የወያኔ የምርጫ ቅስቀሳ ስልት አደጋ እያስከተለ ነው

በቀጣዩ ሚያዝያ ለሚካሄደው የአከባቢና የማሟያ ምርጫ ለቅስቀሳነት ይረዳኛል በሚል በተመረጡ የኦሮሚያ ክልሎች የወያኔ ካድሬዎች በገበያ ስፍራዎች በመዘዋወር የምግብ እህል ዋጋዎችን ዋጋ በማውጣትና ከዚያ በላይ የሚሸጡ ነጋዴዎችን ምርት በመውረስ እንዲሁም ባለንብረቶቹን በማሰር ‘የወያኔ የቁርጥ ቀን ደራሽ’ መሆኑን ለማመልከት በመጣር ላይ ይገኛል፡፡

በተሰበረ ዋጋ ነጋዴዎች እንዲሸጡ እየተደረገ ያለበት አካሄድ የወያኔ ሹማምንት ቀደም ባሉት አመታት “ገበሬው ምርቱን በፈለገው ዋጋ መሸጥ እንዲችል አድርገነዋል” ከሚለው ጋር ፈጽሞ የሚጣረስ ከመሆኑም በተጨማሪ እርምጃው ቅዳሜ ከተወሰደ በኋላ በዛሬው እለት አብዛኞቹ የኦሮሚያ የገበያ ስፍራዎች የእህል ሸቀጦች ያልታዩባቸው ሆነዋል፡፡

ለዜና አገልግሎቱ በደረሱት ዝርዝር የገበያ መረጀዎች መሰረት ማኛ ጤፍ በኪሎ ከአምስት ብር በላይ የሚሸጡ በሙሉ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሲሆን የገበያ ማረጋጋት ዘዴ በመጠቀም የዋጋ ግሽቱን ከማረጋጋት ይልቅ ለምርጫ ቅስቀሳ በሚረዳ መልኩ ብቻ በጠመንጃ አፈሙዝ እርምጃውን በመውሰድ መንግስት ከጎናችሁ ነው የሚል ህገወጥ ዘመቻ (የጫካ ህግ) ሲካሄድ በመዋሉ በዛሬው እለት (ሁኔታው ቀጣይ ይመስላል) አሳሳቢ የምርት እጥረት ታይቷል፡፡

የተመረጡ የገበያ ቦታዎች የተባሉት ከደብረዘይት እስከ ምስራቅ አዋሽ ያሉ የገበያ ስፍራዎች፤ ከመልካሳ እስከ መረሮ ያሉ ገበያ ስፍራዎች፤ በምስራቅ ሸዋ ከእድርገሳ ሞርቾ (ከአዲስአበባ 300 ኪ.ሜ.ርቀት ላይ) በሰሜን ሸዋ ዞን ፊቼን ጨምሮ ሁሉም ከተሞች፤ ከአለም ገና እስከ ቁምቢ ባሉ በሁሉም ከተሞች የገበያ ስፍራዎችን በመሳሰሉት ላይ በተደረገው በምጣኔ ሃብት የገበያ መርህ ያልተደገፈ የምርጫ ቅስቀሳ ፍጆታ ማሟያ ግልጽ አደጋዎች መከሰት ጀምረዋል፡፡