሬ የኢትዮጵያና የልጆቿ ፈተና ከምንጊዜውም በላይ ከፍቶ፣ በሀገራችን ረሀብ፣ በሽታ፣ የአስተዳደር መዛባት፣ ወዘተ.. ወገኖቻችንን በሚፈትንበት ወቅት እያንዳንዳችን እጅ ለእጅ ተያይዘን በሰከነ አእምሮ፣ በቀና መንፈስ፣ የልዑል እግዚአብሔርን ታጋዥነትን ተማጽነን ወደ ብርሃኑ ጎዳና መጓዝ ሲኖርብን “ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሉ በየቀኑ የምናነበው ጽሁፍ፣ በሬዲዮ ሞገዶች የምንሰማው አብዛኛው ሁካታ የክፋት፣ የሀኬት፣ የሰውን ስብዕና የማጣጣልና የማንቋሸሽ መሆኑን እያየሁ ከልብ አዝናለሁ። ታዲያ ምንም እንኳን ስለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የጠለቀ ዕውቀት ባይኖረኝና፣ ስለ ስነ መለኮት ሂስ ለመስጠት ችሎታው የሌለኝ ቢሆንም፣ ግን ኢትየጵዊነቴና፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይነቴ እያስገደደኝ እንዲህ በሕዝብ ዓይን ላይ የበርበሬ ዱቄት የሚበትን ዓላማ ያለው ጽሁፍ ሳነብ ስለጉዳዩ በቅርብ የማውቀውን በመንተራስ መልስ መመለስ እንዳለብኝ ግዴታ ተሰምቶኝ ነው። በተለይም ከሙታን ሀገር በሚላኩልን ደብዳቤዎች የሚተላለፉ የክፋትና የአሉባልታ ዝባዝንኬዎችን እየተመረዝን በመካከላችን ሰላምን ስላጣን፣ የሀገራችንንም ትንሳዔ እየራቀብን ስለመጣ፣ በኢትዮጵያዊነት ስም “እባካችሁ ገንቢ በሆነ ጉዳዮች ላይ እንነጋገር፣ መሰዳደብ፣ መዘላለፍ፣ ሰዎችን አውርዶ መጣልንና፣ የሰዎችን ስብዕና ዱቄት ማድረግ፣ አልፎ ተርፎም የማናውቀውን ነገር ቀነጣጥበን በወሬ የ”ባቢሎን ግንብ” እየሰራን የሞት አዝመራ ማዝመሩን ይብቃን፣፡ ይልቅስ አባቶች ያወረሱንን የኢትዮጵያዊነት አብነት ማለትም ስለሕያውነት፣ ሰውን ስለማዳን፣ ስለ መልካሙ፣ ስለቀናው ጉዳይ፣ ስለይቅርታ፣ በብርሃን ስለመመላላስ፣ ስለመማርና ጥበብን ስለመገብየት እንሽቀዳደም” ብዬ ለወገኖቼ የዜግነት ጥሪ ለማስተላለፍና ይኸንን የሚያሳዝን አጋጣሚ ቢያንስ የምንማማርበትና ወደፊት ከተመሳሳይ ማህበራዊ ዝቅጠት ውስጥ እንዳንወቅድ የምንመለከትበት ጥሩ መነጽርና፣ አስረጅ መጠቀሜ ነው።

ለ. በጽሁፉ ስለቀረቡት ግለሰቦች።

1ኛ. እናታችን እማማ ውድነሽ አምሳሉ፦ በእውነት እኒህ እናት ታላቅ ኢትዮጵያዊና የሀገር አንጡራ ሀብት ናቸው። ጸሀፊው በጽሁፋቸው ስለእኒህ ግለሰብ ማንነት ካሰፈሩትም በላይ እናታችን አንደበተ ርቱዕ፣ የውስጥ ነጻነትን የተቀዳጁ፣ የሚመስላቸውን የሚጠይቁ፣ እውነትን ለማግኘት፣ የእምነት ትጥቃቸውን ታጥቀው፣ የእውነትን ጦር በተገኘው ሁኔታ ከመስበቅ ወደ ኋላ የማይሉ፣ በመምሰል ካባ ተጀቡኖ በሚኖር አለም ውስጥ ራሳቸውን ሆነው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው። እንደ እውነቱም እማማ ውድነሽ ኢትዮጵያውያን በበለጠ ለያውቋቸው የሚገባ የጠለቀ የመንፈሳዊና የአለም እውቀት ያካበቱ የነጠሩ ምሁር፣ ታላቅ እናት፣ የቤተክርስቲያናችን ዋልታ፣ መካሪ፣ ዘካሪ ናቸው። ስለኢትዮጵያ ያላቸው መቆርቆር፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያላቸው ቀናኢነት፣ ወጣቱ ትውልድ ሊማረው የሚገባ ሲሆን ደከመኝ፣ ታከተኝ ሳይሉ ወገንን ለመርዳት፣ የአለም ፈተናና ዕድሜ ሳያግዳቸው በነፍስ አድን የወገን ጥሪ፣ ለልጆች ተስፋ ለመሆን፣ በቤተ ክርስቲያን ደህንነት ዙሪያ፣ በደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም መጠንከር አቢይና ለተቀባይ ትውልድ የሚዘከሩ ጉልህ ስራዎችን የሚሰሩ እናት ናቸው። በዚህ ሁኔታ በሚያደርጉት ሁሉ የሚመለከተውና ኣርኣያ የሚሆነው ላጣው ትውልድ ተምሳሌት የሚሆኑ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው። የዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያውያን አለመታደላችን ከሚገለጽበት አንዱ መንገድ እንደዚህ ያሉ ሊመክሩንና ሊገስጹን የሚችሉ እናቶችንና አባቶችን እየቀረብን አውቀናቸው ከአንደበታቸው የሚገኘውን ፍሬ ከናፍር አዳምጠን መማር ጥበብን መገብየት አለመቻላችን ነው። ሲነግሩንም አናዳምጣቸውም። ልዑል እግዚአብሔር እናታችንን በጤንነት፣ በዕድሜ በጸጋ ይጠብቅልን!

2ኛ. መምህር ቀሲስ ዘበነ ለማ፦ በደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ናቸው። ጸሀፊው አቶ “ምትኩ” ኢትዮጵያዊና ክርስቲያናዊ ትሕትና በጎደለው አጻጻፍ “ዘበነ” እያሉ በስድና በብልግና አጠራር እንዳቃለሏቸው ሳይሆን መምህር ቀሲስ ዘበነ ለማ በወጣትነት ዕድሜያቸው “አንቱ” መባልን ያተረፉ፣ በወንጌል ገበሬነታቸው ብዙ ሺ ወጣቶችን ወደ ሕያው ጎዳና መልሰው በክርስቶስ የመዳንን ተስፋ ያስጨበጡ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የህይወትን ቃል የሚዘሩ፣ በደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም መንፈሳዊ ጉባዔ ውስጥ ካላቸው ሃላፊነት ባሻገር በሁለት የተለያዩ ቦታዎች (በአሌክዛንደሪያ፣ ቨርጅኒያና በሲልቨርስፕሪንግ ሜሪላንድ) የወንጌል ስብከት የሚሰጡባቸው ወንበሮች ዘርግተው ለብዙ ሺ ወጣቶች የመንፈስን ትጥቅ የሚያስታጥቁ፣ በቤሪያ ጉባዔ የወንጌል ትምህርት ለብዙዎች የነፍስ ምግብ እየሰጡ የኮተኮቱ፣ እንዲሁም ዛሬ በክርስቶስ ተከታዮች ላይ ከጨለማው ሰፈር በተለያዩ ሜዲያዎች የተቃጣውን ነፍስን የሚሰቅዝ ከፍተኛ የሆነ የመንፈስ ጦርነት ለመዋጋት በሬዲዮና በኢንተርኔት የወንጌልን ስብከትን እያካሄዱ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና ለአማኞቿ አለኝታና በመሆን ስማቸውንና አንገታቸውን በአደባባይ አውጠው ሰጠው ራሳቸውን በመንፈሳዊ እስጢፋኖስነት አቅርበው ሰማዕት እየሆኑ ያሉና ከየአቅጣጫው በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚዘምቱ የሞት ፊታውራሪዎችን የሚፋለሙ ዕንቁ የቤተ ክርስቲያን ልጅ፣ የሚመኩባቸው፣ የሚያኮሩ ኢትዮጵያዊ የመንፈስ ወንድም ናቸው።

መምህር ዘበነ ዛሬ ከምዕራቡ ዓለም በሚመነጩ የእምነት ሰደዶች ከፍተኛ የሆነ ጥቃት እየተሰነዘረባት ያለችዋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ የነፍስ ጥሪ ሆኖባቸው ከላይ ታች የሚማስኑና የሚደክሙ፣ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በምድረ በዳ ከሚጮሁ እፍኝ የማይሞሉ ወጣት ወንጌላውያንና ሰባኪያን አንዱ ናቸው። በርግጥም የጎደለውን ከመቁጠርና የግለሰቡን ስብዕና ከማጥቆር፣ የሞላውንና ያደረጉትን ሙከራ ለሚመለከት መምህር ዘበነ ለኦርቶዶክስ አማኞች ባለውለታ ናቸው። አሁንም እኒህን ታላቅ ወጣት መንፈሳዊ መሪ በዕድሜ፣ በጤና ጠብቆ፣ በመክሊታቸው ላይ መክሊትን አብዝቶ፣ ለኛም የበለጠ እንዲመግቡን፣ ለሳቸውም የበለጠውን ሰማያዊ የድል አክሊል እንዲያጎናጽፍልን ሁሉም ነገር የማይሳነውን ቸሩን መድኃኔ ዓለምን እማጸናለሁ፡፡ እኒህ መንፈሳዊ አባት ለቤተ ክርስቲያኑ በሰጡት ላቅ ያለ አገልግሎት ከቤተ ክርስቲያኗ ምዕመናን በተመረጡ ታላላቅ አባቶችና እናቶች ተመርጠው ለላቀ አገልግሎት ዕውቅና ካገኙ አራት ካህናት ውስጥ አንዱ መሆናቸውን መገንዘብ ከፈለጉ ከ2007-2009 በስራ ላይ የነበረው የባአደራ ቦርድ ለአባላቱ ባቀረበው የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ሊመለከቱ ይችላሉ። በነገራችን ላይ መምህር ዘበነ እንደ ሁላችንም የሚሳሳቱ ሰው ናቸው፣ ይኸንንም ስለሚያውቁ በግልም ይሁን በአውደ ምህረት ላይ ለሰራሁት፣ ለበደልሁት “ይቅር በሉኝ” ብለው ይቅርታን የሚጠይቁ፣ ይቅርታን የሚያስተምሩ፣ መክሊታቸውም እንደ መጽሐፉ አባባል “30፣ 60፣ 100” የሚሆን ያማረ ፍሬ የሚይዝላቸው መምህር ናቸው።

