Seye Abraha’s trademark arrogance endures

The following Amharic article by editor-in-chief of Awramba Times analyzes recent political developments in Ethiopia involving the Addis Ababa-based opposition parties, particularly the joining of UDJ by two former high level Woyanne officials — Defense Minister Seye Abraha and President Negasso Gidada. The writer hammers Seye Abraha as incurably arrogant.

ስዬ ወደ አንድነት፤
የገነቡትን ለማፍረስ ወይስ ያልዘሩትን ለማጨድ

በዳዊት ከበደ

[pdf]

የቀድሞው የኢህአዴግ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር ስዬ አብርሃ አንድነት ፓርቲን በይፋ መቀላቀለቸው የሰሞኑ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ባለፈው ሐሙስ አቶ ስዬና ዶ/ር ነጋሶ አንድነት ፓርቲን በይፋ የመቀላቀላቸውን ዜና በውጭ ድረገጾች ሲቀርብ ኢትዮጵያዊያን በዜናው ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡ በኤሊያስ ክፍሌ የሚመራው ‹ኢትዮጵያን ሪቪው› ድረገጽ ለምርጫ እየተዘጋጁ ያሉ የኢትዮጵያ ፓርቲዎች በሁለት ጎራ ይከፍላቸዋል፡፡ በሁለቱም ጎራ ያሉ ተፋላሚዎችም ኢህአዴግ መሆናቸውን ገልጾ መጪው ምርጫ በሁለት ኢህአዴጎች መካከል የሚደረግ ምርጫ ነው ብሎታል፡፡ እሱም በአንድ በኩል መኢአድን ያቀፈውና በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞ ኢህአዴግ አመራሮችን ያቀፈው አንድነት/መድረክ ነው ይላል፡፡

‹ናዝሬት› ድረገጽ በኩሉ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በዚህ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡ ባቀረበው ጥሪ መሰረት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አሰተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከጥቂቶቹ በስተቀር የበርካቶቹ አስተያየትም አሉታዊ ነበር፡፡ በተለይ አንድ አስተያየት ሰጪ ‹እነ ስዬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጓደኞቼን ያስጨፈጨፉና ለበደኖና አርባጉጉ እልቂት ተጠያቂ ናቸው፡፡ እነሱ አንድነት ፓርቲ ሳይሆን ዘ ሄግ ፍርድ ቤት ውስጥ መግባት አለባቸው የሚል አስተያየት አስፍሯል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ደሳለኝ አስፋው የተባሉ ፀሐፊ በ‹ኢትዮፖለቲክስ› ድረገጽ ላይ እርምጃውን በጎ ጅምር ሲሉ አድንቀዋል፡፡ በእለቱ ‹ኢትዮፎረም› ላይ አስተያየት ከሰጡ ኢትዮጵያውያን መካከልም ብዙዎች ለግለሰቦቹ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡

ምርጫው እንደመቃረቡ መድረክ በአንድ የመወዳደሪያ ምልክት ግለሰቦቹን አቅፎ ምርጫ ውስጥ ለመግባት ሰዎቹ ከመድረክ አባል ፓርቲዎች ውስጥ ወደ አንዱ መቀላቀላቸው የግድ ነበር፡፡ በብዙዎች ዘንድ የነበረው ግምት ዶ/ር ነጋሶ ኦፌዴንን አሊያም ኦብኮን አቶ ስዬ ደግሞ ከህዋሀት የተሰናበቱ ጓዶቻቸው በመሰረቱት አረና ፓርቲ ውስጥ ይቀላቀላሉ የሚል ሰፊ መላምት ነበር፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ከቀድሞ ጓዶቻቸው ጋር የዘር ፖለቲካ በሀገሪቱ ስር እንዲሰድ አይነተኛ ሚና የተጫወቱ እንደመሆናቸው ከዚህ ማዕቀፍ ወጥተው አገር አቀፍ ፓርቲ ውስጥ በመግባት ደጋፊን ለማሰባሰብ መሞከር ‹ያልዘሩትን እንደማጨድ› ስለሚቆጠር ነው፡፡ እንደውም ቀላል በማይባሉ አክራሪ ደጋፊዎቻቸው ዘንድ እንደ ክህደት ሊያስቆጥርባቸው እንደሚችል ብዙዎች ግምታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ስለሁለቱም ይህን ያህል ካልኩኝ ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ልግባ፡፡

