ወያኔ የአንድነት ፓርቲ ምስረታ ፊርማ አሰባሳቢዎችን ማገት ጀመረ

የቅንጅት ስያሜ ለአንድ ግለሰብ ከተሰጠና ህዝባዊ ባለቤትነቱ በወያኔ ከጠነጠቀ በኋላ ፓርቲው የተነሳለትን አላማ በስያሜ ሰበብ ላለማደናቀፍ በሚል ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያሉ ደጋፊዎችንና አባላትን በማወያየት “አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ” በሚል ስያሜ ፓርቲ ለመመስረት የመስራች አባላት ፊርማ በማሰባሰብ በመላ አገሪቱ በመንቀሳቀስ ላይ ካሉት አባላት የተወሰኑት ብርቱ ማስጠንቀቂያ ሲደርሳቸው በጉራጌ ዞን ኢጃ ወረዳ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ላይ የነበሩ አባላት ደግሞ መታገታቸውን ክልሉ የፓርቲው አስተባባሪ ለዜና አገልግሎቱ ገለጹ፡፡

የአንድነት ፓርቲ ስራ አስፈጻሚዎች፤ የላእላይ ም/ቤት አባላት፤ የተለያየ ሃላፊነት ያላቸው ነባር አባላትና የፓርቲው አስተባባሪዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር የመስራች አባላት ፊርማ ከማሰባሰቡ ጎን ለጎን ደጋፊዎቻቸውን የማነቃቃት ስራ በመስራት ላይ የሚገኙ ሲሆን እንቅስቃሴያቸውን ለማደናቀፍ የወያኔ ካድሬዎች እያካሄዱ የነበሩት ተግባር የፓርቲው ከፍተኛ ደጋፊ ባለበት የኢጃ ወረዳ ፊርማ በማሰባሰብ ላይ የነበሩትን አባላት በማሰር ‹‹ለልማት ያለው ብቸኛው አማራጭ ኢህአዴግ ብቻ ነው››የሚል ገለጻ ካደረጉ በኋላ የተወሰኑትን ሲለቁ ሁለት አስተባባሪዎችን እስካሁን በእስር ላይ አቆይተዋቸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው አመራር አባል በአሁኑ ወቅት የሚፈጸሙት ወከባዎች እየባሱ መጥተዋል ሆኖም የአባላቱን ጉዳይ በህግ አካሄድ እንከታተለዋለን ብለዋል፡፡

የመስራች አባላት ፊርማ የማሰባሰብና የግንዛቤ ማስጨበጫ (የማነቃቂያ) የግዜ ገደቡ የፊታችን አርብ ይጠናቀቃል፡፡