የመራጮች ምዝገባ ነገ የጀመራል

ወደ ምርጫ የሚገቡት ተቃዋሚዎች ሁኔታ አልታወቀም

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በዛሬው እለት በምርጫ ቦርድ የቀረቡለትን ሶስት ጸሃፊዎች በአብላጫ ድምጽ የመረጠ ሲሆን በጊዜ ሰሌዳው መሰረትም የመራጮች ምዝገባ ከነገ ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል ይቀጥላል፡፡

በተሻሻለው የምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/99 አንቀጽ 15 መሰረት አንድ ዋ/ጸሃፊ/አቶ ተስፋዬ መንገሻ እና ሁለት ም/ዋ/ጸሃፊዎች አቶ ኤርሚያስ አሰፋና ወ/ሮ ራሄል ታደሰ ተመርጠዋል፡፡

በምርጫ 97 ከተከሰቱትና እስካሁን እልባት ካላገኙት ችግሮች አንጻር ቀጣዩ ሂደት የህዝቡን ትኩረት ይስባል ወይ በማለት ዋና ጸሃፊ ሆነው የተመረጡትን አቶ ተስፋዬን ጠይቀናቸው ጨለምተኛ ሆኖ መጀመር አይገባም ተገቢው ስራ ሁሉ ይሰራል የሚል ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል የቅንጅት፤የኦፌዴንና የህብረት አመራሮችን በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት የጠየቅን ሲሆን ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች አውስተዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ በርካታ ቢሮዎቻቸው የተዘጉ መሆናቸው፤ያለ ፍርድ የታሰሩ አባሎቻቸው ሁኔታ ያልተቋጨ መሆኑ፤የሜዲያ አጠቃቀም ኢ-ፍትሃዊነት፤ የተለያዩ ጫናዎች የሚደረጉ መሆኑ፤ በህጉ መሰረት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደረጉ የተለያዩ ድጋፎች/የገንዘብና የማቴሪያል/ያለመኖራቸውና በሌላ በኩል ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ ያለው የቅንጅት ፓርቲ ያለበት ሁኔታ ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የወረዳና የከተማ አስተዳደር ም/ቤት ምርጫ ሚያዝያ 5 እንዲሁም የቀበሌ ም/ቤት አባላትናየማሟያ ምርጫ ሚያዝያ 12 ቀን 2000 አ.ም እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