3ኛ. ጸሀፊው አቶ “ምትኩ ይመር”፦ “ምትኩ ይመር” በሚል ስም የሚታወቁ በደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አባል የሉም። የተጠቀሱት ጉዳዮች ሲፈጸሙና ሲነገሩ በአባልነት ተሳትፈው ጉዳዩን የተከታተሉና የሚያውቁ ግለሰብ አልነበሩምም፣ የሉምም። እንደመሰለኝ ጸሀፊው የብዕር ስም ተጠቅመው እነደጻፉት አስባለሁ። በእውን በዚህ ስም የሌሉ ግን በብዕር ስም ተደብቀው የሚጽፉ ከሆነ ከወዲሁ የጻፉበት አላማና ሊያስተላፉ የሞከሩት መልዕክት ሁሉ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ምክንያቱም መደበቁ የፍርሃትና የሸፍጥ ብሎም የሸንጎኛነት ምልክት ስለሆነ ነው።
የብዕር ስም በሥነ-ጽሁፍ አለም ውስጥ ለጥቅም የሚውልበት የራሱ ምክንያት አለው። የስነ ጽሁፍ አለም እውነትንና የፈጠራን ስራ ስለሚያካትት የብዕር ስም ደራሲያን ቢጠቀሙበት ስራቸው ፈጠራም ስለሚኖርበት ተቀባይነት ያለውና አንዳንዴም ገበያቸውን ለመጨመር ነው። እውነት አርነት ታወጣሃለች የሚል ሀይማኖት ለሚከተልና እውነትን ለሚሻ ጸሀፊ ግን ብርሃኑን ሸሽቶ ከጨለማ አምባ ስሙኝ ማለት ይቸግራል። እንደገባኝ ጸሀፊው “ምትኩ ይመር” የሚል የጨለመ ትንቢትን የተሸከመ ስም ያወጡት ካስተላለፉት መልዕክት አንጻር የመምህር ዘበነ ለማን ከደብረ ገነት መነሳትና በሌላ መተካት አጥብቀው ስለሚመኙ “በሱ ምትክ የሚመጣው ይመርልን” በሚል ከንቱ የልባቸውን ፍላጎት በውስጠ ታዋዊነት ማስደመጣቸው ይመስለኛል። ተሳስቼ ከሆነ ይቅርታ እየጠየቅሁ “ምትኩ ይመር” በሚል ስም የሚታወቁ በእውን ታውቀው የሚኖሩ ግለሰብ ካሉ በክርስቶስ ወንድም አድርጌ የማከብርዎ፣ መሆኑን እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ። ይኸንን የአጸፋ መልስ እንድሰጥዎ ያስገደደኝ ያስነበቡን የጭንቀትና የጠብ ድግስን የሚነግር ደብዳቤ በ”ሀመር ፈረስ” ተጭኖ የመጣ ከሙታን ምድር የተቀኘ ያልተዋጣለት ቅኔ ሆኖ በጥላቻና በክፍፍል መንፈስ ተሞልቶ ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዝኖ ስላየሁትና እኩይነቱ ስለሚያውክና ስለሚያስተክዝ ብሎም ወደ ነፍስ ውስጥ ገብቶ ስለሚመርዝ ለአንባቢያን የጽሁፉን ማህበራዊ እሴትና ጠቀሜታ መመዘን የሚያስችላቸው ተጨማሪ መረጃ ለማቀበል ነው። በዚህ አጋጣሚ የደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ምዕመናን በይቅርታ መንገድ ወደ ሕያዋንን ሀገር መጓዝን መርጠን፣ በይቅር ምንተእግዚአብሔር ፍቅርን ተላብሰን የሰላም የወይን ፍሬ እየተመገብን መሆኑን አቶ “ምትኩ ይመር” እንዲያውቁትም ለመግለጽ እፈልጋለሁ።

ሐ. መታረም የሚገባቸው አቢይ ስህተቶች
1ኛ. ጸሀፊው በጽሁፋቸው ላይ በደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም የአባላት ስብሰባ ላይ እናታችን እማማ ውድነሽ “….በስብሰባው ላይ ልትገኝም አይገባህም፣ በነጻነት እንወያይበት” ብለዋል የሚል ሀረግ አስቀምጠዋል። በቅድሚያ የተከበሩ እናታችን ይኸንን አላሉም፣፡ “ይኸን አልሽ ተባለ” ቢባሉ እንኳን በጣም ያዝናሉ። አንድም ካህናት በስብሰባችን ሊገኙ አይችሉም የሚል መንፈስም በንግግራቸው ውስጥ ስላልጨመሩ፣ በሁለተኛ ደረጃም ህጉን ጠንቅቀው ስለሚያውቁት ይኸንን አይነት ያለአዋቂ አባባል ሊሉ እንደማይችሉ ስለሚያውቁት ነው። ጸሀፊው በዚህ ግድፈታቸው እናታችንን ያለቦታቸው ከማዋል ባሻገር የቤተ ክርስቲያናችንን የአባላት ጉባዔ የሌለውን ስም ሰጥተውታል።እማማ ውድነሽ ቤተ ክርስቲያኗ አሁን የምትተዳደርበትን መተዳደሪያ ደንብ ሲዘጋጅ በጸሀፊነት አገልግለዋል።በዚሁ ለ3ኛ ጊዜ ተሻሽሎ በቀረበው የቤተ ክርስቲያኗ መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ አንቀጽ 3፡ሀ፡ክፍል 4፡ “ጠቅላላ ጉባዔ ማለት ይህን ደንብ የሚያከብሩ ካህናቱንና አባላቱን ያጠቃለለ ነው።” ይላል። በዚህ ህግ መሰረት ለአመታት በርካታ ስብሰባዎች ሲካሄዱ የካህናት በጠቅላላ ጉባኤ ሙሉ ተካፋይነታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቶ አያውቅም። የእናታችን አስተያየትም ይህ አልነበረም። አቶ “ምትኩ” ይኸንን ያህል ለደብረ ገነት ዋቢ ጠበቃ ሆነው ሲናገሩና የቤተ ክርስቲያናችንን አሰራር እንዲህ በቅርብ የሚያውቁ ከሆነ እንዴት የቤተ ክርስቲያኗን መተዳደሪያ ደንብ በትክክል ማወቅ ተሳናቸው? ካህናት ሳይኖሩበት የተደረገው ስብሰባ መቼ ነው? እናታችንን እንዲህ ካወቋቸው እንዴት በዚህ ስብሰባ የተናገሩትን አቢይና ትክክለኛ መልዕክት ለአንባቢያን ማቅረብ ቸገራቸው? በጣም ይገርማል!

የማናውቀውን ስንጽፍ ለኛም ለሌሎችም ፈተናንና ውዥንብርን የምንፈጥረው ለዚህ ነው። በርግጥም ጸሀፊ የሚጽፈው የሚዋጣለትና ፍሬ የሚይዝ የሚያውቀውን ሲጽፍ ብቻ ነውና ወደፊትም ስለሚያውቁትና በትክክል በማስረጃ በሚቀርብ ነገር ዙሪያ ቢጽፉ ድካምዎ ጣፋጭ ፍሬ እንደሚይዝ እመክራለሁ።

2ኛ. ጸሀፊው አቶ ምትኩ “የቤተ ክርስቲያኒቷ ምእመናን ላይ “ነግ በኔ” የሚል ከፍተኛ ጭንቀትና ሥጋት አሳድሯል።” ብለው ስላሰፈሩት ጉዳይ ይመለከታል። አቶ “ምትኩ ይመር” የደብረ ገነትን መድኃኔ ዓለምን ምዕመናን ቢያውቋቸው ኖሮ ይኸንን ደግመው አይጽፉትም ነበር። “እሱ ነው የጻፈው” ተብለውም መታወቅም አይፈልጉም። ምናልባትም በብዕር ስም ጽፈው ከሆነ ስለማያውቁን ምዕመናን ያለዎት ግምት ኃፍረትን ስለሚያመጣ የጨለማ ስም መምረጥዎ ጥሩ መደበቂያ ይሆንዎታል። ቤተ ክርስቲያናችን እንደ እማማ ውድነሽ የከበሩና ከፍተኛና የጠለቀ እውቀትንና ጥበብን ያካበቱ ምዕመናን አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጽሙበት፣ በጠቅላላው ምዕመናኑ ሰላምን ፈላጊ፣ ጠንካራዎች፣ ለጋሶች፣ ያላቸውን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያናቸው በመስጠት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገረ አሜሪካ አብርታ የምትታወቅበትን መንገድ የሚያመቻቹ ናቸው። የቤተክርስቲያኗ አስተዳደርም በቀለጠፈና በተመሰከረለት ሁኔታ ስራውን የሚያከናውንና በዘረጋው የሰከነነና የተደራጀ አካሄድ የሚደነቅ ሲሆን በጠቅላላው የቤተ ክርስቲያኑ ማህበረሰብ ሰላምን በመሻት ረገድ የሚያደርገው ጥረትና ስኬታማ የተመላበት ጉዞው ለሌሎች በፈተና ላይ ላሉ አብያተ ክርስቲያናት አርኣያ የሚሆን ነው።

