ለጥምቀት የወጣው ህዝብ ለቅንጅት አመራር የማበረታቻ መልእክት አስተላልፈ

የጥምቀት በዐልን ለማክበር በቦሌ መድሃኔአለም የተገኙት የቅንጅት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ግዛቸው ሽፈራው ለበዐሉ ካደመው በብዙ ሺህ የሚቆጠር ምእመን “በርቱ” የሚል የድጋፍ መልእክት ተላለፈላቸው::

አቶ ግዛቸው በስፍራው የተገኙት ከቤተሰባቸው ጋር በበዐሉ ለመካፍል ቢሆንም በቦታው መኖራቸው እንደታውቀ ብዙ ሺህ ህዝብ ከቧቸው አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን ሲሰነዝር የነበረ ሲሆን ህዝቡ የቅንጅት ምልክት የሆነውን ሁለት ጣት ማሳየት ሲጀምር በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶች የመደናገጥና ግራ የመጋባት መልክ ይታይባቸው ነበር::

አቶ ግዛቸው በርካታ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን ካስተናገዱ በኋላ ቅንጅት የህዝብ ድርጅት በመሆኑ ጊዜያዊ ችግሮች ቢያጋጥሙትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው ወደቤታቸው ተመልሰዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ የነ አቶ አባይነህ ቡድን በመኢዐድ ስም መንቀሳቀስ በመጀመራቸው ምክንያት ከፍተኛ የህዝብ ቁጣ እየደረሰባቸው በመሆኑ ስልት በመቀየር “ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ” በሚል ስያሜ የፓርቲ ፈቃድ ለማውጣት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል::