Assimba.org responds to Dawey Ibrahim

Assimba.org has issued the following press release in Amharic regarding comments by Ato Dawey Ibrahim, former chairman of the Ethiopian Workers Confederaiton. (Amharic font can be downloaded here).

አቶ ዳዊ ኢብራሂም በአሲምባ የውይይት መድረክ ላይ ለሰነዘሩት አስተያየት የተሰጠ ምላሽ

በስደት የሚኖሩ ወገኖች ከመካከላቸው አንዱ የማይመስል ሲያወራ “ስደት ለወሬ ያመቻል” ይላሉ። እንዲያም ሲል ተንኮል የተሞላበት ፈጠራን ሲገነዘቡ “ጅብ ከማያቁት ሀገር ሄዶ ቆርበት አንጥፉልኝ አለ” ይላሉ። ከጥቂት ቀናት በፊት “የኢሕአፓና ትርምሰ ዑደትና የኢትዮጵያ ሠራተኞች” በሚል ርዕስ በአቶ ዳዊ ኢብራሂም ተጽፎ በአንዳድ ድረ-ገጾች ከተበተነ በኋላ በአንዳንድ የፓልቶክ መድረኮች ይህን ጽሁፍና ያአሲምባ ድረ-ገጽንና ሌሎችን በሚመለከት በኛ ግምት ኃላፊነት የጎደለውና ከዕውነት የራቀ ተራ ወሬ ሲነዛ በመክረሙ በጣም አዝነናል። በተለይም አቶ ዳዊ ከሦሥት ወራት በፊት በአሲምባ የውይይት መድረክ የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን አንተርሶ የአቀረብናቸውን በስደት የሚገኙ የቀድሞ ሠራተኞች መሪዎችን አስመልክቶና የአሲምባ የውይይት መድረክን ተልዕኮ አጣመው የራሳቸውን ትርጉም በዘፈቀደ ለማቅረብ በመሞከራቸው ይህንን መግለጫ እንድናወጣ ተገደናል። ከዚህም በላይ የሳቸውን ጽሁፍና በዕለቱ ከእንግዶቻችን ጋራ ያደረግነውን ቀለ-መጠየይቅ እንዳለ እቅርበን ፍርዱን ለአንባብያን እንተወዋለን።በመጀመሪያ የአሲምባ ውይይት መድረክ እንዴትና ለምን ተመሠረተ?

አቶ ዳዊ እንደጻፉት የአሲምባ የውይይት መድረክ የኢሕአፓ ተለጣፊ አይደለም። በጥቂት ሀገር ወዳዶች የሚንቀሳቀስ ከማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ነጻ የሆነ ፤ ዘለቅ ብሎ የተገለጸውን ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ መሆኑን እንዲገነዘቡልን እንወዳለን። ይህንንም ስንል ግን ኢሕአፓ የኢትዮጵያ የቁርጥዬ ቀን ጀግኖች በደም አጥንታቸው የገነቡት ዕውነተኛ ሕዝባዊና ኢትዮጵያዊ ድርጅት መሆኑን ላንዴም አንጠራጠርም። ኢትዮጵያዊነቱን ለሚጠይቁ በድረ-ገጻችን በየቀኑ እያደገ ያለውን የሰማዕታት ስም ዝርዝርና አጠር ያለ ታሪክ ላስተዋለ ፣ በስማቸው ብቻ በኢትዮጵያ ያሉትን ብሔሮች፣ ሃይማኖቶችና የሥራ ዘርፎችን እንደሚያንጸባርቁ መረዳት ይችላሉ። ይህም ራሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሞላ ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሶ በደሙ የጻፈው ዕውነተኛ ታሪኩ ነውና ዛሬ የትግራይ ተወላጅ ብቻ ለትግራይ ሕዝብ ወይም የኦሮሞ ተወላጅ ብቻ ለኦሮሞ ሕዝብ ወዘተ,,ሃሳቢና ተቆርቋሪ እንደነበሩ አድርገው ሊያስተምሩን የሚዳዳቸውን ሁሉ ከሚያስፋፉት ጥላቻና ድንቁርና ጋር እርቃናቸውን ያስቀረዋል።