የደብረ ገነት ምዕመናን በጥቃቅኑ ጉዳይ ሁሉ የጽሁፉ አቅራቢ እንደጠቀሱት “በከፍተኛ ጭንቀትና ሥጋት” እንቅልፍ የሚያጡ ሳይሆኑ፣ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ በተዘረጉት የመስተዳድር ዘርፎች ማለትም የአስተዳደር ቦርድ፣ የካህናት ጉባዔና የመንፈሳዊ ጉባዔ አማካኝነት የቤተ ክርስቲያኗን ጉዳዮች በተገቢው መንገድ እልባት እየሰጡ ሰላማቸውን የሚያራምዱ ድንቅና ግሩም ሰዎች ናቸው።

የደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ምዕመናን ቤተ ክርስቲያናቸው በግለሰቦች የምትመካ ሳትሆን ክርስቶስ መሰረቷ ሆኖ የጸናች፣ አለም ሳይፈጠር የነበረው፣ አለምን አሳልፎ የሚኖረው ኃያል ፈጣሪ ክቡር ስሙ ተጠርቶ መንፈስ ቅዱስ የሚከብርባት፣ ማንኛውንም የሰው ሰውኛ ፈተና መቋቋም የምትችል መሆኑን ያምናሉ። ብዙ ውጣውረድም አሳልፈዋል። በአሸናፊነትም ተወጠዋል። እንዲህ “መድኃኔ ዓለም ረድኤታችን ነው” ብለው የሚያምኑ ምዕመናንን ነው ጸሀፊው በጭንቀትና በሥጋት የሚወጥሯቸው። በእውነት እንዲህ ማሰብ የምዕመናኑን ጉባዔና እያንዳንዱን አባል (አቶ “ምትኩ” አባል ከሆኑ ራሳቸውንም ጨምሮ) መተረብ ነው። ይህ የምዕመናን ጉባዔ ነው ዛሬም መምህር ዘበነ ለማን የቤተ ክርስቲያኗ ምክትል አስተዳዳሪ እንደሆኑ ተቀብሎ፣ አምኖበት፣ ጉባኤው አለቃ እስኪሰይም ድረስ መንፈሳዊውን ክፍል እንዲመሩ አውቋቸው የሚኖረው። ይህ እኔ ስለጻፍኩት ሳይሆን ላላንቀላፋ (ከሙታን ምድር ላልሆነ) የሚያየው የሚመሰክረው ጉዳይ ነው። የደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ምዕመናን ይኸንን ባይፈልጉ ለቤታቸው የሚበጀውን ከማድረግ እጃቸውን የሚይዘው፣ ወይም የሚያስፈራቸው አንዳች ነገር የለም።

3ኛ. ጸሀፊው ስለዘገቧቸው በቤተክርስቲያናችን ስለተፈጠሩት ክስተቶች፦
“በምኒልክ ዘመን የደነቆረ ምኒልክ ይሙት እንዳለ ይኖራል” ሆኖ ነው እንጂ ዛሬ ስለደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም መዘገብ ለሚፈልግ የወገን ተቆርቋሪ የሆነ ማንኛውም ግለሰብ የዛሬ 6 ወር ያለፈ ያረጀ ዜና ከመተረክ ዛሬ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ በመተዳደሪያ ደንቧ እየተመራች እንዴት በሰላም መንገድ እንደምትጓዝና በማኔጅመንትና አስተዳደር አሰራር የዘረጋቸውን ቅልጥፍና የተመላበት አሰራር ምን እንደሚመስል በማጥናት ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ትምህርት በሚሆንበት ሁኔታ ላይ በተቸና፣ በጻፈ ነበር። ግን ለዚህ አልታደል ብለን ገና ከሙታን ምድር የተላኩ ደብዳቤዎችን እያነበብን ያለን ትውልድ ነን። ለዚህ የአጸፋ ምላሽ ጽሁፍ መነሻውም እንዲሁ ሁከትን ያነገበ የሙታን ምድር ደብዳቤ በኢንተርኔት መበተኑ ነው። አቶ “ምትኩ ይመር” በዘገቧቸው ጉዳዮች ዙሪያ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ከ6 ወር በፊት የተፈጠሩትን ጉዳዮች በተመለከተ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር፣ የቤተ ክርስቲያኑ የሽምግልና ኮሚቴና፣ የካህናት ጉባዔ በአንድነትና በህብረት መክረውና ዘክረው ለቤተ ክርስቲያኗ የሚበጀውን መፍትሔ ነድፈው፣ በይቅር ምንተእግዜአብሔር ዕርቀሰላም ወርዶ፣ ሁለቱ ግለሰቦች የመንፈስ እናትና የመንፈስ ልጅ ሆነው የሚኖሩበት ጊዜ ነው። (ተሰራ ለተባለው ስህተትና መተላለፍ ሁሉ የጠብ አታሞ የሚያስመታ ነገር፡የለውም። ሁለቱም ታላላቅ የቤተ ክርስቲያናችን ሰዎች ናቸው። በሰውነታቸው ጥፋት ሰርተው ከሆነ ሁሉንም በሚያጥበው በክርስቶስ ደም ተወግዶ ዛሬ የሰላም ዘንባባ በቤታችን ተንዠርግጓል። ወደፊትም ሰዎች በሰውነታቸው የሚሰሯቸው መተላለፎች ይኖራሉ፣ አሉም፣ ሰው ከስህተት ውጭ ታስቦ አያውቅም። እግዚአብሔር ብቻ ፍጹም ነው። ይኸንን አቶ “ምትኩ” አስረግጠው ሊያውቁት ያስፈልጋል።) እንዲህ ያለ የሰላምና የይቅርታን ጥሩ መንፈስ በቤተ ክርስቲያናችን ያለ መሆኑን መዘገብ ለአንባብያን ጆሮ የሚጣፍጥ ዜና ማቀበል ይሆን ነበር። ከዚህ ይልቅ አቶ “ምትኩ” በምትኩ ለግርግርና ለፍጥጫ ጋብዘውናል – “ሳይቃጠል በቅጠል” እያሉ! የሚቃጠል ነገር አላየንም። ክብር ምስጋና ይድረሰውና ቸሩ መድኃኔ ዓለም ሁልጊዜም ወደ ብርሃኑ እየመራ ዛሬ ከደረስንበት አድርሶናል።

መ. የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር ማን እንደሚፈታልን …
ጸሀፊው በቤተ ክርስቲያናችን አሰራር ዙሪያ አንተርሰው በመምህር ዘበነ ሥልጣን ዙሪያ ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት የሊቃውንትን – ስም ጠቅሰው ሲጋብዙ ተነበዋል። ዛሬ ሊቃውንት የሚሰባሰቡ የደብረ ገነት መድኃኔ ዓለምን ችግር ለመፍታት ነው? “ዝሆኑን አስወስዶ በጭራው መጣላት” እንዳይሆን ያስፈራል። ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከላይ እስከታች ፈተና በዝቶባት በምታቃትትበት ወቅት የሊቃውንት መጋበዝ በአንዷ ቤተ ክርስቲያን ችግር ላይ ለመፈላሰፍና ለመጠበብ ነው? ይልቅስ ቤተ ክርስቲያናችን በሲኖዶስ ችግር ስትፈተን ሊቃውንት ስለበጎው ነገር ስለቀናው ነገር ቢመካከሩ አይሻልም? በነገራችን ላይ ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን የመስተዳደር ጉዳይ፣ መንፈሳዊም ይሁን አስተዳደራዊ በሚገባ በተዘረጉት የመስተዳድር መዋቅሮች በመጠቀም የምትፈታ ስለሆነች የተጋበዙትን ቀሲስ ምክር አትሻም። ጸሀፊው ለጠቀሷቸው ክስተቶች መፍትሔ ለመፍታት ደግሞ ከሰው ይልቅ የልዑል እግዚአብሔርን አጋዥነት ለምነን ብዙ ወደፊት ገስግሰናል።

በርግጥ ከእከሌ ከእከሌ ሳይል በጠቅላላው በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ ያለው ችግር እንዲፈታ የሊቃውንትና የጠበብት፣ የካህናትና በሙሉ የቲኦሎጂ ተመራማሪዎች፣ የላቁ አባቶችና እናቶች መምከርና ከፈተናው መውጣት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ህብረትን አንድነትን መሻት መወያየት አልፎ ተርፎም ውጤት ማስመዝገብ ያሻል። ከሁሉም በላይ ግን ለችግሩ ሁሉ መፍትሔ ለሆነው “ሰላማችሁን እንኩ” ለሚል ክርስቶስ ሁላችንም የምንገዛ ከሆነ ከጳጳሳት እስከ ዲያቆናት እስከ ምዕመናን ድረስ በደሙ የዋጃት የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆንን ሁሉ በተቀደሰና በሰከነ፣ ትሕትና በተመላበት መንገድ ወደ አምላካችን እጆቻችንን ዘርግተን፣ እንደ ነነዌ ሰዎች አልቅሰን ጾመን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ ቀደመ ክብሯ የመመለስ ሰማያዊና ምድራዊ አደራ፣ ሃላፊነትና ግዴታ አለብን።

ይህ አንኳር የሆነው የጠቅላላ የቤተ ክርስቲያኗ ችግር ሳይፈታ በጎን ግን እከሌ የእከሌን ችግር ይፍታው፣ እከሌ ጠበብት ይጠየቅ እያሉ አንዱን በአንዱ ላይ ማነሳሳት ግን ለሰላም ከቆመ ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም።