ከበርካታ ወራት በፊት፥ ሚያዝያ 15 ቀን 2000 ዓ.ም ረፋዱ ላይ አቶ ስዬ ስልክ ደወሉልኝና ‹ጊዜ ካለህ እቤት መጥተህ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ እንዲሁ በግል እንድንወያይ ፈልጌ ነበር› አሉኝ እኔም ደስተኛ መሆኔን ገልጬ ወደ አቶ ስዬ መኖሪያ ቤት አቀናሁ። ስለ አገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣ በወቅቱ ስለነበረው የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ፥ እንዲሁም ስለገዢው ፓርቲ አንዳንድ ሀሳቦች አንስተን ተወያየን። ዛሬ ስለ ያኔው ውይይታችን ሳስብ የአሁኑ የአቶ ስዬ ውሳኔ ግራ አጋብቶኛል፡፡ በወቅቱ የነበረው የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ የጠራ መስመር አልያዘም ነበር፡፡ እነ ወ/ት ብርቱካን አንድነትን አልመሰረቱም። እነ ኢንጅነር ኃይሉም በይፋ ወደ መኢአድ አልተመለሱም፡፡ ዶ/ር ብርሃኑም በሰላማዊ ትግል ተስፋ መቁረጣቸው ይገለጽ እንጂ ግንቦት 7 ንቅናቄን አልመሰረቱም ነበር፡፡ ሁሉም ግን በየፊናቸው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ (ስማቸው በኢህአዴግ ቢነጠቅም) የቅንጅት አመራሮች እየተባሉ ነበር የሚጠሩት፡፡ ከአቶ ስዬ ጋር በነዚህና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳብ ከተለዋወጥን በኋላ አቶ ስዬ ‹ምናልባት ከዶ/ር ብርሃኑ ጋር መግባባት ይቻል ይሆናል፤ ከሌሎች ጋር ግን አብሮ መስራት የማይታሰብ ነው፡፡› አሉኝ፡፡ ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን አስረግጠው ነገሩኝ፡፡ አንዱ ምክንያታቸው ይደግፈኛል ብለው የሚተማመኑበት የትግራይ ህዝብ በ1997 ምርጫ ሙሉ ድጋፉን ለህወሓት የሰጠ ከመሆኑም በላይ ገዥው ፓርቲ ቅንጅትን ከ‹ኢንተርሃምዌ› ጋር በማያያዝ ትግራይ ውስጥ ሰፊ ቅስቀሳ ማካሄዱን አስታውሰው ዛሬ ከቅንጅት አመራሮች ጋር ጥምረት ፈጥሮ ትግራይ ውስጥ ድጋፍ ለማሰባሰብ መሞከር ከባድ እንደሚሆን ስጋታቸውን ገለፁልኝ፡፡ ከዚህ ጋርም አያይዘው አሜሪካ ውስጥ ከዶ/ር ብርሃኑ ጋር ፖለቲካዊ ውይይት ስለማካሄዳቸው ኢህአዴግ ሆን ብሎ የነዛው እና ስዬ ቅንጅት ሆነ ብሎ በትግራይ ህዝብ ዘንድ እንዲጠሉ ለማድረግ የሸረበው ሴራ መሆኑን አጫወቱኝ፡፡ በውይይታችን መሀል ያነሳነው ሁለተኛው ነጥብ የተቀዋሚዎች መንደር ‹የንትርክ አውድማ› የመሆኑ ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህ ዙሪያ አቶ ስዬ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተመሳሳይ አቋም እንደነበራቸው ግልፅ ነው፡፡ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ ከአንድነት ወጣቶች አባል እንዲሆኑ ለቀረበላቸው ጥሪ ‹አንድነት ያልተሰራ ቤት ነው፡፡› በማለት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡ ታዲያ ያ ያልተሰራ ቤት ከመቼው ተሰርቶ ዛሬ ለአቶ ስዬ ዝግጁ ሆነ? መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፡፡