መድረኩም ሆነ ድረ-ገጹ በተመሠረቱበት ወቅት የወያኔ መንግሥት በዘጠና ሰባቱ ምርጫ ማግስት ያታልልበት የነበረውን የዲሞክራሲ ሽርጥ አውልቆ ጥሎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድሮውንም ግልጽ የነበረውን ፋሻሽታዊ ገጽታውን ይዞ በዓለም መድረክ ላይ ብቅ ያለበት የቀውጢ ጊዜ ነበር። ይህም ሁኔታ አዲሱ ትውልድ ለሚጠብቀው መራራ ትግል፤ ሊመረምረውና ሊማርበት የሚገባ፤ በዛሬዪቱ ኢትዮጲያችን የተንሠራፋው የዘረኞች፤ የጎጠኞችና፤ የሆዳሞች መንጋ አቶ ዳዊ እያደረጉት እንዳሉት ሁሉ የሚከላልሰውን፤ በጀግንነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባላቸው ፍቅር፤ ለፍትኅና ለዲሞክራሲ፤ በውድ ሕይወታቸው ምስወዕትነት ያዳበሩትን የዚያን ትውልድ ጅግኖች የትግል ታሪክ፤ ሳይቀነስ፤ ሳይበረዝና ሳይደለዝ፤ አሁንም በሕይወታቸው ከሚኖሩ የትግል ጓዶቻቸው፤ የሥራ ባልደረቦቻቸው፤ ወዳጆቻቸውና ቤተ-ዘመዶቻቸው ተሰባስቦ፤ ዕውነቱ በትክክል እንዲቀርብ ለማድረግ የጀመርነው ውጥን ወይም ፕሮጀክት ነው።

ከዚህም ሌላ ይህ መድረክ ባለፉት አርባ ዓመታት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትኃዊ ነፃነት ሲታገሉ ለወደቁ፤ በደርግ ፋሺሽታዊ ሥርዓት በቀይ ሽብር ሠለባ ለሆኑ፤ ለሕዝባችን ነፃነት እንታገላለን በሚሉ ጠባብ ብሔረትኞች ለተጨፈጨፉ፤ በፅናታቸው፤ በኢትዮጵያዊነታቸው ተግዘው ለማቀቁና አሁንም በየጉድባው አሣራቸውን ለሚቆጥሩ፤ ከምድረ-ገጽ ደብዛቸው ለጠፉ የቁርጥዬ ቀን የኢትዮጵያ ጀግኖችና በዓለም ዙሪያ ካለውዴታቸው ተሰደውና በሀገር ቤትም አንገታቸውን ደፍተው ለሚኖሩ ታጋዮች መተሰቢያ እንዲሆን አስበን የመሠረትነው እንጂ አቶ ዳዊ እንደለጠፉብን ሴረኞች አይደለንም። ሥራችንም ሃላፊነት የተሞላው ለመሆኑ በግልጽ በውይይት መድረኩም ሆነ በድረ-ገጹ የሚንጸባረቅ ስለሆነ በተዘዋዋሪም መንገድ ጸረ-ቅንጅት አድርገው ሊቀቡን የሚሞክሩትን ሁሉ አንቀበላቸውም።