ሠ. እውን የመምህር ዘበነ ቅስና ተቀባይነት አለውን?
የመምህር ቀሲስ ዘበነ ለማንም ሆነ የእያንዳንዱን ካህን ብቃት በተመለከተ በኢንተርኔት የሚያፈራርድ ምንም ምክንያት የለም። ሁላችንም የማንዘነጋው ከሁሉም በላይ የአንድን ካህን ሥልጣነ-ክህነት የሚያጸድቅለት ዋና ሿሚና፣ ቅባቱን የሚያፈስ የህያውነት ምንጭ ሊቀ ካህናቱ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በክርስቶስ ስም ያልከበረ ሊቀ ካህናቱ ያልተቀበለው ክህነት ሲነባበር ቢውል የፈሰሰ ውሀ አያቀናም። በርግጥም ፍትሐ ነገስቱና የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና ቀኖና በሚፈቅደው መሰረት ካህናት ክህነታቸውን መቀበል፣ ማክበር፣ ተገቢውን የክህነት ብቃት ማሟላት ይኖርባቸዋል። ለኛ ምዕመናን ግን ለዘመናት በካህናት ፊት ቀርበን፣ በእጃቸው ተባርከን፣ የያዙትን የክርስቶስ መስቀል ተሳልመን ስንሄድ የበለጠውና በመንፈስ አይናችን የምናየው “ከበደን” ወይም “አበበ” ወይም ‘ሙሉጌታ” ወዘተ የተባለ ሰው ሰርቲፊኬት ይዞ ቆሞ ሳይሆን የሊቀ ካህናቱን ውክልና ይዞ የዘላለማዊ ሕያውነትን መንፈስ ተላብሶ፣ መስቀል ይዞ፣ በልዑል እግዚአብሔር ስም “ይፍታህ” ብሎ የክርስቶስን የድህነትን የተስፋ ቃል የሚመግበንን የክርስቶስ ወኪል ነው። ለምዕመናን ወደ ቤተክርስቲያን ስንመጣ፣ ለጸሎት፣ ለምስጋና፣ ለንስሀ እጃችንን ስንዘረጋ በልባችን ጽላት የተጻፈው ሰማያዊውን ውል የተፈራረምነው ከአንዱ አምላክ ከመድኃኔ ዓለም እንጂ ከግለሰቦችም አይደለም። እንደ እውነቱም በየደብሩ፣ በየቤተ ክርስቲያኑ በየገዳሙ ሄደን ለነፍሳችን አስቤዛ ስንሸምት ነፍሳችንን ሐሴት የምታደርገው እከሌ የሚባለውን ሰርቲፊኬት ያለውን ለማግኜት ሳይሆን በሁሉም ቦታ ሆኖ ለሚጠብቀን ለሚታደገን ኤልሻዳይ አምላክ ባለን መታመን ተከልለን ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመናን ካህናት እከሌ ሰርቲፊኬት አለው የለውም የሚል አይነት ቋንቋ እየተነጋገሩ ካህናትንም ኑ እንመርምራችሁ፣ እናጣራ እያሉ የጠየቁበት ታሪክ የላቸውም። እምነታቸው በቂ ጋሻ ናትና!! በእምነት ድልድያቸው እየተሸጋገሩ በካህናት ላይ ሙሉ እምነት እያሳደሩ አምላካቸውን እያመለኩ ኖረዋል። በርግጥ ካህናት በቂ የሆነ ለክሀነት የሚያበቃ ስልጠና፣ ትምህርት፣ መባረክ፣ መመረቅ፣ ሊኖራቸው ያስፈልጋል። ካህናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባላት አሰራር ውስጥ አልፈው ክህነታቸውን ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይህ የቤተ ክህነት የአሰራር መዋቅር በሚፈቅደው መንገድ የሚሰራ ነው።( በርግጥ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያለው የአመራር መፈረካከስና ያስከተለውን ግርግርና ውዥንብር ከግምት ያስገቧል። ችግራችን እዚያም ላይ አለ፣ ይልቅስ ይኸን ነው መፍታት፣ እንዴት ወደ አንድ መንፈስ እንደምንመጣ!)።

የቤተ ክርስቲያናችን አንዱ ጥንካሬዋና የመጎልበቷ መገለጫም ሊቃውንቶቿ የረቀቁና የመጠቁ መሆናቸውና ኢትዮጵያዊ የሆነ ወጥ አስተሳሰብና የሐይማኖት ፍልስፍናና እይታ ያላቸው ስለሆኑ ነው። በጸሀፊው ጽሁፍ ውስጥ አንድ አውሮፓዊ ስለ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ባሉት ነጥብ እስማማለሁ። ሊቃውንቶቻችን ያወቁ፣ የነቁ፣ የተጠበቡ ናቸው። ወደፊትም ይኸው አካሄድ በበለጠ ተጨምሮበት፣ መቀጠል አለበት። የእድገት ምልክቱ ባለው ላይ አሻሽሎ መገኘት ነው። ለቤተ ክርስቲያናችን መበልጸግ አሁንም ለሙያው ብቃት የሌላቸውና በአግባቡ የክህነት ሥልጠናና ሹመት የሌላቸው ካህናት ካሉ ልቦና እንዲሰጣቸውና ወደሚችሉት ሙያ እንዲሰማሩ ያስፈልጋል።

የደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ምዕመናን የቀሲስ ዘበነን ሥልጣነ-ክህነት እንደሌሎች ካህናቶቻችንና በሌላም ደብር እንደሚባርኩን ካህናት አውቀነው ተቀብለን፣ አምነንበት ካህኑ የአምላካችንን ስም ጠርተው “አሀዱ አብ…” ብለው ቅዳሴ እየቀደሱ፣ እየባረኩን ፣ ነፍሳችን ኃሴት እያደረገች አለን፣ ሰላምም አለን። በአጋጣሚ ደግሞ ዛሬ (11/15/09) ቀሲስ ዘበነ በዋና ቀዳሺነት አገልግለው፣ ባርከውን፣ አቁርበውን ደስ ብሎን ወደ ቤታችን ተመልሰናል። ታዲያ እውነታው ይኸ ሆኖ ሳለ፣ እኒህ ካህን ፍሬያቸውን እያየን በምንኖርበት በአሁኑ ሰዓት አቶ “ምትኩ” የሚያደርጉት በእምነታችን ውስጥ የጥርጣሬ መርዝና፣ የወሬ “H1N1” የሚበትን የነገር ቋት ከደጃችን ላይ አምጥቶ መጣል፣ ትርጉም የሚያጣ የጨለማ ጩኸት ነው። ቀሲስ መምህር ዘበነ ለማ እንደሌሎች ካህናት በእምነት ካህናችን አድርገን ተቀብለናቸው፣ በደስታ እያገለገሉን ነው። አቶ “ምትኩ’ ራሳቸው መምህር ዘበነ በሚያገለግሉበት ጊዜ እየተሳተፉ ግን ሥልጣነ ክህነታቸው “አልዋጥ” ስላላቸው ከሆነ የሚጽፉትን የጻፉት ራስን መቃረን ይመስለኛልና ከራሳቸው ጋር እንዲታረቁ ያሻል። የመምህር ዘበነን የክህነተ ሥልጣናቸውን እሴት ዝርዝሩና ውስጠ ነገሩ በካህኑ፣ ዕልቅናውን በሰጧቸው አባት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስና በተለይም በሊቀ ካህናቱ በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ያለ ነው። እኛ መንፈሳዊ ዕውቀት የሌለን ግን የማንችለውን ነገር ከምንቧጥጥና የሀገራችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳይ በማይገባው አይነት ለአፈርሳታና ለአሉሽ አሉሽ ከምንዳርግ በቦታችን ሆነን የመድኃኔ፡ዓለም ክርስቶስን ጥበቃ እንለምን። የሚያዋጣው እሱ ስለሆነ!

ጠቅላላውን ጸሀፊው ለእኛ እንኳን ባያስቡልን ለራሳቸው የውስጥ ሰላም ለምን እንደማይጨነቁ አጠይቃለሁ። ምን ለማትረፍ ነው ይሆን? እላለሁ። ግዴለም እኛስ የምድር ሰዎች ትቢያ ስለሆንን ብዙ አያሳስብ ይሆናል። በታላቁ ጌታ በክርስቶስ ስም ተሰይሞ የሚቀድስን አንድ ካህን ሰርቲፊኬት አለው ወይም የለውም ብሎ ለማከራከር በድህረ ገጽ አፈርሳታ ከማውጣትስ በፊት ስለጉዳዩ እውነትነትና አግባብ ያለው አካሄድ በሕሊና ማመላላስ ተገቢ አይሆንም ወይ? እውን እንዲህ የአምላካችንን ስም በከንቱ ለአእምሮአዊ አጠይቆና አሉሽ አሉሽ መዳረግ በእሳት መጫወት አይሆንም ወይ? ሆኖም እንኳን ቢሆን ምነው የቤተ ክህነት አዋቂዎች በአርሞሞና በጸሎት ቢመክሩበት? እኛ ምዕመናን ስለሰማያዊው አለም ያለን ግንዛቤ በጣም ውሱን እንደመሆኑና ካህናት በሚመግቡን የመንፈስ “ወተት” የምናድግ ሆነን ሳለን፣ የከበረውን የቤተ ክርስቲያናችንን ክብርና፣ ህልውና ምነው በአለም ቋንቋ በአደባባይ ባንዘባበትበት? ለእኛ ብዙ ለማናውቀው እምነታችንን ያጠነጠነባቸውን የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት እንዲህ ውል እንደሌለው ልቃቂት ሲጎለጎሉ ስናይ ውስጣችን በውዥንብር እንዲጋይ የታሰበ ይመስላል። ለምን? ማንን ለመጥቀም? አቶ “ምትኩ” እንዲህ ያስነበቡንን ነገር ሲዘክሩ በምን አይነት መልኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትጠቀማለች ብለው አስበውት ነው? ምነው ነገራችንንና የሕይወት መገለጫችንን ሁሉ “ያላዋቂ ሳሚ” ባናደርገው። በነገራችን ላይ እኒህ ጸሀፊ ለምን እንዲህ ያለ ጽሁፍ ጻፉ ብየ ሳስብ ያገኘሁት በቂ መልስ ባይኖርም፣ ቅዱስ ጴጥሮስ በ1ኛ መልእክቱ ምዕራፍ 5፡(8-9) ላይ፣ “እንግዲህ ዐዋቂዎች ሁኑ፣ ትጉም፣ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ፣ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና። እርሱንም በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፣ እንዲህም ያለ መከራ በዓለም በአሉ ወንድሞቻችሁ ላይ እንደሚፈጸም ዕወቁ” ብሎ የመከረው ትዕይንቱ ከፊቴ ድቅን አለብኝና አዘንኩ። ምናልባት በዓለም በአሉ ወንድሞች ላይ ይፈጸማል የተባለው ፈተና እንዲህ ይሆን ይሆን?፣ የሚውጠውን የሚፈልገውስ የተባለው ጋኔንስ ተሳክቶለት እየዋጠን ይሆን? ብዬም ፈራሁ።

