የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባለፈው ሳምንት ኤርትራ የነፃነት ቀኗን ስታከብር በነበረበት ዕለት፣ ባድመ በሚገኘው የኤርትራ ጦር ላይ ጥቃት ማድረሱን ወታደራዊ ምንጮች ገለጹ፡፡ ጥቃቱ በትግራይ አካባቢ በቅርቡ በኤርትራ ጦር ታፍነው ለተወሰዱ ኢትዮጵያውያን አጸፋዊ ምላሽ ነው ተብሏል፡፡
ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የመከላከያ ሠራዊት ምንጮች እንደገለጹት፣ ግንቦት 16 ቀን 2004 ዓ.ም. የኤርትራን ድንበር ጥሶ የገባው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባድመ አካባቢ በሰፈረው በአንድ ብርጌድ የኤርትራ ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
በጥቃቱ በርካታ የኤርትራ ወታደሮች የመቁሰልና የሞት አደጋ የደረሰባቸው መሆኑን፣ እስከ ሻለቃ ማዕረግ ያላቸው በርካታ የኤርትራ ጦር አመራሮችም እጃቸውን የሰጡ መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከወራት በፊት በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጽመው የሽብር ጥቃት ተመጣጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይ አፋር ክልል ውስጥ የተገደሉትና ታፍነው የተወሰዱትን የአውሮፓውያን ቱሪስቶች ሴራ ያቀነባበረው የኤርትራ መንግሥት ነው ብሎ ያመነው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የመከላከያ ሠራዊቱ የኤርትራን ድንበር ጥሶ በመግባት ሽብርተኞች የሚንቀሳቀሱባቸው ናቸው ባላቸው ሦስት የጦር ካምፖች ላይ ጥቃት ፈጽሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ጥቃት ካካሄደ በኋላም ግን ትግራይ አካባቢ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው በኤርትራ ጦር እየታፈኑ እንደሚወሰዱ በተቃዋሚዎችም ሆነ በመንግሥት በኩል ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
የመከላከያ ምንጮች እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ጦር ሰሞኑን በኤርትራ ላይ የወሰደው ወታደራዊ ጥቃት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ አካባቢ ለሚፈጽሙት አፈና አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የወሰደውን ዕርምጃ በማስመልከት ከኤርትራ በኩል የተገለጸ ነገር የለም፡፡
Source: http://www.ethiopianreporter.com/news/2 ... 08-14.html