እንግዲህ ይህንን ግልጽ ካደረግን በኋላ በአቶ ዳዊ ጽሁፍ ላይ በጥቅሉ የተገነዘብነው ነገር ቢኖር የደርግ ፋሺሽቶችና ግብረ-አበሮቻቸው ያፈሰሱትን ደም ከጃቸው ያነጹ እየመሰላቸው በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሏቸውን፤ ያረዷቸውን፣ በዘይት የቀቀሏቸውን ኸረ ስንቱን ይገባቸዋል ብለው የሚያቅራሩትን ያክል በሚያሳዝን ሁኔታ እኚህም ሰው በዚህ ጽሁፋቸው በአጠቃላይ የፋሺሽቶች ሰለባ የሆኑትን ወገኖቻችንን የሙት ወቃሽ መሆናቸውን ነው። በአሲምባ ደግሞ ይህን ዓይነት የተንሸዋረረ ታሪክ የሚያቀርቡትን ለማስተካከል ስለቆምን እንዳለፉት ሃያና ዓመታት ተድበስብሶ የሚቀር የለምና እንግዲህ አረፍ ይበሉና እስኪ ከላልሰው ካቀረቡት የሰማዕታት ታሪክ መካከል ጥቂቱን እንስተን በጥሞና እንወያይ። ከዚያ በፊት ግን እንዲያውቁልን የምንሻው ኢህአፓ በዓለም ዙሪያ ሕጋዊ ጽ/ቤቶች ፣ የራዲዮ ጣቢያዎች ፣ የራሱ ድረ-ገጽና “ዲሞክራሲያ” ልሣኑ ያለው ድርጅት ስለሆነ በድርጅቱ ያቀረቡትን ክስ መልስ እንደማይነፍገዎ እንተማመናለን።

በመድረካችን ባሉት ቀን ቀርበው ውርጅብኝ ያወረዱባቸው እንግዶቻችንም እንዲሁ መልስ የሰጥዎታል ብለን እንገምታለን። ከዚህ ጽሁፍም ጋር አባሪ አድርገን ዝግጅቱን ያቀረብን ዕለት ውይይት ቅጂ እንደሚያመለክተው የእርስዎ ስም በመጥፎ አልተነሳም፣ ቅጂውን እንዲያዳምጡም እንጋብዞታለን። አንባቢያንም የአቶ ዳዊ ኢብራሂምን ጽሁፍ የኛን መልስ እንዲሁም የውይይቱን ቅጂ በማድመጥ በዕለቱ የውይይቱ መንፈስ ምን እንደነበር ያራሳችሁን ግንዛቤ እንደምትወስዱ አንጠራጠርም።

የምንተችባቸው ጽንሰ ሃሳቦች

1. በእርስዎ የደበዘዘ መነጽር ተመልክተው ደርግ በ1968 ዓ/ም ዲሞክራሲያዊ እንደ ነበር ሁሉ በዚያን ሜይ ዴይ የፈጸመውን እልቂት በኢህአፓ ተንኳሽነት እንደሆነ አድርገው ለማቅረብ መሞከርዎ የታሪክ ክለሳ ነው። ከጻፉት ለመጥቀስ “…በ1968 ዓ/ም ሜይ ዴይ በሚከበርበት ዕለት በዓብዮት አደባባይ ሠራተኞችን የማስመታትና ከሠራተኞች መሞት ስለደርግ ጨካኝነት ማስረጃ ለመፈልቀቅ የፈጸመችው መሠሪ ተግባር… ሠራተኛው ሕንፃ ላይ ለተጠመዱ መትሪየሶች የእሳት ዕራት እንዲሆን አደረገች…” ብለው የዚያን ትውልድ ሰማዕታት ወቃሽ ሆነው ተሰልፈዋል።