ረ. ምነው የጎደለውን ማጉላት መረጥን?
በጠቅላላው ከዚህ ትርምስምስ ውስጥ ጎልቶ የሚወጣው አንድ ነገር ለምንድነው እንዲህ መራር የሆንነው የሚል ነው፡ ሁላችንም እኮ ስህተት እንሰራለን። ግን የይቅርታ ቋንቋ የት ሄደ? ምነው ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ከባቴ አበሳ” አይደለምን? እውን እንደ ቸርነቱ ስለሚምረን እንጂ የስንታችን ኃጢአት ቀላል ሆኖ በእርሱ ፊት ያቆመናልን? የተበዳደልነውስ ነገር ካለ አጋጣሚውን እየፈለግን በደመኛችን ላይ በጀርባው ጦር ለመውጋት ከምናሰፈስፍ፣ ለምን የበደለንን ሰው መስቀል ተሸክመንለት አንጓዝም? በሮሜ 12፡20-21 ሐዋርያው ጳውሎስ የመከረን በፍቅር ጠላትን የማሸኘነፍን አብነት መቼ እንተረጉመው ይሆን? ክርስትና ትርጉሙስ ከቂም በቀል ነጻነትን ማወጅ አልነበረምን? ታዲያ እንዲህ ቂም በቀልን የሚተፋ ብዕር እንደምን በክርስቶስ ስም ይጽፋል? እውን የኢየሱስን ስም ኃይል ያወቀ እንዲህ ይደፍራል? ለመሆኑ ስንቶቻችን ነን ከኃጢአት ሳንነካካ እንደ በረዶ ነጭ የሆንነው? ስንቶቻችን ነን የመምህር ዘበነን የሰውነት ድክመቶች ናቸው የምንላቸውን በኩራዝ እያፈላለግን እየተነተንን በድረ-ገጽ ትራጂክ ተውኔቶችን ስንጽፍ ሕሊናችን ብሩህ የሚሆንና ሀገራዊ አስተዋጽኦ አደረግን ብለን የምንኮራ? ማነው በማን ላይ የመጀመሪያውን ደንጋይ የሚወረውር? በንጹሐን ደም የታጠቡት እነ ኮሌኔል መንግሥቱና ተባባሪዎቻው በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በአሜሪካና በሌሎችም አለማት አለማቸውን እየቀጩና አብረውን እየኖሩ ባሉበት ዘመን ጥሩ የሰሩልንንና ሊያድጉ የሚችሉ ወጣት መሪዎችን የአፍ እላፊያቸውንና ትንንሽ ድክመታቸውን እየቆጠርን በዘመኑ የ”ዲጂታል ድንጋይ” በቁም ስንወግራቸውና በነጋታው ደግሞ ለኢትዮጵያ ትንሳዔ ወደፈጣሪ እሮሮ ስናሰማ የትኛውን ሰምቶ ፈጣሪ አቤት እንደሚለን ለማሰብ ይቸግራል። አንዳንዴ ስራችን አህያውን ትቶ ዳውላውን ይመስላል! የኢትዮጵያን ሕዝብ በቁሙ የሚቀብሩ ስንቶች የሉምን? ለነገሩ “ባልንጀራው ቢያጠቃው ወደሚስቱ ሮጠ” ይባል የለ። ይሁንና እንዲህ እርስ በእርስ እየተጠላለፍን፣ ወንድማችን የሚወድቅበትን ጉድጓድ እየቆፈርን ቀናችንን ስናጠፋ በረከቱም እንደራቀን፣ እንደተቸገርን ውሉ እንደጠፋብን እንቀጥላለን። …..ኦሮማይ!

ሰ. ከሙታን ምድር ቅኔ ዘረፋ የሕያዋን ሀገር ሀ፣ ሁ.. ነፍስን ያለመልማል።
“ሥልጣነ-ክህነት የቂም መወጫ በትር አይደለም” በሚል ርዕስ አቶ “ምትኩ ይመር” የዘገቡልን ጽሁፍ ከየት ሀገር የተላከ ነው ቢባል “ከሙታን አለም” ይሆናል ብዬ እወራረዳለሁ። ምክንያቱም በሕያዋን አለም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገዛው መንግሥት ውስጥ “የአሳደህ በለው” ቋንቋ የለም። በወንጌሉ የሰፈረው ትምህርት ሁሉ ወደቀራንዮ መስቀል፣ ለእኛ ሲል ደሙን ያፈሰሰውን ክርስቶስን ያመለክተናል። እርሱም ዘላለማዊ ሕይወት ለማግኘት ህግጋቱን ፈጽሙ ይላል። የህግጋቱ ሁሉ የበላይ አድርጎ ሁለቶችን ሲመርጥልን፣ አምላክህን ውደድ፣ ጎረቤትህንም ውደድ፣ በእነዚህ በሁለቱ ላይ ህግጋትና ነቢያት ይፈጸማሉ ነበር ያለን። ከሁለቱ የትኛውን ህግ ተጠቅመው ይሆን አቶ “ምትኩ ይመር” ጽሁፋቸውን ያስነበቡን? የትኛው ህግ ነው እራሳቸው አንጋፋ ባሉት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎ የሚሰብክን ሰባኪ መምህር ከዚህ በታች ለናሙና የተጠቀሱትን ጸያፍ ገለጣዎች ተጠቅሞ ለመናገር የሚያደፋፍራቸው?
“ለስጋ ለገበያና የሚለፈልፍና የሚቀባጥር ካድሬ አይደለህም”
“ሸቀጥ ለተጠቃሚዎች ለመሸጥ እንደሚንገበገብ ማስታወቂያ ተናጋሪ የቃላት ወንጭፍ በጆሮአችን አትወርውር፡”
“በኛ በምእመናን በራሳችን ገንዘብና ማዕድ አትስደበን፡”
“የእግዚአብሔርን ቃል ከማንብነብ ባሻገር”
“እንደ ዘበነ ያሉ አጥፊዎች ….” ወዘተ
እያሉ ተራና መረን የሆኑ የስድብ ውርጅብኙን ያወርዱታል። አዎ! የአቶ “ምትኩ” ደብዳቤ እነዚህንና ሌሎችንም ለጆሮ የሚዘገንኑ የመደዴና የስድነት ባሕሪ የተጠናወታቸውን ሐረጓች ያካተቱ ናቸው።

እንዴት ያለ ክርስትና ነው ካህናትን ሲመዝን “በኛ በምዕመናን በራሳችን ገንዘብ…” እያለ የቅዱሳን አባቶችን አገልግሎት በሥጋዊ ሚዛን የሚለካ? ድሮስ ቢሆን የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ በምዕመናን እንጂ በማን ይሰራል? ካህኑማ ስራው መቅደስ ውስጥ ነው። እውን የመንፈስ አባቶች ከሚመግቡን ወርቃማ የሕይወት ቃልና ከሚያገለግሉት አገልግሎት የሚበልጥ እኛ የምንሰጣቸው ነገር ይኖራል? ለመሆኑ በ”እኛ ማዕድ አትስደበን” የሚያሰኝ ምኑ ማዕድ ነው? ከአገልግሎት በኋላ የሚቀርበውን ሙት እህል ነው? ወይስ ይኸ መሰረታዊ የስጋ ፍላጎታቸውን የማይሸፍን ብል የሚበላው አፈር የሚሆን “መደጎሚያ ደመወዝ” እያልን የምንሰጣቸውን ገንዘብ ይሆን? ወይንስ ምኑን እየቆጠርን ይሆን “በኛ በምእመናን በራሳችን ገንዘብ..” እያልን የምንገዳደርና የምንለፋቸው? እግዚኦ ነው! ማንኛውም ቤተ ክርስቲያን ሕያው የሆነ፣ የብዙዎች እጅ እንደ አንድ እየሆነ እየተጣመረ እየሰራው፣ ሃላፊዎች ለአዲሶች እያስረከቡት፣ በቀጣይነት ለትውልድ በሚያልፍበት መንገዱ ተዋቅሮ የሚሄድ በክርስቶስ ደም ላይ የሚታነጽ ዘላለማዊ ውቅር እንጂ እንደ ግል ርስት “የእኔ” እያሉ የሚገዳደሩበት አይደለም። እንዲያውም ሰማየዊው መቅደስማ ሰው የሚሰራው አይደለም፣ በቅድምና የነበረ ነው። ለመሆኑ ሰው ለእግዚአብሔር ቤት የሚበቃ ምን በቂ መባ አግብቶ ቢቆጥር ነው “በእኛ ማዕድ” “በእኛ ገንዘብ እያለ” የሚፎክር? እውን “እኔ ባስገባሁት መባ” እያሉ መገዳደር ለእግዚአብሔር ቤት ይሰራልን? ለእግዚአብሔር የሚያስደስተው የተሰበረ ልብ እንጂ ክፋት እንደቡና ከሚያፈላ ልብ የመጣን እምክ እምክ የሚል ዶላር አይደለም። ልባችን ሳይነጻ፣ ወንድሞቻችንን እየበደልንና ካህናትን በስጋዊ እይታ እየለፈፍን የምናቀርበውን መባና “የእኛ ገንዘብ..ማዕድ” እያልን የምንመካበት ገንዘብ በአምላካችን ፊት እንደ ፋንድያ የሚቆጠር ይመስለኛል። በመሰረቱ ቤተ እግዚአብሔር በግል መንፈስ መነካካትም የለበትም፣ ቤተ ክርስቲያን ሲታሰብ ሥጋ መገነዝ አለበት። ነፍስ ብቻ እግዚአብሔርን ታገልግል። ከዚህ ውጭ እንዲያው በሙታን አለም መመላለስ ነው!