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁለቱም አንድነት ፓርቲ ውስጥ መግባታቸው አልቃወምም፡፡ ከዛ ባሻገር ግን ዶ/ር ነጋሶ በይፋ የሰሩት ስዬ ግን ‹በመቃበሬ ላይ› የሚሉት አንድ ወሳኝ የቤት ስራ መኖሩን ግን መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ አቶ መለስ ባለፈው አመት የተከሰተውና መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ያስከተለውን የኤሌትሪክ መቋረጥ አስመልቶ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንዲጠይቁ ከተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ጥያቄ ሲቀርብላቸው ‹ድህነት ይቅርታ ይጠይቃችሁ እንጂ እኔ አላደርገውም› ማለታቸውን እናስታውስ፡፡ በመሰረቱ የምትመራውን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ የአክብሮት እንጂ የሽንፈት መገለጫ አይደለም፡፡ ለኢህአዴግ መሪዎች ግን ይቅርታ መጠየቅ የአለም ፍጻሜ ነው፡፡ አቶ ስዬም በይቅርታ ላይ ያላቸው አቋም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የህወሓት አክራሪነት ባህሪ እስካሁን እንዳልለቀቃቸው ከማሳየት ውጪ ሌላ መልዕክት የለውም፡፡ አቶ ስዬ ከ1968 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 1993 ዓ/ም ድረስ በከፍተኛ ወታደራዊ አመራርነት ደረጃ ጥሩ አዋጊና ተዋጊ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ ከ1983 ዓ/ም እስከ ተሰናበቱበት 1993 ዓ/ም ድረስ በተለያዩ የመንግስትና የፓርቲ ኃላፊነት ላይ አገልግለዋል፡፡ መከላከያ ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሊቀመንበር፣ በአሁኑ ወቅት በአዜብ መስፍን የሚመራው ኤፌርት ዳይሬክተር፣ የፓርላማ አባል፣ የህወሓት ፖሊት ቢሮ አባል እንዲሁም የሌሎች በርካታ ሹመቶች ባለቤት ሆነው ‹ጦርነትን መፍጠር እንችላለን› እስከማለት የደረሱት ሰውዬ ‹ንፁህ ሰው ነኝ ይቅርታ አልጠይቅም› ሲሉ አሳማኝ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ዶ/ር ነጋሶ ባለፈው ሀሙስ የኢትዮጵያን ህዝብ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ በርግጥ ከዛም በፊት በተደጋጋሚ ‹ሳላውቅ ተታልዬ መጠቀሚያ ሆንኩ› ሲሉ ብዙ ጊዜ ተደምጠዋል፡፡ ብዙ ሰዎች የዶክተሩን አባባል ‹የመለስ መጠቀሚያ ነበርኩ› የሚል አንድምታ እንዳለው አድርገው ይመለከታሉ፡፡ በኔ እምነት ይህ የዋህነት ነው፡፡ ነጋሶ ኢህአዴግ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ስዬ ከመለስ ባልተናነሰ ሁኔታ የህወሓት አድራጊ ፈጣሪ እንደነበሩ መዘንጋት የለብንም፡፡ እናም ነጋሶን መጠቀሚያ በማድረጉ ሴራ ውስጥ ስዬ ጭራሽ የሉበትም ማለት ዘበት ነው፡፡ ነገር ግን ነጋሶ ይቅርታ ሲጠይቁ ስዬ ግን እምቢተኛ የሚሆኑበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ በ2000 ዓ/ም መጀመሪያ ወራት አቶ ስዬ ወደ አሜሪካ አቅንተው ኢትዮጵያዊያንን ባነጋገሩበት ወቅት ይቅርታ ይጠይቁ ዘንድ ሀሳብ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ስዬ ግን አስቂኝ ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡ እንዲህም አሉ ‹እዚህ አዳራሽ ውስጥ የኢህአፓ አባላት የነበራችሁ፣ ደርግ ውስጥ ያገለገላችሁ፣ መኢሶን የነበራችሁ ልትኖሩ ትችላላችሁ፡፡ ሁሉም በየፊናው ስህተት ሰርቷል፡፡ ነገር ግን ሁላችንም የይቅርታን ሂሳብ በማወራረድ ጊዜ ከምናጠፋ ለወደፊት ምን ማድረግ እንዳለብን ብንወያይ ይሻላል፡፡› ነበር ያሉት፡፡ ይህ አባባል ለኔ አሳማኝ አልመሰለኝም፡፡ የራስን ጥፋት የደርግ አባላት ከሰሩት ጥፋት ጋር እያነፃፀሩ እናንተ ካልጠየቃችሁ አልጠይቅም ማለት በትጥቅ ትግል ከተፋለሟቸው ሰዎች ጋር ራስን ማወዳደር ብቻውን ይቅርታ ያስጠይቃል፡፡

አንድ ነገር ግልጽ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ ጉዳዩ የስዬ ይቅርታ የመጠየቅ ያለመጠየቅ ግለሰባዊ ጉዳይ ብቻ ሆኖ መታየት የለበትም፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ አመኔታን አግኝቶ ወደ ፊት ለመራመድ ምርጫው ይሄ ብቻ ስለሆነ እንጂ፡፡ አለበለዚያ ግን ‹ቂም ይዞ ፀሎት› ይሆናል፡፡ ይቅርታ የመጠየቅ ክቡር ስብዕና የተመካው ለኢትዮጵያ ህዝብ ከሚኖረው አክብሮትና እንዲፈጠር ከሚፈለገው የመቻቻል ሰርዓት አንፃር እንጂ በተለያየ ተሳትፎ ውስጥ ያለፉ ሌሎች ወገኖች ለጉዳዩ በሚሰጡት ምላሽ የሚሆንበት ምንም ስነ አመክንዮ የለም፡፡ ሌሎች አካላት ይቅርታ አለመጠየቃቸው ከደሙ ንፁህ የመሆንን ዋስትናም አያጎናጽፍም፡፡