ዛሬ ሀገራችን እንደ ሀገር የምትቀጥልበትን ሁናታ በጥያቄ ውስጥ ያስገባውን ወያኔን አስወግደን በምትኩ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመሥረት ኢትዮጵያዊ ኃይሎችን ወደ አንድ ወገን እንዴት ማምጣት የቻላል ብለው ሀገር ወዳዶች ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሚጨነቁበት ወቅት እርስዎ ታሪክን የሚያውገረግር ተራ ወሬ የአሲምባንም ሚና ያጣመመ አጀንዳ ሲያሲዙን ማንን እየጠቀሙ መሰለዎት? ከፍተኛ መስዋዕትነት እየተገበረበት ያለን ሕዝባዊ የዲሞክራሲ ትግል እየጠቀሙ መሰለዎት? ኢሕአፓ የወያኔን ጠባብነት አውቆ ታጋዮቹን የገበረው ዛሬ አይደለም። ገና ከመነሻቸው ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ነውና ያም ጥፋቱ ነው ብለው ያስተምሩን ይሆን? ከ1991 ዓ/ም ወያኔዎች ደብዛቸውን ላጠፏቸው አባላቱ፣ በአደባባይም ለገደሏቸው ታጋዮቹ ጥፋቱ የኢሕአፓ ነው ይሉን ይሆን?

ለማንኛውም ከላይ ከጽሁፎ ለጠቀስነው ዕውነታውን እንመልከትና በዚያን ቀን ማለትም ሜይ ዴይ 1968 ዓ/ም ልክ በ1997 ዓ/ም የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔን ምንነት አንቀርቅቦ እንዳወቀ ሁሉ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠራተኛውንም ጨምሮ የደርግን ምንነት በግብሩ የተረዳ ስለነበር በዚያን ዕለት ሠራተኛው “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አሁኑኑ!” የሚሉ መፈክሮችን አንግቦ መውጣቱ፤ ብሎም በጊዜው የሕዝቡን ዋይታ ያንጸባርቅ የነበረውና ሕዝቡንም አደራጅቶ ያታግል የነበረ የሕዝቡ ፓርቲ ኢህአፓ ብቻ ስለነበር፤ “ኢህአፓ ፓርቲያችን ነው!” በሎ መፈክሩን በአደባባይ የዞ መውጣቱ ያስቆጣቸው የደርግ ባለሥልጣናት የፈጸሙት ይቅርታ የሌለው ጭፍጨፋ ነው።

ለመሆኑ እርስዎ በጽሁፎ ኢህአፓ ያንን ቀን የደርግን ፋሺሽትነት ለማስመስከር ተጠቀመበት የሚሉን ከዚያ በፊት ደርግ በሥልጣን ከወጣ ጀምሮ በግልጽ ያስመሰከረውን ካለፍርድ ሲሻው በአዋጅ የፍየል ወጠጤ በራዲዮ እያዘመረ ይገድል እንደነበር ፤ አለያም የደርግ አባላትና ተጠሪዎቹ በደረሱበት ቦታ ተቃዋሚ ተብለው የሚጠረጠሩትን የሠራተኞች ተሟጋቾችንም ጨምሮ ማለት ነው ይረሽኑ ያሰቃዩ እንደነበር እረስተውት ነው? ወይስ ዛሬ ለፖለቲካ ሥልጣን ራስን ለማመቻቸት ኢሰፓዎችን ማሞካሸት ይሻላል ብለው ገመቱ? ወይስ ተልኮዎ ረቀቅ ያለ ኢትዮጵያዊው ኃይል ወዳንድ እንዳይመጣ የመከፋፈያ መርዝ መርጨትዎ?

እንግዲህ ታሪክን እንደ ታሪክነቱ እንዲከለስ መፍቀድ ለወደፊት ለምናደርገው ትግል ጥራትን ከማሳጣቱም ሌላ ስህተቶች እዲደገሙ መሠረት ስለሚሆኑ በኛ በኩል እንዲህ ያለውን የውሸት ዘመቻ እየሰማን ዝም ማለቱ ጉዳቱ እንጂ ጥቅሙ ስላልታየንና የርስዎንም የመዋሸት ችሎታ ህዝቡ እዲረዳ በማድረግ በመድረካችን የተካሄደውን ውይይት ቅጂ እንዳለ በማቅረብ እንዴት ሊያጣምሙት እንደሚሞክሩ አሳይተን የርስዎና የመሳሰሉትን የተዛቡ አስተያየቶችን እንደዕውነታ ወስደን የተሳሳተ ግምት ውስጥ ከመግባት በፊት ሁሉም ወገን የሚያቀርበውን ተመልክቶ ትክክለኛው የትኛው እንደሆነ ከድምዳሜ መድረስ እንደሚቻል ለማሳየት ነው።

