በምርጫ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ ስምንት እጩ ተወዳዳሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ

በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ጉለሌ ወረዳ ውስጥ ለቀጣዩ የሚያዝያ የአከባቢና የማሟያ ምርጫ በመቀስቀስ ላይ የነበሩ ስምንት እጩዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሪፖርተራችን ዘገበ፡፡

ትናንት ከሰአት በኋላ በጉለሌ ዋና ከተማ ካምቦ ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ የነበሩት ወጣቶች የኦፌዴን እጩዎች እንደነበሩ ዘጋቢያችን ያረጋገጠ ሲሆን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከመዋላቸው አስቀድሞ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በየመንደሩ በመዞር እድገትና ልማት ባመጣላችሁ መንግስት ላይ ልጆቻችሁ ሸፈቱ በሚል ውዥንብር ሲነዙ እንደነበር የከተማዋን ነዋሪዎች ዘገባ ዋቤ ያደረገው ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የንቅናቄው ሊቀ መንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ክስተቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸው ሁኔታውን እየተከታተሉት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጨምረውም ሁኔታው ምን ያህል አስቀያሚ ደረጃ ላይ እንደደረሰ አመላካች ክስተት ይሆናል ብለዋል፡፡ አቶ ቡልቻ በጉለሌ ወረዳ ስለሚካሄደው ምርጫ ኢ-ፍትሃዊነት ሲገልጹም የምርጫ ጣቢያው በፖሊስ ጽ/ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመሆኑ ስነ ልቦናዊ ጫና እንዲኖረው ሆን ተብሎ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