ለነገሩ ለቤተ ክርስቲያናችን ዕድገትና ግንባታስ ቢሆን መምህር ዘበነ ለደብረ ገነት ህንጻ መሰራትና በጠቅላላ የቤተ ክርስቲያኑ ሞገስና ክብር መጨመር ያደረጉትን አስተዋጽኦ ምን እንደሆነ አቶ “ምትኩ” ያውቃሉ? ለደብረ ገነት ግንባታ መምህር ዘበነ ያደረጉት ተዋጽኦ ቀላል ነውን? የደብረ ገነት አባል ቢሆኑ የተናገሩትን ለመናገር አይደፍሩም። አዎን ደብረ ገነት ከ30 ዓመት በላይ ሲለፉ፣ ሲማስኑ፣ ሲወድቁ፣ ሲነሱ ከሌላቸው ቆርሰው እየሰጡ ቤቱን ከአሁኑ ደረጃ እንዲደርስ የገነቡ የብዙ ጠንካራ ኢትዮጵያውያን ውጤት ነው። በዚህ ጉዞ ውስጥ አብሮ ደግሞ መምህር ዘበነም የራሳቸውን አመርቂ የሆነ አኩሪ ውጤት አስመዝግበዋል። ሁሉም በመክሊቱ፣ በችሎታው አበርክቶ ነው ደብረ ገነት ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ የደረሰው። ለመሆኑ አቶ “ምትኩ” ደብረ ገነትን ካወቁ ስለ”ዘሩባቤል እጆች”ና ስለ”ዳግማዊ ዘሩባቤል” ፕሮጀክቶች ያውቃሉ? ለአብነት ለመጥቀስ ያህል መምህር ዘበነም በበኩላቸው የዘሩባቤል እጆች የተባለውን ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ መርተው በአንድ ቀን ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲሰባበስ ከፍተኛ የመንፈሳዊ ቅስቀሳ እንዳበረከቱ የቤተክርስቲያናችንን ታሪክ ከስሩ የሚያውቁ ይመሰክራሉ። በቅርቡም ዳግማዊ ዘሩባቤልን በመንፈሳዊ መሪነት እንዲከወንና አመርቂ የሆነ ገንዘብ እንዲሰበሰብ የበኩላቸውን ላቅ ያለ ድርሻ አበርክተዋል። ታዲያ የሰራን ሰው ማመስገን እኮ ተገቢ ነው (Let us give credit where credit is due!)፣ የሰራን ሰራህ ብሎ “እሰየው” “ጎሽ” ማለት የዕድገት ምልክት ነው። አብሮም በተገቢው መንገድ መገሰጹም አስፈላጊ ነው። ግን ተግሳጽ ክብረ ነክ ሲሆን ወደሞት አፋፍ ይወስዳል። ማህበረሰባችን ጥሩ የሰራን የሚደግፍ፣ የሚያጠፋን በአግባቡ የሚገስጽ ነበር፣ የምህረትን ቋንቋ እየተናገረ። እንደዛሬው ጀግኖችን በቁም የመቅበር፣ በጥይት የመረሸን ባሕል ሳንላበስ ጀግኖች እንደ ኮከብ የሚያበሩባት የኢትዮጵያ ምድር ልጆች ነበርን!

ይኸም እንኳን ቢቀር በቅዱስ መጽሀፉ እኮ “የእግዚአብሔርን ቃል የሰጧችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ” የሚል ማስታወሻ ነበረ። እስኪ አቶ “ምትኩ” በጢሞቴዎስ 1፡5(17-18) እንዲሁም፣ መምህራንን ስለማክበር በዕብራውያን 13፡(17-19) የተጠቀሰውንም ያንብቡት። ወንጀል እንኳን የሰራ ግለሰብ በፍርድ ቤት ሲከሰስ በአግባቡና በክብሩ ይጠራል። በሰሞኑ በዚህ የምንኖርበት ሀገር በቴክሳስ ግዛት 13 ሰዎችን በመግደል ከፍተኛ ሀገራዊ ወንጀል የፈጸሙት ሜጀር ሁሴን የተባሉ መኮንን እንኳን ስማቸው በየሜዲያው ሲነሳ ከነሙሉ ማዕረጋቸው እየተጠሩ ነበር። እንዲያው ምን አይነት ስልጣኔ ተላብሰው ይሆን አቶ “ምትኩ ይመር” የአንድን ቤተ ክርስቲያን ምክትል አስተዳዳሪ፣ ሺዎች በወንጌል ሰባኪነታቸው የተጠቀሙባቸውን የተከበሩ የቤተ ክርስቲያናችንን ካህን “ዘበነ” እያሉ የሚያንጠለጥሉ? ይህ ነው የእውቀት ድንበሩ? ይህ ነው የክርስቲያንነት መገለጫው? ይህ ነው ኦርቶዶክስ እምነታችን የምታስተምረን? ያሳፍራል! ታዲያ እንዲህ የበላንበትን የእምነት ወጪት ስንሰብር እንዴት በረከት ይኖረናል? በእውነት አቶ “ምትኩ” የጻፉበትን አላማ ሊመረምሩት ያሻል።

ዛሬ ሀገራችን ከደረሰችበት የውድቀት ደረጃ የደረስንበት አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት ሰውን ያህል በአርኣያ ሥላሴ የተፈጠረ ፍጡር ከእንስሳ አሳንሰን ሸክም ስናከብድበት፣ ስሙን ማጥፋትን፣ ማሳደድን፣አልፎ ተርፎም ግድያን እንደ ልማድ ስለቆጠርነው ነው። አዎን ላለፉት 35 አመታት በአንጻራዊ አመለካከት ሰው እየረከሰ ጤፍና በቆሎ እየተወደደ መጧል። ራሳችንን አረከስነውና ከፈጣሪያችንም ተጣላንና የሞት ከበሮ በየቀዬው እየተመታ፣ የኃዘን ድባብ በሀገራችን ላይ አጥልሎ ይገኛል። በአብዮት ስም ሰውን በሜዳ ላይ የማረድና ደሙን እንደ በግ የማፍሰስን ጭካኔ ተመለከትን። ደነዘዝንና ሰዎች ሰዎችን ማሳደድ ነውር መሆኑን የሚያስተምረንን ዕንቁ ኃይማኖታችንን፣ ትውፊታችንንና ገንቢ ባህላችንን ቀስ በቀስ እየናድነው መጣን። ፓትርያርክ የሚረሸንበትን ዘመን አየነው፣ የሰው ነፍስ ቀልድ ሆነ። በጦርነት መቶ ሺ፣ ሁለት መቶ ሺ..ወዘተ.. ማጣት ተለመደ። በዘርና በጎሳ ፖለቲካም ሆድና ጀርባ ሆንን;፤ ..ፕሮፌሰር መስፍን “የክህደት ቁልቁለት” በሚል መጽሀፋቸው እንዳስጨበጡን መቆሚያችን ሳይታወቅ እንዳንቆም ሆነን ቁልቁል መንከባለሉን ቀጥለናል።… አዎ ዛሬ የሰዎችን ስም በአደባባይ ጭቃ መለወስ፣ ትንሽ እንኳን ብቅ የሚሉትንና ለሀገር ተስፋ የሚሆኑትን እንደ ጫማ ሚስማር ወደ ውስጥ መቀብቀብ ክብራችንን ይጨምርልን ይመስል በአንድ ጊዜ ለሺዎች በሚበተን የዘመኑ ድረ-ገጽ ላይ ችሎት መሰየምና እንካስላንትያ መግጠም ባህል ሆኗል። በምን ሂሳብ? የትኛውን ገነት ለመውረስ? እንዴት ተደርጎ የማሸነፍ ስሌት እየተሰራ ነው? አረ ደሙን በቀራንዩ ባፈሰሰው ስሙ ሁሉንም ኃይላትና ሥልጣናት በሚገዛው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወደአእምሮአችን እንመለስ፣ አረ ልቦና እንግዛ! አረ እብደታችን ይብቃን!

ጸሀፊው አቶ “ምትኩ ይመር” ማንን እንደወከሉ ባይነግሩንም በአቃቤ ህግነት ፍርዳቸውን ሲመሰርቱ “እኛ ለዘበነ የምንለው…” ብለው ቁጣቸውንና ዘለፋቸውን ሲያፈሱት ይነበባሉ። “ለመሆኑ እናንተ እነማን ናችሁ?” የሚል ጥያቄም አብሮ ያስነሳል። የሰዎች ስብስብና ለቤተ ክርስቲያን የምትቆረቆሩ ወይስ ይኸ ጠበል ሲረጭ እንደሚወጣው አይነት “መናፍስት”? እነማን ናችሁ? አቶ “ምትኩ ይመር” አንድ ግለሰብ ሆነው ቀርበው እንደገና “እኛ” እያሉ ድንገት ሲቀየሩ በመጽሀፉ የተጠቀሰው በአንዱ ግለሰብ ውስጥ 2000 ሆነው የተቀመጡትን የሌጌዮን መናፍስትን ታሪክ ወደ አእምሮ ያመጣል። እናንተ ስንት ናችሁ? ምሳችሁስ (አድርግ አድርግ የሚላችሁ) ምንድን ነው? ምዕመናንን ማራበሽ፣ የሰውን ስብዕና ማቆሸሽ፣ ሌላስ? በአንድ አእምሮ ውስጥ ብዙ ሆነው የሚነጋገሩ ድምጸቶች ሲሰሙ በኢንተርኔት ጦርነት ለማዋጋት ከመነሳት የፃድቃኔን ጸበል ከወዲሁ ማሰቡ ይበጃል። ከጨለማው አደባባይ የሚያስደብቅ ምን ጉዳይ አለ? የሚገርምዎት የደብረ ገነት መድኃኔ፡ዓለም ድንቅና ጠንካራ ምዕመናን በጨለማው ውስጥ ሆነው፣ በብዕር ስም ተደብቀው፣ ራሳቸውን እየሰደቡ፣ የሚወዱትን ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አፈርሳታ አያወጡም። የደብረ ገነት መድኃኔ፡ዓለም ቤተ ክርስቲያን ጨዋና፣ የከበሩ የዕድሜ፣ የዕውቀትና፣ የልምድ ባለቤት የሆኑ እናቶችና አባቶች የመሉበት ሲሆን፣ ምዕመናኑ ስለቤታቸው ጉዳይ ሁሉ በሰከነና ዲሲፕሊን በተመላበት የዲሞክራሲን አሰራር በጠበቀ መልኩ እየመከሩና እየተወያዩ በብልጽግናና በዕድገት ጎዳና የሚጓዙ ለሌሎች ተምሳሌት ናቸው።