የአቶ ዳዋን የ1968ቱን የሜይ ዴይ ታሪክ እንኳ ይሁን ብለን ብንቀበል ፣ በዛሬዎቹ የጎጠኞች መንግሥት ከ1997 ዓ/ም በኋላ የሕዝብ ድምፅ ይከበር ብለው ሰላማዊ ሠልፍ ሰለወጡ ብቻ ለተጨፈጨፉ ወገኖች ተጠያቂዎቹ ታሥረው የነበሩ የቅንጅት መሪዎች ናቸው የሚሉንን ልንሰማ ነው ማለት ነው።

ከታሪክ ያልተማሩ ታሪክን ይደግማሉና በ1968 የተፈጸመን በደል ትክክለኛ ምንጩንና በጊዜው የነበረውን ሁኔታ በትክክል እንዳይጤን አውቀውም ሆነ ሳያውቁት ያ ትውልድ ከልቡ አምኖ ለወገኖቹ በቅንነት መሥዋዕትነት የከፈለበትን ታሪክ መከላለስ አዳጋው የዛሬው ትውልድ የአለፈውን ትውልድ ድክመቱን ሳይደግም ግን ከጠንካራ ጎኑ በተለይም ለሀገርና ወገን ያለውን ፍቅር እዲሁም በራስ መተማመንና ጀግንነትን ሰንቆ ለኢትዮጵያችን ያለናት እንደ አባቶቻችን እናቶቻችን እኛው በኢትዮጵያ የምንኮራ ሀገር ወዳዶች ብቻ መሆናችንን በቶሎ ተገንዝቦ እንዳይታገል ነገሮች እየተምታቱበት ፈራ ተባ እያለ እንዲጃጃልና ሀገሩን እንዲነጠቅ ማድረግ መሆኑን ልናስገነዝብ እንወዳለን።

ይህ ደግሞ ኢህአፓ ነበርን፤ ታሪኩን ከኛ የበለጠ የሚያውቅ ላሳር ነው እያሉ የዚያን ትውልድ ሰማዕትነት እያደባዩ ድርሳነ ክህደት የሚያነበንቡትንም ስለሚመለከት ፤ ሁሉም አንድ እንዲረዱልን የምንፈልገው ነገር ቢኖር፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጊዜና ሁኔታዎች ሲመቻቹለት የኢህአፓንና የዚያን ትውልድ መስዋዕትነት ዕውነተኛውን ታሪክ እንደሚናገር በፍጹም አንደማንጠራጠር ነው።

2. የዚህ ምላሽ ዋና ዓላማ አቶ ዳዋ ኢብራሂም የጻፉትን 6 ገጽ የታሪክ ክለሳ መስመር በመስመር ልንተችበት ሳይሆን ቢያንስ አንድ ሁለቱን አንስተን የቀዳዳውን ስፋት በህዝብ መነጽር እንዲታይ በማድረግ የዚያ ትውልድ ታሪክ በብዙ ሊመረመርና ሊጠና የሚገባው፤ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው የምናየው ታሪክን የሚያንቋሽሽ ወሬና አሉባልታ እንዴት ወደ ሕዝቡ ዓዕምሮ ሰርፆ እንዲገባ እየተቀረገ እደሆነ ለማሳየት ብቻ ስለሆነ በዚህ ክፍል አንድ ነጥብ አንስትን እንተችበትና ወደ ማጠቃለያችን እንሄዳለን።

አቶ ዳዊ ኢብራሂም ሲጽፉ “…ከ1967 እስከ 1969 ዓ/ም ድረስ ኢህአፓ በኢትጵያ ሠራተኞችና ማህበሮቻቸው ያደረሰችው ጉዳት ይቅር የማይባል ዘግናኝና አሳዛኝ እንደነበር…” ይሉና ቀጠል አድርገውም “…ሥዩም ከበደ የኢህአፓ የትጥቅ ትግል (እነሱ እንደሚሉት የጥቃት መከላከያ) ዋና መሪ ስለነበር የሠራተኛውን ብሔራዊ ጽ/ቤት የግድያ ዕቅድ ማውጫ፤ …የመቺ ቡድን መጠለያና መሸሸጊያ፤ …የማህበሩ ሕንፃ ከመሬት በታች ምድር ቤት ስለነበረው የጦር መሳሪያ መደበቂያ ምቹ ሥፍራ አድርጋ ቆየች…” ብለው ይቀጥላሉ። ምናለ የሚመስል እንኳ ቢያወሩልን። ሥዩም ከበደና ኢህአፓ ያበዱና ሞትን ያሸተቱ ካልሆነ በቀር፣ በጊዜው ደርግ የሠራተኛውን ድርጅታዊ ነፃነት በራሱ ታማኝ መሪዎች ለመተካት እየታገለና እያስፈራራ እርስዎም ያልካዱት ደጋፊ ነን የሚሉ ውሁዳን መሪዎች እንደ ጣዕም ያለው እሸቴ አይነቱ ነገር አቀባዮች በሚርመሰመሱበት ጽ/ብት ውስጥና፤ ከሁሉም በላይ የደርግ የስለላ መረብ 24 ሰዓት በዓይነ ቁራኛ የሚጠበቀውን ህንፃ ወደ ምሽግነት ኢህአፓ ቀየረችው በሎ እንደ ታሪክ ማውራት የሚያሳፍር ቅጥፈት ነው። ለርስዎ አፈርንልዎ።

ሌላው ደግሞ ያኔ ደርግ ኢህአፓዎችን እያደነ ሲገድል “ሥርዓተ-አልበኞች” እያለ እኒያን ሰማዕታት ሰብአዊ ገጽታ እንዳይኖራቸው ግን ግዑዝ ከም አርዮስ መልክ በመቀባት፤ ቢገደሉም ምንም አይደለም አይነት ነገር በሕዝቡ እዕምሮ ይቀርፅበት የነበረውን የጭካኔ ቋንቋ ከሠላሣ ዓመት በኋላ ይዘው ብቅ ሲሉ ዛሬም እንደ ትላንቱ የሚኮንኑት መሠረታዊ የስብአዊ መብቶችን ፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ካለገደብ መጠየቅን፣ የመሰብሰብ፣ የመጻፍ፣ የመናገር፣ በነፃ የመደራጀት መብቶች መረጋገጥን፤ ባጠቃላይ የህግ የበላይነት የሚረጋገጠባት ለሁሉም ኢትዮጲያዊ እኩል የሆነች ሕዝባዊ ሥርዓት የተመሠረተባትን አንድ ኢትዮጵያን እንደሆነ ይገንዘቡልን።

ሊነግሩን የፈለጉት በዚያን ጨለማ ዘመን ካለፍርድ በነፃ እርምጃ በቀይ ሽብር የታጨዱትን ሰማዕታት ይገባቸዋል ነው። ይህንንም ዓይነት የተንሻዋረረ አመለካከት እንደርስዎ ያለ ስለሚያስፋፋው ዛሬም ስለፖለቲካ እስረኞች እንኳ አንዳንድ መሪዎች ነን የሚሉ ሲያወሩ ከ1991 ዓ/ም ጀምሮ ካለአግባብ ታሥረው ደብዛቸው የጠፉ በአብዛኛው ኢህኢፓዎች የት አሉ እንኳ ብሎ ለመጠየቅ ያልቻሉ የተዳነዙ ሰዎች ስለሕግ የበላይነት ሊደሰኩሩብን ሲያምራቸው እያነን ነው። በኛ አመለካከት የህግ የበላይነት ሲባል እንኳንስ በጸረ-ወያኔነት የታገለና ያታገለ በመደዳው ሕዝብ የጨረሰው መንግሥቱ ኃ/ማርያም እራሱ እንኳ ካለህዝባዊ ፍርድ መነካት የለብትም ባዮች ነን። ለዚህም የርስዎን ጽሁፍ አንተርሰውም ሆነ በሌላ ጊዜ የአሲምባ የውይይት መድረክ ስለቅንጅት መሪዎች እንደማናስብ አድርጎ ለማሳየት ቢነዘብንም ትግላችን አሁንም ወደፊትም በሃገራችን ዳግም ቀይ ሽብር እንዳይመጣ በሁሉም መሪዎች ነን በሚሉ ጭንቅላት ውስጥ ለዘለዓለም እንዲደውል የምንፈልገውም ለዚህ ነው። የማንም ይሁን የማን ድርጅት ወይም አማለካከት ደጋፊ ተብሎ ወደ እሥር የማይወረወርበት፣ የማይገደልበት ሀገር መመሥረት እድንችል የርስዎን ዓይነት ድንቁርና ማጥፋት አለብን በለን አበክረን እናምናለን። ምክንያቱም ለሌላ ማዓት ያዘጋጀናልና።

በአንድ ቦታ ኢህአፓ “…የሠራተኛውን የማህበራት መንፈስ እስከወዲሁ ድረስ እንዲደበዝዝ ከፍተኛ ወንጀል…” ብለዋል። የሠራተኛውን የማህበራት መንፈስ ያደበዘዘው ኢህአፓ ሳይሆን የሠራተኛውን በነፃ የመደራጀት መብት በመፃረር ሥልጣንና ኃይልን በመጠቀም የሠራተናውን ማህበራት በራሳቸው ምስል ሊቀርጹ የተነሱ የዚያን ጊዜ የደርግ ኢሠፓዎችና የዛሬዎቹ በክልልና በዘር የሚያናክሱት ወያኔዎች መሆናቸውን መረዳት የማይፈልግ ራሱን ያመመው ብቻ ነው።

ለማጠቃለል፥

እኛ የአሲምባ የውይይት መድረክ መሥራቾች ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትንንቅ ያለፉና ሚና የነበራቸው ግለ ሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ከተሠሩ ስህተቶች አንዳቸውም ነፃ ነን ብለው እጃቸውን እንደጲላጦስ መታጠብ እንደማይችሉ እናምናለን። በዓፄው ዘመነ-መንግሥት ፤ በደርግ ፋሻሽታዊ ሥርዓትና በዛሬዎቹ ጠባብ ብሔረተኞች ጊዜ፤ በምንግሥት ደረጃ ጥቂት ቡድኖች ራሳቸውን በሥልጣን ተክለው ለዘላዓለም ለመኖር ሲፍጨረጨሩ የፈጸሙትን ጥፋት፣ በሕዝብ ያደረሱትን በድልና ግፍ ከሕዝቡ ለመከላከል ሲውተረተሩ እንደ ኢህአፓ ያሉ ሕዝባዊ ድርጅቶች የፈጸሙትን ስህተቶችና ከሚደርስባቸው ምት የተነሳ ያሳዩትን መዝረክረክና ግድፈት በማንኛውም ዓይነት መሥፈሪያ ለማነፃፀር መሞከር ራሱን የቻለ ስህተት ነው በለን እናምናለን።

ሌላው ደግሞ ልንገነዘበው የሚገባ ነገር ቢኖር ከ30 ዓምታት በፊት ሲውተረተር ራሱን ገምግሞ አነሰም በዛም የሰራቸውን ስህተቶች ለማረም የሞከረና አቅጣጫውን በይፋ የቀየረ በጊዜው ከነበሩ ኃይሎች በድርጅትም ሆነ በግለ-ሰብ ኢህኢፓ ብቻ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህንን ሁሉ ካልን በኋላ የአቶ ደዋ በኢህአፓ ላይ እጣታቸውን መቀሠር በአሁኑ ወቅት ጠቀሜታውና ዓላማው ምን ይሆን ብለን ስንጠይቅ ያገኘነው መልስ ምንም ነው። ሀገራችን እንድትፈርስ እየተመቻቸች፣ የህዝባችን ውስጣዊ ቅራኔው ተጋግሞ እርስ በእርስ ተፋጦ ወደማይሆን አቅጣጫ እየተገፋ እያለና ከመቼውም የበለጠ ሀገር ወዳዶች ወደአንድ ወገን መሰባሰብና ሀገራችንን ከጥፋት ለማዳን ልንረባረብ በሚገባን በአሁኑ ጊዜ ፤ በመካከላችን መተማመንን የሚያደርቅ ላለፉት 30 ዓመታት ልንተማመንባቸው ያልቻልንባቸውንና የሚያፋጥጡንን ደጋግሞ ማንሳት ሁላችንንም የትም አያደርሰንም። በዚህም ከቀጠልን በጥቂት ጊዜ ውስጥ የምንከራከርበትና የምንኮራረፍብት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አትኖርም።

ምጀመሪያ የመቀመጪያዬን እንዳለች ሁሉ ዝንጀሮ፤ ሀገራችንን የምንወድ ወገኖች ሁሉ ትላንት ያልተስማማንባቸውን ነገሮች ሁሉ ከጠረጴዛው አንስተን፤ ተከባብረን እየተዳማመጥን የምንከራከርብት ህዝባዊ ሥርዓት እስከምንመሠርት ጌዜ በይደር አቆይተን፤ ሀገር የማዳኑና ፍትኃዊ ሥርዓት መምጣትን የምናምን ፤ ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የማንደራደር ተሰባስበን ኃይላችንን አፈርጥመን በአንድ አቅጣጫ እንቅስቃሴ መጀመሩን ዋነኛ ተግባራችን እናድርገው።

በዚህ ሀገር አድን እንቅስቃሴ ደፍረን መሳተፍ ስንጀምር ካለጥርጥር ወደድንም ጠላንም መተማመንን በትግሉ ውስጥ ቀስ በቀስ እንገነባለን። ይቅር መባባሉንም እንደገና “ሀ” ብለን እንጀምራለን። ስህቶቻችንም ለመጠፋፊያ ሳይሆን የምንማማርባቸው መሠረቶች አድርገን አባቶቻችን ከሁሉ ጋር ተናጭተው በጥሩ የባህል ምግባር መሠረት አዋቅረው ያስረከቡንን ኢትዮጵያዊነትን መልሰን እናገኛታለን። ህዝባዊ ሥርዓትን ምሥርተን የህግ የበላይነት በሚረጋገጥባት ሀገር ምህረት አድራጊውም ከሳሹም ህዝብ ነው። ለዚህም ነው ዛሬ ያልተስማማንባቸውን ለህዝቡ ፍርዱንም እንተውለት የምንለው። ዛሬ በምንጫወተው ሚና በምናሳየው ምግባር ያለጥርጥር ህዝባችን ለሁላችንም ምስጋናውን እኩል ይሰጠናል። ምህረቱንም እንዲሁ። በህዝባችን እንተማመን። ዛሬ እኮ የሚገፋውን ያክል ኢትዮጵያን ይዞ ካለመሪ ከወያኔ ጋር ተፋጦ ያለ ህዝቡ መሆኑን አንርሳ።

ኢትዮጵያዊነት ያለጥርጥር ያቸንፋል!
ፍትኃዊ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ እንነሳ!

የአሲምባ የውውይይት መድረክ