የቅንጅት ምክትል ፕሬዚደንት ብርቱካን ሚደቅሳ መኪና ተሸለሙ

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ፈረንሳይ ለጋሲዮን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች የአካባቢያቸው ልጅ ለሆነችው ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ መኪና በመሸለም ደስታቸውን ገለጹ፡፡ በተጨማሪም ከእስር ለተፈቱት የቅንጅት አመራሮች የምሳ ግብዣ አደረጉ፡፡ በግብዣው ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም እና ወ/ት ብርቱካን ንግግር አድርገዋል፡፡ ከቀኑ አምስት ሰአት ጀምሮ ነበር ግብዣውን ያዘጋጁት የአካባቢው ነዋሪዎች ጉድ ጉድ ማለት የጀመሩት፡፡ እንግዶቹ በተጠሩበት 7፡00 ሰአት ሲመጡ ግን አካባቢው በጩኅት ተናወጠ፡፡ ሁሉም ደስታውን በጭብጨባ መግለጽ ጀመረ፡፡

ዝግጅቱ ወደተደረገበት የቀበሌ እድር አዳራሽ ሲገባ አዳራሹ ውስጥ የተሰበሰበው ህዝብ ደስታውን የሚገልጽበት ስሜት ምናልባትም ከምርጫው በሓላ የመጀመሪያው የህዝብ ስሜት ሊባል የሚችል ነበር፡፡ ሁሉም ታዳሚ የቅንጅት አርማ የሆነውን የጣት ምልክት በማውጣት በፉጨት ደስታውን ይገልጻል፡፡
አዘጋጆቹ ንግግር ካደረጉ በሓላ የምሳው ግብዣ ሥነስርአት የተከናወነ ሲሆን ኣቶ ኃይሉ ሻውል ባለመገኘታቸው የተዘጋጀላቸውን ስጦታ በልጃቸው አማካኝነት ተሰተቸዋል፡፡

በተጨማሪም ለፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ስጦታ የተሰጠ ሲሆን ይህ ለሁለቱም የተሰጠው ስጦታ የቅንጅት አርማ የሆነው የጣት ምልክት የተቀረጸበት ዱላ ሲሆን ‹‹በትረ መንግስት›› ሲሉም ሰይመውላቸዋል፡፡

ለአቶ ሙሉነህ ኢዩኤል እና አቶ አለማየሁ ለተባለ የአካባቢቸው ወጣት ተጨማሪ ሥጦታን ከሰጡ በኋላ ለወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ ሽልማት እንዳላቸው ተናገሩ፡፡ ህዝቡ ሽልማቱን ለማወቅ በከፍተኛ ጉጉት የጠበቀ ሲሆን ‹‹ጀግና›› ላለት የአካባቢያቸው ልጅ የመኪና ቁልፍ አስረከቡ፡፡ ህዝቡ ደስታውን በጭብጨባ ገለጸ፡፡

ወ/ት ብርቱካን ምን እንደምትናገር የጠፋት በሚመስል ስሜት በሁለት እጆችዋ አርማውን እያሳየች ከወገቧ በመጎንበስ ምስጋናዋን ገልጻለች፡፡ ወደ መኪናዋም በመሄድ የተሸፈነችበትን ጨርቅ ገልጣ ተረክባለች፡፡

አዘጋጆቹም ሽልማታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ‹‹አቅማችን ፈቅዶ ሁላችሁንም ብንሸልም ደሰ ባለን ነበር… ግን ለሁላችሁም የሚሆን አንድ ስጦታ አለን እሱም ልባችን ነው›› ብለዋል፡፡

ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳና ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ረዘም ያለ ንግግር አድርገው ፕሮግራሙ ተፈጽሟል፡፡