ነገ እሁድ የቅንጅት አመራር መሰረታዊ ውሳኔዎችን ያሳልፋል

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለዛሬ (ቅዳሜ) የጠራው የላእላይ ም/ቤት ስብሰባ ምልአተ ጉባኤ ባለመሟላቱ ባይካሄድም በህገ ደንቡ መሰረት በነገው እለት በሚገኙት የላእላይ ም/ቤት አባላት አብላጫ ድምጽ መሰረታዊ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ የፓርቲው ቃል አቀባይ ዶ/ር ኀይሉ አርአያ ለዝክር ዜና አገልግሎት ገለጹ፡፡

ዶ/ር ያቆብ ኃ/ማርያምንና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ በተለያየ ምክንያት በአገር ውስጥ የሌሉ 11 የላእላይ ም/ቤት አባላት በነገው እለት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የሚተላለፉትን ውሳኔዎች እንደሚደግፉ በላኩት ደብዳቤ አረጋግጠውልናል ያሉት ቃል አቀባዩ ወሳኝ የፓርቲውን ስራዎች የምናከናውንበት ምእራፍ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡

በተጓደሉና ሪፖርት ባላደረጉ የላእላይ ም/ቤት አባላት ምትክ የሚደረገውን ምርጫ አስመልክቶም ይህ የሚታወቀው በነገው እለት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ አመራሩ ውሳኔ ከሰጠበት በኋላ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