አቶ “ምትኩ” በወኪልነት ከሆነ የሚናገሩት ማንን ወክለው ነው? አባልስ ከሆኑ ለምን ቤተ ክርስቲያኗ በምትከተለው የመተዳደሪያ ደንብ ስርዓት ተጠቅመው የጠቀሷቸው ችግሮች እንዲፈቱ አይጠይቁም? ታዲያ ከጨለማው ውስጥ “እኛ” የሚሉንና በድብቅ ስም ተሸፍነው የሚናገሩ ከሆነ ይህ ከሙታን ምድር፣ ብርሃን ከሌለበት፣ ሕሊና ከጠፋበት አለም የተከሸነ የሙታን ደብዳቤ እንጂ ሕያዋን የጌታችን የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር ስም እየጠቀሱ የሚጽፉት ጽሁፍ አይደለም። አዎ! የሙታን ምድር ደብዳቤ ያስታውቃል፡፡ ሞት ሞት ይሸታል! ማሳደድ ቋንቋው ነው! ስድብ ዝልፊያ፣ ሸንጎን ያራምዳል። እንዲህ ያለ ቋንቋ በሕያዋን ምድር፣ በሰላም ፈላጊዎች ሰፈር አይነገርም። በርግጥም የደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም አባላት አቶ “ምትኩ” የተጠቀሙበትን ቋንቋ አይጠቀሙም፣ እንዲህ ያለ የጨለማ አካሄድ መርጠው፣ ቤተ ክርስቲያናቸውን ለአፈርሳታ አያወጡም፣ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ለቤታቸው ተቆርቋሪዎች ናቸው። ማንኛውም አይነት አስቻጋሪም ይሁን ቀላል ጥያቄ ካላቸው በስነ ስርዓት ተደማምጠው የሚግባቡበትና መፍትሔ የሚፈልጉበት የምዕመናን ጉባዔና አስተዳደራዊ መዋቅሮችና መንገዶች አላቸው። አቶ “ምትኩ ይመር” የመረጡትን አይነት አክብሮትና ብስለት የጎደለው ስነጽሁፍ የትህትናን አካሄድ የሳተ የስድብ ውርጅብኝ የደብረ ገነት ምዕመናን ይጸየፉታል፣ አይቀበሉትም፣ እኛንም አይወክልም።

የሰላምን ቋንቋ የሚናገር፣ የክርስቶስ ባሪያ የሆነ ሰው የበደለው ጠላቱን እንኳን ሲያገኝ በእርምት የተሻለ ሰው የሚሆንበትን መንገድ ያሳያል። ይቅርታ ቋንቋው ነው። በሀገራችንን አነጋገር “ሰው ለሰው መድኃኒት ነው” እንላለን። እውነት ነው ሰው ለሰው አጋር፣ መድኃኒት፣ አለኝታ፣ ድጋፍ ነው። ሰው እንዲህ ያለ መድኃኒትነት የሚገለጽበት መልካም ስራ የሚሰራ የተቀደሰው የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጡ ሲኖር ነው። ሰው በራሱ ምንም አያደርግም። በተቃራኒው ደግሞ ሰው የሰው ገዢና የስቃዩ ምንጭ ሆኖ ሲወከል ስናይ በውስጡ የሚሰራውንም መንፈስ እንድናጠይቅ እንገደዳለን። የዚህን አካሄድ በአጭሩ ለመረዳት ከፈለግን ከአቤልና ቃየል ወዲህ የሰውንና የአለምን ታሪክ ዝም ብሎ ማጤን በቂ ነው። ሰው ለሰው አጥፊው የሆነበት ከበቂ በላይ ማስረጃ አለን። ከኦሽዊዝ (Auschwitz) እስከ ሩዋንዳ፣ ከ911 እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ከኢትዮጵያ የጦርነት ታሪኮች እስከ ተለያዩ የሀይማኖትና የእርስ በእርስ ትንንቆች ድረስ ምክንያቶች የሰው በጨለማ አስተሳሰብ ውስጥ መኖር ነው፣ ምክንያቱ ቢባል ሰው የጨለማ ቋንቋን ሲነጋገር የሰውን ክቡርነት ስለሚረሳ! ፕላዩተስ (Plautus) የተባለ ሮማዊ ተናገረው የሚባል “ሰው ለሰው ተኩላ ነው” (Homo Homini lupus or Man is wolf to man”) የሚል ብሂል ከላይ የጠቀስናቸውን የሰው ልጅ የጥፋት ታሪኮች የሚገልጥ መስሎ ይገዝፍብናል። ታዲያ የትኛው ባሕሪያችን በድርጊታቸን ውስጥ እንደሚጎላ ሁልጊዜም ማመዛዘን ይገባል። ለሰው ልጅና ለወንድማችን መድኃኒት ነን ወይስ ተኩላ ነን? ሰውን ሲርበው እናበላዋለን ወይስ ለራሳችን ዝና የሰውን ስብዕና አጉድፈን እንጥላለን? ይኸው ነው የዘመናችን የመኖር ወይም ያለመኖር ሐምሌታዊ ጥያቄ!

አቶ “ምትኩ” ይመር የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ፣ ቅዱስ መጽሀፉን አዋቂና ጠቃሽ ሆነው የቀረቡትን ያህል፣ በጻፉት ጽሁፋቸው የሰው ፈጣሪው ልዑል እግዚአብሔር የደነገገውን “ጎረቤትህን እንደራስህ ውደድ” በሚል መርሆ ስር እየተዳደሩ ከሆነ ጽሁፋቸው አክብሮትን የሚገልጸውና፣ ይህን ህግ በስራ ላይ የሚያውለው፣ የት ላይ ነው? ሰው ለሰው አዛኝ መሆኑን የሚመሰክሩልን እንዴት ነው? የት ላይ ነው የይቅርታን ቋንቋን የሚጠቀሙት? ምነው እንዲህ ያለ ቁጣ? ምን ለማትረፍ? ሰዎችን እያሳደዱና እየዘለፉ ሰው ለሰው ተኩላ መሆኑን በሚመሰክር አካሄድ መጓዝ? ለምን አስፈለገ? እውን ስለቤተ ክርስቲያናችን ሲጽፉ ይኸንን መሰረታዊ ህግ ማሰብ አያሻም ነበርን? የሚጽፉትን ማወቅ መሰረታዊ ነው፡፤ የፈላስፋዎች ቁንጮ የሆነው ሶቅራጥስ የሚያውቀውን ሁሉ አውቆ በጣም ከሚደነቅባቸው ብሂሎች በዋናነት የሚጠቀሰው “የማውቀው አለማወቄን ነው” ማለቱ ነው። ምነው በሚያውቁት መጠን መተዳደርና አንደበትን ማሰራት የትህትና መገለጫውና የጥበብ ትሩፋቱ መሆኑን አቶ “ምትኩ” ባወቁት! አባቶቻችን “ዝምታ ወርቅ ነው” የሚል ብሂል ሲያስተላልፉልን ያለምክንያት አልነበረም። አላዋቂ ሲናገር ጥፋትን ስለሚተፋ ነው።

ሸ. ምዕመናንና መምህር ዘበነስ ከዚህ ስንክሳራችን ምን እንማራለን?
በርግጥ ሰው ጥሩ የሚሰራውን ያህል በአካባቢው ላሉ ሰዎች የማይመች ንግግር፣ ስራና ባሕሪ ሊያሳይ ይችላል። ከዚህ ነጻ የሆነ ሰው የለም። መምህር ዘበነም ከዚህ የሰው ተፈጥሮ ነጻ ሊሆኑ አይችሉም። በተለይ በአሁኑ ሰዓት እንዲህ ከተለያየ አቅጣጫ የሚሰነዘሩ ጥቆማዎች ሲኖሩ የግለሰቦችን ክብር የሚነኩ፣ እንደ ትዕቢት ሊቆጠሩ የሚችሉ አካሄዶችን የሚጠቁሙ አስተያየቶችና የመረሩ ስሜቶች ሲመነጩ፡ በተለይም አመኔታ የሚጣልባቸው ሰዎች ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚቆረቆሩ ሰዎች ሲመክሩ “እውን ሕዝብ የሚያስቀይም ነገር እየፈጸምሁ ነውን?” በማለት ራሳቸውን ሊገመግሙና ሊያጠኑ ከስህተታቸውም ሊማሩ ያስፈልጋል። ይኸንንም የሚያደርጉ ሰው ናቸው ብዬ አምናለሁ። ከዚህ በፊት በአውደ ምሕረት ላይ መስቀል ይዘው “ይቅር በሉኝ” ብለው ንስሐ ሲገቡ አይቻለሁ። ስህተት መስራታቸውን ካመኑበት ይቅርታን ይጠይቃሉ፡ ይኸንን አብረን በሰራንባቸው ጊዜያት ሁሉ በሚገባ ታዝቤያለሁ።

ለሁላችንም ልንገነዘበው የሚያስፈልገዉ ነገር ግን ችግር የሚመጣው ከስህተት መማር ሳይቻልና ስህተት ልማድ ሆኖ ጉዳት ማስከተል ሲጀምር ነው። መሪዎችና በሕዝብ ፊት ያሉ ሰዎች ስሕተታቸው ቶሎ ይታያል፣ ከታዬም በኋላ ጎልቶ ይወጣል። ታዲያ በሕዝብ ፊት የሚንቀሳቀስ መሪ ትሕትናን ገንዘቡ አድርጎ፣ ለሚሰራው ስህተት ይቅርታን እየከፈለ፣ ለትሕትና ተምሳሌት እየሆነ መሄድ ይገባዋል። የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ መሪዎቹን አክብሯቸው የሚኖር ስህተት ስለማይሰሩ አልነበረም፣ ብዙ ስህተቶችን የሰሩ መሪዎች አሉን። ዛሬም እየተሰሩ እንመለከታለን፡፤ ግን ሕዝቡ የሞላውን እየቆጠረ፣ በጎደለው ይቅር እያለ መሐሪነትና ታጋሽነትን ባሕሪው አድርጎ የኖረ መልካም ሕዝብ ስለሆነ ነው። ታዲያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲጠላም ያንኑ ያህል ነው። ከዚህ ታሪካችን መማር አለብን፡፤ ለዚህ ነው መሐሪነትንና ታጋሽነትን ገንዘባችን ማድረግ የሚገባን። የሚያሳዝነው ግን የኛ ትውልድ ለዚህ ልቡ ደንዳና ሆኗል። በሀሳብ መለያየት ማለት ደም የተቃባ ባላጋራ የመሆን ያህል መጠላላት ሆኗል። ከዚህ አካሄዳችን መለወጥ ይኖርብናል። ዛሬም እንደትላንትናው አባቶቻችን እንደተጠቀሙበት በይቅርታ መንፈስ፣ ተግባብቶ፣ ተከባብሮ ተቻችሎ በፍቅር መኖር ከምንም በላይ ምርጫችን ሊሆን ይገባል። በመስቀሉ ላይ የተሰዋው አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ በደሙ የጻፈልን ኑዛዜ ይኸንኑ የፍቅር አብነት ነው። ትላንት ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት ሴኔተር ክሊንተንና ሴኔተር ኦባማ ምን ያህል የሃሳብ ፍጥጫ ላይ ደርሰው እንደነበረ የምናውቀው ነው። ዛሬ ደግሞ አንዱ የሌላው መከታ ሆነው እየሰሩ ነው። ይህ በአለም ሕይወት እንኳን እንዲህ ከተቻለ በክርስትና ጥሪማ ምን ያህል የዕለት ተግባራችን በሆነ! በእውነት ይህ በሆነበት የአሜሪካ ምድር እየኖርን ከዚህ ቅዱስ አካሄድ ተምረን የማንለወጥና የራሳችንም ሀገራዊ፣ ማህበራዊና፣ ግላዊ ሕይወት ለማስተካከል የማንጥር ከሆነ እግዚአብሔርስ ምን ምሳሌ ሊያቀርብልን ይችላል?

ቀ. ማጠቃለያ
(1ኛ) በአጭሩ ከላይ ምክንያቶችን ጠቅሰን እንዳነበብነው “ሥልጣነ-ክህነት የቂም መወጫ በትር አይደለም።” በሚል አቶ “ምትኩ ይመር” ያስነበቡን ጽሁፍ “ቢከፍቱት ተልባ” ነው። ምክንያቱም፡

(ሀ)፣ የተሸከመውን መልዕክት በትክክል ለማስተላለፍ የተጠቀሱት ግለሰቦች ተናገሩት የተባለውን ነገር እንኳን በትክክል ጠቅሶ አያስቀምጥም። ለአብነት ያህል ካህኑን “በስብሰባው ላይ ልትገኝ አትችልም” ብለዋል ብሎ የተጠቀሰው በስብሰባው ላይ ያልተባለ፣ ተናገሩ የተባሉትንም ግለሰብ የሚያሳዝን ነው።

(ለ) ጸሐፊው የአንድን ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በተቆርቋሪነት ተፈርጀው ሲናገሩ የቤተ ክርስቲያኗን መተዳደሪያ ደንብ እንኳን አጥርተው አያውቁትም። ካህናት የጠቅላላ ጉባዔ አባላት መሆናቸውንና እንደማንኛውም አባል በእኩልነት መሳተፍ የሚችሉ መሆናቸውን እንኳን አያውቁም። ይኸንን ቢያውቁ ኖሮ ሲጀመር ከላይ በ(ሀ) የተጠቀሰውን፣ እከሌ ተናገረው ብለው እንኳን ለማለት አይታሰባቸውም ነበር። የስብሰባ ባህላችንን ቢያውቁት ሁልጊዜም በስብሰባችን መካከልም ካህናት መኖራቸውንም ያውቁት ነበርና።

(ሐ) ለሺዎች አንባቢያን የኦርቶዶክስ እምነት ተቆርቋሪነታቸውን ለማስገንዘብ የተነሱ እኒህ ግለሰብ፣ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቀውን የትሕትና አቀራረብና አጸጻፍ አፋልሰው መድረኩን መዘራጠጫ ሊያደርጉት ሞክረውል። እንዲህ ያለ የስድብ ውርጅብኝ፣ ዘለፋ፣ ያካተተ ጽሁፍ በየትኛውም ቦታ ሞገስ ኖሮት አያውቅም። እስኪ አቶ “ምትኩ” በገላትያ 5፡19- 21 ድረስ የጠቀሳቸውን የስጋ ስራዎችንና በአንጻሩ ደግሞ በተቃራኒው ሐዋርያው ጳውሎስ እዚያው ወረድ ብሎ በቁጥር 5፡ 22- 26 የተጠቀሱትን የመንፈስ ፍሬዎችንም ይመርምሩ። እስኪ የሥጋንና የመንፈስን ፍሬዎች አወዳድረው ከሁለቱ አማራጮች የርስዎ ጽሁፍ በየትኛው እንደሚፈረጅ በእውነት ይፍረዱ። ይኸንን ቢያውቁ ኖሮ እውን ብዕርዎን ያነሱ ኖሯል? ለዚያ ነው ጽሁፉ በቁምነገር ወንፊት ቢነፋ እብቅና እንክርዳድ ብቻ የሚወጣው!

2ኛ) ሌላው በዚህ አጋጣሚ ላሳስበው የምወደውና ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ ለሀገራችን የወደፊት ትንሳዔ፣ ለእድገቷና ለብልጽግናዋ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ደህንነት ስንል ኢትዮጵያውያን ሁሉ በችሎታችን ያለውን አንድ ነገር ማድረግ የትውልድና የዜግነት ግዴታ አለብን። ይኸውም በጽሁፍም ይሁን በአየር ሞገድ በሚተላለፉ ዜናዎች በጆሮአችን የምናዳምጣቸውና የምናስተላልፋቸው መልእክቶች ስለጤናማነታቸውና ስለገንቢነታቸው መመርመር ይገባናል። ክፉ መናፍስት አለምን ያጣበቡበት ዘመን ነው። የሚተላለፉልን መልዕክቶች ወይ የሕይወትን ቃል በውስጣችን የሚያሰርጹ ወይንም የሞትን ጡሩንባ የሚነፉ ናቸው። ከሁለቱ መምረጥ የእኛ ፋንታ ነው። ለመምረጥም ችሎታው አለን – በአምሳሉ መፈጠራችንን አንርሳ – የጥበብን ሀገር መሻት ብቻ ይኖርብናል። በጥበብ ሁሉም ስለሚገለጽና ስለሚታይ! የሰዎችን አብሮ የመኖር፣ ሰላምን፣ ይቅር መባባልን፣ ፍቅርን የሚያራምዱ መልዕክቶች ከሕያዋን ሀገር የመጡ በሕያው አምላክ የተቀደሰ መንፈስ የተባረኩ ጽሁፎችና ድምጸቶች ናቸው። ሰዎችን በማዋረድ ክብርን በመግፈፍፍ፣ ለጠብ በማዘጋጀት፣ በስድብ፣ በዘለፋ መልክ የተቀረጹ ጽሁፎችና የአየር ሞገድ መልዕክቶች ደግሞ ለነፍሳችን ሁከትን የሚያመጡ አብሮ መኖራችንን የሚፈታተኑ ለሀገራችን ትንሳዔ፣ ለቤተክርስቲያናችን ደህንነት ቀቢጸ ተስፋን የሚያራምዱ የሙታን ጩኸቶች ናቸው። እግዚአብሔር በሰጠን የሰውነት ጥበብ ከታገዝን የሙታንን እንጉርጉሮ ከሕያዋን ዝማሬ መለየት ስለማይቸግረን በጎውን፣ መልካሙን፣ ጥሩውን የሚያስጨብጡንን ከመርገምና ከመዝለፍ ተቆጥበን ለሀገራችን የሚበጀውን እናድርግ። ሐዋርያው ጳውሎስ በቅዱስ ቃሉ የመከረንን በጥሞና መመርመሩ ስለወንድሞቻችንና ስለእህቶቻችን ከአንደበታችን የምናፈሰውን እንድንመረምርና በጥፋት ጎዳና እንዳንጓዝ ይረዳናልና ከዚህ ላይ ማስታወሱ ይበጃል። እንዲህ ይላል፦

“የሚሰሙአችሁ ሞገስ ያገኙ ዘንድ ግዳጃችሁ እንዲፈጸም መልካም ነገር እንጂ ከፉ ነገር ሁሉ ከአፋችሁ አይውጣ። በዳናችሁ ጊዜ የታተማችሁበትን የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑት። መራራነትንና ጥፋትን፣ ስድብን ሁሉ ከክፉ ነገር ሁሉ ጋር ከእናንተ ጋር አርቁ። እርስ በእርሳችሁም ቸሮችና ርህሩሆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።”ኤፌሶን 4፡29-32

አዎ! በኢትዮጵያውነታችን እንድንኮራና የሀገራችንን ትንሳኤ እውን እንዲሆንልን፣ በፍቅርና፣ በይቅርታ ቋንቋ እየተናገርን፣ “ለሚሰሙን ሞገስ ያገኙ ዘንድ ግዳጃችንን” እየፈጸምን፣ ለጆሮአችን ከቅዱሳን የከንፈር ፍሬ እየመረጥን እያዳመጥን በጥበብ እንደግ! ኢትዮጵያውያን ሆይ!፡ከሙታን ምድር የሚላኩልንን ደብዳቤዎችና በሬዲዮ ሞገዶች የሚለቀቁብንን የክፋት ንግግሮች ማንበብና ማዳመጥ ይብቃን! ይልቅስ ሁላችንም ተባብረን አንዳችን ለአንዳችን ዋቢና ቋሚ ጠበቃ ሆነን ሐይማኖታችንን እንጠብቅ፣ ሀገራችንን እንታደግ፣!

የሞትን ትዕዛዝ ለመፈጸም በ ሀመር ፈረስ እየጋለቡ ከሚመጡብን መናፍስት ሁሉ የይሁዳ አንበሳ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲጠብቀን በእርሱ እንመን እንታመን!!

ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይጠብቀን፣ እንደበደላችን ሳይሆን እንደ ቸርነቱ የሚያኖረን አንድ አምላክ ለሁላችንም የፍቅርንና የሰላም የአንድነትን ልቦና ይስጠን፣

የኢትዮጵያችንን በክብር መቆም ያፋጥንልን!!!

ሁሉን ለሚያደርግ፣ ሲመታትን፣ ኃይላትንና ሥልጣናትን ለፈጠረ፣ ነገስታትና ኃይለኞች ሁሉ የሚንበረከኩለት አንዱ ጌታ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምሥጋና ይግባው።