ሰሞኑን አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሚጠበቅብንን ያህል አልሰራንም ብለው ይቅርታ እየጠየቁ ባሉበት ሁኔታ የገዥ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የነበረ ሰው ‹ድሮም አሁንም ትክክል ነኝ› ብሎ የተቃዋሚዎችን መንደር በነፃነት ሲቀላቀል አንድም የተቃውሞ ጎራውን ከልቡ አላመነበትም አሊያም ደግሞ እራስን በሰማየ ሰማያት ላይ ከማስቀመጥ የመነጨ ግለሰባዊ ጀብደኝነት ነው፡፡

አንድነት ፓርቲም ህዝብን የሚያከብር ከሆነ እንዲህ አይነቱን ውዥንብር አጥርቶ መሄድ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ፕሬስ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ ተጠያቂነት እንዲኖር፣ አምባገነኖች የሚያራምዱትን ኢዴሞክራሲያዊ አሰራር እንደሚኮንን ሁሉ ተቃዋሚዎች ውስጥም ችግር ሲኖር ፕሬሱ ችግሩን ማጋለጥ አለበት፡፡ በግሌ አንድነት ውስጥ አንድ መሰረታዊ ችግር ይታየኛል፡፡ ፕሬስ ገዥውን ፓርቲ ብቻ እንዲኮንን፣ እንዲያጋልጥ አንድነት ውስጥ ያለውን ድክመት ግን አይቶ እንዳላየ አድበስብሶት ብቻ እንዲያልፍ ግዴታ ያለበት አድርጎ እንዲገነዘብ የማድረግ ችግር ይታየኛል፡፡ የውስጥ ችግራችንን ማንም አይስማው፤ የፕሮፌሰር እከሌን መጣጥፍ ለምን አተማችሁ ብሎ ፕሬስን ማሳቀቅ ፓርቲው ከቅንጅት ይልቅ ‹የኢህአዴግ ሞራላዊ ወራሽ› እየሆነ መሄዱን ያሳያል፡፡

ለዚም ይመስላል አቶ ስዬ ከባህሪያቸው ጋር የሚጣጣም ፓርቲ መርጠው የተቀላቀሉት፡፡ በጥር ወር 2000 ዓ/ም ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የስዬን ቃለምልልስ መነሻ በማድረግ በፃፉት መጣጥፍ ‹ስዬ ተለውጧል› ብለው ነበር፡፡ እኔ ግን በፕሮፌሰሩ አባባል አልስማማም፡፡ ስዬ በጭራሽ አልተለወጡም፤ አሁንም አምባገነን ናቸው፡፡

በሚያዝያ እና ግንቦት 2000 ዓ/ም ከአውራምባ ታይምስ ጋር ሁለት ጊዜ ሰፋፊ ቃለምልልስ አካሂደው ነበር፡፡ በወቅቱ የአንባቢ አስተያየት ምን እንደሚመስል በየሰዓቱ እየደወሉ ይጠይቁኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የተስፋዬ ገ/አብ የጋዜጠኛው ማስታወሻ መፅሐፍ የካቲት 10 ቀን 2001 ዓ/ም ዳሰሳው በአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ሲሰራ ስዬን በተመለከተ ደራሲው ያሰፈረውን ፅሁፍ በጋዜጣው ላይ በከፊል መጠቀሱ ክፉኛ አበሳጭቷቸዋል፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ደራሲው አቶ ስዬን በመልካም ሁኔታ አልጠቀሳቸውምና ጋዜጣው ዳሰሳውን ሲሰራ ምን ማድረግ እንደነበረበት ባይገባኝም፤ አውራምባ የሳቸውን ‹መልካም ገፅታ› ብቻ የመፃፍ ግዴታ የተጣለበት ይመስል መበሳጨታቸው እጅግ አስገርሞኛል፡፡ በርግጥ አቶ ስዬ ለረጅም አመታት ካካበቱት ‹ነገሮችን በጉልበት የመፍታት ልምድ› አንፃር ለሰላማዊ ትግል አዲስ ስለሆኑ ለእርሳቸው የሚቀርብ የትግል ስልት ከሚከተሉ ወገኖች ጋር መቀላቀል ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን በሰላማዊ ትግል ቆርበናል ከሚሉት ጋር እስከቀጠሉ ድረስ ትእግስት የግድ ነውና በተለይ ሀሳብን በነፃ የመግለጽ መብትን ሊያከብሩ ይገባል፡፡ የትግል ስልትም ቢቀይሩ ይህንን መሰረታዊ መብት ማክበር ግድ ይላልና::

(ዳዊት ከበደ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ነው)