ወያኔ አጼ ምኒልክ ላይ ዘመቻውን እንደገና በአዲስ መልኩ ጀመረ

በቀጣዩ ሚያዝያ ለሚካሄደው የአከባቢና የማሟያ ምርጫ ፓርቲዎች የምረጡኝ ዘመቻቸውን የጀመሩ ሲሆን ወያኔ በ1887 ዓ.ም አጼ ምኒልክ አደረጉ የሚባለውን መስፋፋት በማስታወስ ‘ነፍጠኞች’ የአርሲ ሴቶች ጡት ሲቆርጡ የሚያሳይ ምስሎችን (ፖስተሮችን) የወያኔ ካድሬዎችን በክልሉ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የኦህዴድን 18ኛ አመት የምስረታ በአል አስመልክቶ በአርሲ ልዩ ስፍራው ‹‹አኖሌ ሃርመ ሙራ›› በተደረገው ቅስቀሳ ‹‹በቀጣዩ ምርጫ የምኒልክ ነፍጠኞችን ጭፍጨፋ መቃወማችንን በሚያሳይ መልኩ ኦህዴድን እንምረጥ›› የሚሉና ተመሳሳይ አሉታዊ ቅስቀሳዎች ተንጸባርቀዋል፡፡

በዛሬው እለት በአዳማ በተካሄደው ተመሳሳይ የበአል አከባበር ላይ ከመቶ አመት በፊት የተፈጸመው የምኒልክ ዘመቻ ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት ለሚያዝያው ምርጫ በመቀስቀሻነት የዋለ ሲሆን በምርጫ 1997 ወቅት የአከባቢው ነዋሪ ህዝብ ‹‹ወሬ መፍጠራችሁን ትታችሁ አንገብጋቢ የልማት ጥያቄዎቻችንን አሟሉ›› ከማለት አንስቶ የክልሉን ፕሬዝዳንት በአሳፋሪ ሁኔታ በምርጫው እንዲሸነፉ ከፍተኛ ሚና መጫወቱ ይታወሳል፡፡